>

ጠበቃው ....!!! (ጌታቸው ሽፈራው)

ጠበቃው ….!!!

ጌታቸው ሽፈራው

አርበኞች ግንቦት 7 “ፊሽካ ተነፍቷል” ብሎ ወደ ኢትዮጵያ የላካቸው የአርማጭሆ ልጆች ታሪክ እጅግ ገራሚ ነው። የሰሩት ታሪክ ያስደምማል።  የትግራይ ሚሊሻና ልዩ ኃይልን እንዳልሆነ አድርገውት አልፈው መጨረሻ ላይ ከመከላከያ ሰራዊት ጋር ነበር ፍልሚያቸው። የቆሰሉት አንማረክም ብለው ራሳቸውን ጨርሰዋል። ብቻውን ግዙፍ ታሪክ ነው።
በእርግጥ ድርጅቱ አለ እንዲባል እንጅ ታጋዮቹ ያደረጉትን ያህል ትንቅንቅ አይፈልግም ነበር። መታሰራቸው፣ መማረካቸው ራሱ የፖለቲካ ትርፍ ነበር። ድርጅቱ “አለሁ” ብሎ መንግስትን አስደንግጦበታል። ዳያስፖራውን ከዳር ዳር አንቀሳቅሶበታል። እነዚህ ልጆች ግን ጠበቃ እንኳን አልነበራቸውም። ይኑሩ ይሙቱ የሚያስታውሳቸው አልነበረም። መብታቸው ነው ተብሎ መንግስት “ጠበቃ አቁሜላችኋለሁ” ይላቸዋል።  ትንሽ አይተውት “ይህስ ከከሰሰን ዐቃቤ ሕግም አይሻል” ብለው “ይቅርብን” አሉ። ብቻቸውን ከዳኞቹም ከአቃቤ ሕጎቹም ጋር ለመከራከር ፍርድ ቤት ይቆማሉ። አስታዋሽ ያለው ደግሞ ሶስት አራት ጠበቃ ያስቆማል።
ብዙ ጊዜ ከፍርድ ቤት ሲመለሱ ከፍቷቸው ነው። መሳርያ ይዘው ስንቱን እንዳልጣሉ “ይሄ ከተማ ለከተማ የሚውል” የሚሉት ፖሊስ ክፉ ሲናገራቸው ይውላል። የዳኞቹ፣ የዐቃቤ ሕጎቹ ንግግር ያስቀይማቸዋል። ከዚህ ግባ የሚባል ትግል ያላደረገው ባለ ጠበቃ ነው። እነሱን ተረስተዋል።
 “ዝም ብለው በፈረዱብን ወዲያ” ይላሉ። ዳኞቹንም  “ላይሆን ነገር ባታመላልሱን ምን አለ? ዝም ብላችሁ ፍረዱብን” ይሏቸው ነበር። አንድ ቀን ግን ወደ እስር ቤት ሲገቡ እየተፍለቀለቁ መጡ። ቁጥቦች ናቸው። ጀግኖች ናቸው። ሰው ይወዳቸዋል። ጓጉተን ጠየቅናቸው። “ምን ተገኘ?”
“ከሰው ጋር እኩል ሆንነ” አለን ደሴ። “ተነሱ ተብለን ስንነሳ አንድ የተባረከ አሽከር እኔ እቆምላቸዋለሁ አለንኮ። ከሰው እኩል አደረገን። አይ እግዜር ይባርከው።” ይላል ራሱን ይዞ። “ታውቀው ይሆናል። ልጅ እግር ነው።  ግን ሽበት ጣል ጣል አድርጎበታል። ለእነ ንግስትም ሲከራከር ሳላየው አልቀርም። አይ… እግዜር ይስጠው” ይላል ደሴ። ሄኖክ አክሊሉን ነው።
ያን ጀግንነት የፈፀሙ አርበኞች ጠበቃ አልነበራቸውም። ብቻቸውን ሲቆሙ ሲመለከት ሄኖክ ቆመላቸው። ማመን አልቻሉም። ወደ እስር ቤት ተመልሰውም ይገርማቸዋል።  “አይ እግዜር ይስጠው፣ እንዲህ አይነትም ሰው አለ።” ይላሉ። ክሳቸው አስፈሪ ነው። ለሌላ ጠበቃ ቢሆን የእነ ገብሬ ንጉሴ ክስ መዝገብ በትንሹ በመቶ ሺህ ብር ያስጠይቃል።  ሄኖክ አክሊሉ በነፃ ቆመላቸው።  ሌሎች ብቻቸውን የሚቆሙ የሽብር ተከሳሾችን ከእነ አለልኝ ምህረቱ፣ ወንድሙ ኢብሳ ጋር ሆኖ ተከራከረላቸው።
እንደ ሄኖክ ያሉት  ለተከሳሾች በነፃ ብቻ አይደለም የሚከራከሩላቸው። የራሳቸውን ገንዘብ ከፍለው ነው። ማመልከቻ ይፅፉላቸዋል። ለቤተሰብ ደውለው፣ ተደዋውለው ማስረጃ ይሰበስቡላቸዋል። ወደ እስር ቤት ሲሄድ ከኪሱ ያለውን “ለሻይ” ብሎ ሰጥቶ ይመለሳል።
“ለውጥ” ተብሎ እስረኞች ተፈቱ። እንደገና እስር ሲጀመርም ሄኖክ ለብዙዎቹ ጠበቃ ሆነ። ለእነ እስክንድር ነጋም ጠበቃ ነው። እስር ቤት ሆነው እንዲወዳደሩ ብዙ ለፍቶ አሸንፏል።
ስለነ ሄኖክ ሳስብ እሸማቀቃለሁ። አዝናለሁ። ዋጋ የከፈለ፣ ጠበቃ ለሌላቸው ጠበቃ የሆነውን አናስታውሰውም። ሌላው ቀርቶኮ የፍትሕ ብሔር ክስ ላይ ጠበቃ የምናፈላልገው ድሮ “እንዴ ሽብር? ምን ሆነሃል? አልፈልግም” እያለ በሽብር ለተከሰሱት በገንዘብም እንዲቆም ሲጠየቅ አሻፈረኝ ሲል ለኖረው ነው። በአብዛኛው።
ጥብቅና ከሚከበረው በላይ በጣም ክብር ያለው መሆኑን የተረዳሁት በዶክተር ያዕቆም ኃይለማርያም ነው። ማንም ለማያስታውሳቸው የጉራፈርዳ፣ የኦሮሚያ፣ የቤንሻንጉል ተፈናቃዮች በነፃ ይቆሙላቸው ነበር። ከዶክተር ያዕቆብ ቀጥሎ በእነ ሄኖክ አክሊሉ አይቸዋለሁ። ገንዘብ ተፈልጎ ሳይሆን የራስን ገንዘብ ተከፍሎ የሚሰራ ሙያ መሆኑን አይቻለሁ። አሁን ደግሞ ከግለሰቦችም በላይ ለአዲስ አበባም ጠበቃዋ ነው። ለእነ እስክርድር ጠበቃቸው ነው።
(ፎቶዋን ከችሎት ውሎ በኋላ ቀሪውን ሰዓት እየቀለድንም፣ እያዘንም፣ ……ከምናሳልፍባት ካፍቴርያ ራሴ ነው ያነሳኋት)
Filed in: Amharic