>
5:26 pm - Friday September 15, 1656

የዛሬዋ ኢትዮጵያና የነገ ውሎዋ (ክፍል ፪ በአንዱ ዓለም ተፈራ)

የዛሬዋ ኢትዮጵያና የነገ ውሎዋ (ክፍል )

 

ነፃ አስተያየት፤ በአንዱ ዓለም ተፈራ


ያለንበትን ሀቅ አለመረዳት፤ ሊከተል የሚችለውን ክስተት አያስቀረውም።

 

ዛሬ በአገራችን ያለው የተመሰቃቀለ የፖለቲካ ሂደት፤ ለአገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን በጣም አሳሳስቢ ነው። በርግጥ እስከዛሬ በተደጋጋሚ፤ “አገራችን አደጋ ላይ ነች!” “ይህን አጋጣሚ ሳንጠቀምበት ካሳለፍነው፤ የሚከተለው አስፈሪ ነው!” የመሳሰሉት ሲነገሩ ነበር። ብዙ ጥሩ አጋጣሚዎች፤ መጥተው አልፈዋል። ሳንጠቀምባቸው አምልጠውናል። በትክክል ለማቅረብ፤ ዕድሉን አባክነነዋል። የዛሬው ከስካሁኖቹ በጣም የተለየ ነው። ከውጪ እየተደረገ ያለው ተፅዕኖ፣ በአገር ውስጥ ያለው የፅንፈኞች አላባራ ያለ አረመኔያዊ ድርጊት፣ የኮቢድ ተስቦ በሽታ፣ ለሃያ ሰባት ዓመታት በትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር የተተበተበውና የተቀበረው የዘር አገዛዝ ረመጥ፣ ቁርጡ ያለታወቀ የትናንቱ ኢሕአዴግ፤ የዛሬው ብልፅግና ፓርቲ አገዛዝ ተደማምሮ፤ አደጋውን ከመቼውም በላይ በተለየ አግዝፎታል። እንደምንረዳው የትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባር ከቦታው መልቀቁ ብቻውን በቂ አይደለም። ይልቁንም በትግሬዎቹ ፋንታ ሌላ ተተክቶ ያንኑ ስርዓት ከነመዘዙ አያካሄደ ነው። የጠገበው ጅብ ሄዶ፤ የተራበው ጅብ ተተክቷል ማለት ይቻላል። ግድያውና ማሳደዱ፣ ንብረት ማውደሙና የሃይማኖት ተቋማት ላይ ያላባራ ዘመቻው፣ ሕግ አክባሪዎች መታሰራቸውና ሕገ ወጦች እንደልባቸው መቧረቃቸው፤ እንደቀጠለ ነው። እስከመቼ!!! ጉዳዩ የሚመለከተን ምን እያደረግን ነው? ኃላፊነታችንን እየተወጣን ነው ወይ? የአደጋውን ክብደት ተረድተናል ወይ? ይሄ አዝማሚያስ ወደ ሌላ ተተኪ አምባገነን እየወሰደን ነው ወይ? እስኪ በዚህ ላይ እናተኩር!

ጉዳዩ  የሚመለከታቸው ችላ ብለው፣ ዝምታን መርጠው፣ በያሉበት በሌላ ክንውን ላይ ሲጠመዱ፤ ጉዳዩ የማያገባቸው፣ ዕውቀቱ የሚጎድላቸው፣ ተከታይ ጉዳቱ የነሱ ያልሆነባቸው፣ ባጠቃላይም ተጠያቂነት የሌላቸው ሰዎች መድረኩን ይጨብጡታል። ሂደቱንና ትርክቱን ወዳልሆነ አቅጣጫ ይመሩታል። የሚከተለው ምን እንደሚሆን ለመገመት፤ ሊቅነት አይጠይቅም። ዛሬ ይሄን በአገራችን ላይ ያንዣበበ አደጋ በውል ተገንዝበን፣ አገራዊ ውይይት አድርገን፣ ወደ መፍትሔው አብረን ካልተጓዝን፤ የተገጣጠመ መፀፀቻ ቦታና ጊዜ፤ ነገ አይኖረንም። ይህን ለማድረግ ደግሞ፤ ሁላችንን የሚያግባባ ራዕይ ሊኖረን ይገባል። ልሂቃንን ወይንም ባለሥልጣናትን ማዕከል ያደረገ መፍትሔ አይሠራም። አገራችን ካንዣበበባት አደጋ የምትድነው፤ ሕዝቡን ያማከለ ራዕይ ሲኖር ነው። የደርግን አረመኔ አገዛዝ፤ ኢትዮጵያዊያን በፍርሃት፣ በድንጋጤና ግራ በመጋባት፤ በተለያየ መንገድ እየተደነባበርን አለፍነው። የትግሬዎቹን ነፃ አውጪ ግንባር ደግሞ፤ በመደናገር፣ ባለመግባባትና በየጎጇችን በመታጎር አለፍነው። አሁን በሩ ተከፈተ፣ ብርሃን ገባ ብለን ስንነሣ፤ የተቀፈደድንበት ገመድ አልለቀን አለ። በአማራው ላይ እየደረሰ ያለው በደል እየባሰ መጥቷል። የተለመደ እኔን ምረጡኝ ውድድር፤ ይደለቅለታል። በሥልጣን ላይ ያለው ፓርቲ ሁሉንም አድራጊ ፈጣሪ ነው። ምርጫው ይካሄዳል፤ ግን ምንም ዓይነት ለውጥ መጠበቁ የዋህነት ነው። የአገራችን የፖለቲካ ሀቅ ይህ ነው።

በመጀመሪያ ከውጪ ሀገራትና ኃይላት የሚደረገው ጫናና ጫጫታ፤ ጊዜያዊ ነው። አብዛኛውን ጊዜ በመንግሥት ሥልጣን ላይ የተቀመጡ ሹሞች የተጠመዱት፤ የሥልጣን ኮርቻቸውን ለማደላደልና ለማርዘም ነው። በጣም ሠልጥነዋል ከተባሉት አገራት እስከ ኋላ ቀር የተባሉት ድረስ፤ ይሄ ሀቅ ነው። የዶናልድ ትራምፕን አጉራ ዘለል ተግባር እያየነው ነው። የሶስተኛ አገራት መሪዎች የተዘገበው ታሪካቸው ይሄው ነው። በርግጥ፤ ምክንያት ያለው የውጪ አገራት ተንኮል፤ በአገራችን የፖለቲካ ሂደት ጣልቃ ገብነቱ አይሏል። ይሄ አይካድም። የፖለቲካ ግብና ዓላማ አንግበው ነው የተነሱትና አታሞውን የሚደልቁት። ይህ ድርጊት በአገራችን ያለውን የገዢ ክፍል ሁለት ምርጫዎች ሠጥተውታል። አንደኛው ምርጫውን በማካሄድ ሕጋዊነትን አግኝቶ፤ ሁሉን እኔ አደርጋለሁ በማለት፤ አገዛዙን መቀጠል ነው። ሁለተኛው ደግሞ፤ ከላይ የተዘረዘሩትን አደጋዎች በውል አገናዝቦ፤ አገር በቀልና የውጪ ኃይላት የደቀኑብንን ጣልቃ ገብነት ለመገላገል፤ ኢትዮጵያዊያን ከመንግሥታቸው ጋር ሆነው እንዲቆሙ፤ “አንድ አገር! አንድ ሕዝብ! አንድ ሰንደቅ ዓለማ!” ብሎ መነሳት ነው። 

የመጀመሪያው ምርጫ፤ ቀላሉና የተለመደው መንገድ ነው። ለውጪ ጣልቃ ገቦች፤ “ጠላቶቻችን!” እያሉ የራስን አታሞ መደለቅ ነው። ለማንኛውም ችግር፤ “መጡብህ!” እያሉ ማስፈራራት ነው። “ሁሉን ትተን ስላገራችን ብቻ እንቁም!” “መጀመሪያ አገር ስትኖር ነው!” “አሁን ዓይኖቻችንን ጨፍነን፤ መሪዎቻችንን እንደግፍ!” እያሉ መጮህ ነው። ይህ ለጊዜው ሲሠራ፤ አደጋው ለነገ የተዳፈነ ረመጥ ነው። ገዢውን ሹም፤ “እንዳሻህ አድርግ!” ብሎ ነፃ ሜዳ የሚለቅለት ነው። ትርፉ ለዘመናት የሚቆይ የቆላ ቁስል ነው።

ሁለተኛው ምርጫ፤ ግልጥ የሆነና ቅንነትን ብቻ የሚጠይቅ ኢትዮጵያዊ ተቆርቋሪነትን የያዘ ነው። የሚነሳው፤ “እኒህን ያፈጠጡ ችግሮች የምንቋቋማቸው፤ በአንድነት ስንነሳ ነው!” ብሎ ከማመን ነው። አንድነት፤ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ስላዘዘ የሚመጣ ክንውን አይደለም። ከሕዝቡ ልብ የሚመነጭ፤ አገር ወዳድነት ነው። አሜሪካም ሆነች ግብፅ፣ ሌሎች አገራትም ሆኑ አውሮፓ፤ የኢትዮጵያን ጥቅም እንጂ፤ የእከሌን ወይንም የእከሊትን ባለሥልጣናትን ጥቅም አይደለም ሊያጠቁ የተነሱት። ስለዚህ ይህን ጥቃት መቋቋም ያለባቸው፤ ባለሥልጣናት ብቻቸውን ሳይሆኑ፤ መላ ኢትዮጵያዊያን ነን። ይህ እንዲሆን ደግሞ፤ መላ ኢትዮጵያዊያንን ያቀፈ ራዕይና አመራር እንዲኖር የግድ ይላል። ሕዝብ ያለ አገር እንደማይኖር ሁሉ፤ አገርም ያለ ሕዝብ ትርጉም የለውም። ሕዝቡን በትክክል የማይመራ ገዢ ክፍል፤ ሕዝቡን አይወክልም። አሁን ባለው የኢትዮጵያ የፖለቲካ እውነታ፤ የችግሮቹ መጠንና ክፋት፤ ጥልቀት ያለው ተቆርቋሪነትና አገር ወዳድነትን ይጠይቃል። ከመንግሥት በኩል፤ ከራስ ሥልጣን በፊት አገርን ማስቀደምን ይሻል። ከሕዝብ በኩል፤ ሙሉ በሙሉ መንግሥቱን የኔ ብሎ ማቀፍን ይፈልጋል። እኒህ ሊገጣጠሙ የሚችሉት፤ አገር አቀፍ የሆነ ራዕይና መሪ ሲኖር ነው። ለውጪ ወራሪዎች መሳሪያ የሆኑትን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ርዝራዥና የኦነግ ሸኔን ኃይል ጨርሶ መልቀምና መደምሰስ አስፈላጊ ነው። በዘር የከፋፈለን አገዛዝ ማስወገድ ያሻል። ይህ ከችግሮቹ አንጻር ባንድ ቀን የሚተገበር አይደለም። ጊዜን ይጠይቃል፤ መሥረቱ ግን መጣል አለበት።

ይሄን ሁለተኛ ምርጫ ትቶ፤ በተለመደው መንገድ፤ የውጪ አገራትና ኃይላትን ጣልቃ ገብነት በማሳበብ የአገርን የፖለቲካ ቅኝት ለራስ ግብ መምራት አደጋ አለው። ምርጫው ይካሄዳል። በሥልጣን ላይ ያለው ፓርቲ ሕጋዊነት አገኘሁ ብሎ፤ ያለውን ይቀጥልበታል። አሁን በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ እውነታ፤ አምባገነንን በሥልጣን ላይ ለማስቀመጥ ምቹ መሆኑን ማወቅ አለብን። አንዳንዶች እንደሚይስቡት አምባገነንነት በአንድ ቀን፣ በአንድ ቦታ ላይ ቡልቅ ብሎ የሚከሰት አገዛዝ አይደለም። ብዙ ታሪካዊ አጋጣሚዎች ባንድ ላይ ሰምረው መሰለፍ አለባቸው። የቀውስ፣ የአደጋና የትርምስ ዳመና ባገር ላይ ማንዣበብ አለበት። ዴሞክራሲን ለማስፈን የቆሙ ተቋማትና አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ወደ ጎን መገፋት አለባቸው። ተቋማቱ ነበሩ ብለን ካመን! አድርባዮችና አቁላቢዎች የሥልጣን ሰልፉን እንደ ጎርፍ መምራት አለባቸው። ግድ የሌሾች መድረኩን ማጣበብ አለባቸው። ይሄንን ለመጋለብ የተዘጋጀ ቁንጮውን መጨበጥ አለበት። የዚህ ሂደት እንግዲህ፤ ዝግጅትና ጊዜን የሚጠይቅ ነው። የእስካሁኑ የአገራችን የፖለቲካ ሂደት ለዚህ አዘጋጅቶናል ብዬ አምናለሁ።

ከውጪ አገራት በኩል፤ እንደልባቸው የሚያዙትና የነሱን ጥቅም የሚያስጠብቅላቸው መንግሥት ለማስቀመጥ፤ ምን ጊዜም አባርተውልን አያውቁም። ችግራችን ራሳችን የምንፈጥረው አምባገነን ነው። ኢትዮጵያን እንዳትሆን አድርጎ፣ አገራችን አገር ወዳድ ወጣት አልባ አስቀርቶ፣ ራሱ ጅራቱን ቆልፎ የሸመጠጠው አረመኔው መንግሥቱ ኃይለማርያም፤ ባንድ ቀን አምባገነን አልሆነም። በተንኮል ልቡ ተበርዞ፣ በመሰሪነት አእምሮው ደንዝዞ፣ በአማራ ጥላቻ ደሙ ተበርዞ፣ በክፍፍል መርዝ ኢትዮጵያዊያንን እርስ በርስ እንድንፋጅ አዘጋጅቶ፤ ተሸማቆ ወደ ሕልፈቱ የወረደው መለስ ዜናዊ፤ በአንድ ዕለት አምባገነን አልሆነም። የአገራችን የፖለቲካ ሂደት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ነው። ከላይ የተዘረዘሩት የአምባገነን ለም መሬት መገኘቱ ገሃድ ነው። የአማራ ብልፅግና ፓርቲ፤ አማራውን የሚወክልና ለአማራው የቆመ ሳይሆን፤ ትናንት አማርኛ ተናጋሪ የትግሬዎች ነፃ እውጪ ግንባር እንደነበር ሁሉ፤ ዛሬም አማርኛ ተናጋሪ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀኝ እጅ ሆኗል። ሌሎች በአገሪቱ ያሉ የተለያዩ የብልፅግና ፓርቲዎችም እንዲሁ ናቸው። ( ክፍል ፫ ይቀጥላል )

Filed in: Amharic