>
5:18 pm - Thursday June 15, 5578

እስቲ ዶሴው ይውጣ. . . ?!? (አቻምየለህ ታምሩ)

እስቲ ዶሴው ይውጣ. . . ?!?

አቻምየለህ ታምሩ

የሕወሓት መስራቹ አረጋዊ በርሄ በትናንትናው እለት ከምኒልክ ቴሌቭዥን ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ  ሕወሓት አማራን በጠላትነት የፈረጀበት ማኒፌስቶ የድርጅቱን መስራች አባላት አስተሳሰብ በሙሉ የማይወክል መሆኑን ጠቅሶ አማራ በጠላትነት የተፈረጀበት የሕወሓት ማኒፌስቶ ይፋ በተደረገ በስድስት ወሩ በኮንፍረስ እንደተቀየረና ማኒፌስቶውን ያዘጋጁትም እነ መለስ ዜናዊ [መለስ ዜናዊ የሕወሓት መስራች አባል እንዳልሆነ ልብ ይሏል]፣ ስብሀት ነጋ፣ ስዩም መስፍንና ዓባህ ፀሐዬ መሆናቸውን ነግሮናል።  
 
አረጋዊ በርሄ ዶክተርነቱ ሳይከብደው እንዲህ አይነት ነጭ ውሸት በቴሌቭዥን መስኮት ብቆ ብሎ ለመናገር የደፈረው የመሰረተውና ለአስር ዓመታት ያህል የመራው ሕወሓት ተጀምሮ እስኪጨረስ  ድረስ፤ የተጠነሰሰው፣ የተወለደው፣ ያደገው፣ የጎለመሰው፣ ለመንግሥትነት የበቃውና መልሶም ወደ ሽፍትነት የገባው ባዘጋጃቸው ፕሮግራሞቹ ሁሉ አማራን በጠላትነት ፈርጆ ለማጥፋት መሆኑን ዘንግቶት አይደለም። 
 
አረጋዊ በርሄ ሕወሓት አማራን በጠላትነት የፈረጀበት ማኒፈስቶ ስድስት ወራት ብቻ የቆዬ፣ በሱና የአስተሳሰብ አጋሮቹ በሆኑ ሕወሕታውያን የውስጥ ትግል ከስድስት ወራት በኋላ በኮንፍረንስ የተቀየረ እንደሆነ አድርጎ  በማቅረብ ወጣቱን  የሚያሳስተው የሚዋሸውን ሁሉ ከስር ከስር እየተከታተለ የሚያጣራ፣ የሚመረምርና በማስረጃ የሚያጋልጥ ሰው ይኖራል ብሎ ስላላሰበና እየኖርንበት ያለው ዘመን የማይዋሽበት ዘመን መሆኑን ዘንግቶ ነው። 
 
በነገራችን ላይ አረጋዊ በርሄና በአስተሳሰብ ስለተለዩ ሳይሆን በልዩ ልዩ የግል ምክንያት ከሕወሓት እንዲወጡ የተደረጉና የተባረሩ  የትግሬ ብሔርተኞች ሁሉ ሕወሓት አማራን ለመጀመሪያ ጊዜ በጠላትነት ስለፈረጀበቱ የ1968ቱ ማኒፈስቶ የሚናገሩት ነገር ተመሳሳይ ነው። ግደይ ዘርዓ ጽዮን በ2010 ዓ.ም. “ከትግል ትዝታዎቼ፡ የደደቢት አብዮት በሴረኞች መቀጨት” በሚል ርዕስ ባሳተመው የቅጥፈት መጽሐፉ፣ ገብሩ አስረት በ2007 ዓ.ም.  “ሉዓላዊነትና ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ” በሚል  ባሳተመድ ድሪቶ ያስተጋባው ተረት አረጋዊ በርሄ ትናንትና  በምኒልክ ቴሌቭዥን ሊነግረን የፈለገውን ቅጥፈት ነው። 
 
እኔ ለነዚህ የሕወሓት ሰዎች የነበረኝ ጥያቄ ሕወሓት አማራን ለመጀመሪያ ጊዜ በጠላትነት የፈረጀበትን የ1968 ዓ.ም. ማኒፌስቶ በስድስት ወራት ውስጥ ከቀየረ ተቀየረ የምትሉትንና አማራ በጠላትነት ያልተፈረጀበትን  ድርጅቱ ከ1968 ዓ.ም. – 1983 ዓ.ም. የተጋገለበትን ማኒፌስቶ አቅርቡና አሳዩን  የሚል ነበር። ሆኖም ግን አንዳቸውም ሕወሓት አማራን  ለመጀመሪያ ጊዜ በጠላትነት ስለፈረጀበቱ  ስለ1968ቱ ማኒፌስቶ እንጂ ከዚህ ማኒፌስቶ በኋላ ሕወሓት ነበረው ስለሚሉት ማኒፌስቶ አውርተውም ማኒፈስቶውንም አሳይተውን አያውቁም።
 
የምንኖርበት ዘመን እውነትን ለሚሻ ሁሉ እስከጥግ ድረስ መሄድና ማጣራት የሚቻልበት ዘመን ላይ በመሆናችን ሕወሓታውያኑ ስለ መጀመሪያው የጫካ ትግላችው የሚዋሹትን ቅጥፈትም ለማጋለጥ ዛሬ ላይ የመንፈስ አባቶቻቸው የነበሩት እነ ፖል ሔንዝ ያከማቹትን መዘክር ሁሉ መበርበር ይቻላል።  
 
ከላይ የታተመው ሕወሓት ለሁለተኛ ጊዜ አማራን በጠላትነት የፈረጀበት ፕሮግራሙና ድርጅቱ በሚያዚያ/ግንቦት 1975 ዓ.ም. ሁለተኛውን ኮንግረስ ካካሄደ በኋላ ያወጣውን ሕገ መንግሥትም ያገኘሁት የነፍስ አባታቸው የነበረው ፖል ሔዝን በማሕደር የከዘነውን የሕወሓት ጉድ ሳገላብጥ ነው። ከዚህ የሕወሓት ሁለተኛ ድርጅታዊ ፕሮግራም ማየት እንደሚቻለው የነበረው እውነት አረጋዊ በርሄ ዛሬ እንደሚለው ሳይሆን ሕወሓት አማራን በጠላትነት ፈርጆ ለማጥፋት የታገለው በ1968 ዓ.ም. ባወጣው ማኒፈስቶ ብቻ ሳይሆን በ1975 ዓ.ም. ባደረገው ሁለተኛ ኮንግረሱም አማራ ጠላት መሆኑን በኮንግረስ  አስጽድቆ ለሁለተኛ ጊዜ በፕሮግራሙ ላይ አስፍሮት ነበር።   
 
ይህንን እውነት ከላይ በተያያዘው  የሕወሓት የ1975 ዓ.ም. [እ.ኤ.አ.በ1983 ዓ.ም.] ሕገ መንግሥት ወይም ማኒፌስቶ በግልጽ  ማየት ይቻላል። በቢጫ ቀለም ያቀለምሁት የሕወሓት የ1975 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት በግልጽ እንደሚያሳየው ሕወሓት አማራ እንደ ሕዝብ ጠላት መበየኑንና የሚታገለው ይህንን ጠላት አድርገው የፈረጁትን አማራን ለማጥፋት መሆኑ ቃል በቃል ሰፍሮ እናገኘዋለን።     
 
ልብ በሉ! ሕወሓት  በ1975 ዓ.ም. ሁለተኛ ድርጅታዊ ኮንግረሱን አድርጎ ይህንን አማራን በድጋሜ በጠላትነት የፈረጀበትን ፕሮግራሙን ሲያውጅ አረጋዊ በርሄ የሕወሓት ወታደራዊ መሪ ነበር። የሕወሓት ወታደራዊ መሪ ሆኖ በመራው ድርጅታዊ ኮንግረስ አማራን በጠላትነት አስፈርጆ  እንዲጠፋ ለመታገል የተዋዋሉበት በኮንግረሳቸው ያጸደቁትን ፕሮግራም  ክዶ ነው እንግዲህ አረጋዊ በርሄ  አማራን በጠላትነት የተፈረጀበት ማኒፌስቶ የድርጅቱን መስራች አባላት አስተሳሰብ በሙሉ የማይወክል፣ ይህ በ1968 ዓ.ም.  ይፋ የተደረገ ማኒፌስቶም  በስድስት ወሩ በኮንፍረስ የተቀየረና ማኒፌስቶውን ያዘጋጁትም እነ መለስ ዜናዊ፣ ስብሀት ነጋ፣ ስዩም መስፍንና ዓባህ ፀሐዬ መሆናቸውን ዓይኑን በጨው አጥቦ ንጹሕ መሆኑን ሊነግረን የሚቃጣው።  
 
ባጭሩ በቤተ ሕወሓት አማራ በጠላትነት የተፈረጀው አረጋዊ በርሄ ሊነግረን እንደፈለገው የሁሉን መስራች አባላት አስተሳሰብ በማይወክል አኳኋን  በ1968 ዓ.ም.  ይፋ በተደረገውና በስድስት ወሩ በኮንፍረስ እንደተየቀረ ሊነግረን በፈለገው ፕሮግራሙ ብቻ ሳይሆን አረጋዊ በርሄ ራሱ የሕወሓት መሪ በነበረበት በ1975 ዓ.ም. በተካሄደው የሕወሓት ሁለተኛ ኮንግረስ በጸደቀው ድርጅታዊ ሕገ መንግሥት ጭምር ነበር። 
 
አማራን በ1968 ዓ.ም. እና በ1975 ዓ.ም. ባወጣቸው ፕሮግራሞቹ በጠላትነት የፈረጀው ሕወሓት ለ27 ዓመታት አገር ሲመትር ኖሮ  ከግፍ ሥልጣኑ ከተወገደና ካለፈው ኅዳር ወር ወዲህ ድጋሚ እንዲሸፍት ከተገደደ በኋላም በጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ በዐቢይ አሕመድ፣ በአየር ኃይል አዛዡ በይልማ መርዳሳ፣ በኢታማጆር ሹሙ በብርሃኑ ጁላና በምድር ኃይሎች አዛዡ በአስራት ዴኔሮ እየተደበደበ ባለበት በዚህ ወቅትም “የሴንትራል ኮማንድ” አመራር ነው  በተባለው በጻድቃን ገብረ ተንሳይና በቃል አቀባዩ በጌታቸው ረዳ በኩል ከተደበቀበት የቀበሮ ጉድጓድ በሚሰጠው መግለጫም የሚናገረው ዛሬም የሚታገለው የአማራን ጭቆና እንደሆነ ነው።
Filed in: Amharic