በምስራቅ ወለጋ ሶስት አማራዎች ተገደሉ…!!!
አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ
በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሞ ወረዳ አሹ ቀበሌ 3 አማራዎች በአሸባሪው ኦነግ ሸኔና በተባባሪዎቹ በጥይት ተገድለዋል።
ሁለት አባቶችና አንድ ህጻን ልጅን በአሹ ቀበሌ ልዩ ስሙ ጉቴ ጊዮርጊስ በተባለ አካባቢ ዛሬ ግንቦት 29 ቀን 2013 ረፋድ ላይ በአማራዊ ማንነታቸው ብቻ በጨካኞች መገደላቸውና ስርዓተ ቀብራቸው መፈፀሙ ነው የተሰማው።
በምስራቅ ወለጋ ዞን በተለይም በኪረሞ፣በጊዳ አያና እና በሊሙ ወረዳዎች አማራዎች በየጊዜው እየተገደሉ፣እየቆሰሉ፣እየተሳደዱና እየተፈናቀሉ መሆኑን በመግለፅ መንግስት አድሎአዊነቱን ትቶ እንዲደርስላቸው ሲጠይቁ መክረማቸው ይታወቃል።
በሌላ ዜና የሽብር ቡድኑ በሆሮ ጉድሩ ዞን አቢ ደንጎሮ ወረዳ ቡለንቴ ቀበሌ ልዩ ስሙ ሶዮማ በሚባል አካባቢ ባሉ ሚሊሾች ላይ ተኩስ ከፍቶ እንደነበር ተገልጧል።
ተኩሱን የከፈተው ግንቦት 29 ቀን 2013 ከቀኑ 10:20 ላይ ሲሆን ከፍተኛ ቁጥር ያለው የኦነግ ሸኔ ቡድን ገበሬዎችን ለማፈን ያደረገው ጥረት በሚሊሻዎች የአፀፋ ምላሽ ከሽፎ ከአከባቢው መሸሹ ተሰምቷል።
ቡድኑ ከሚሊሾች ጋር ለአጭር ጊዜ የተኩስ ልውውጥ ባደረገበት ወቅት በስፍራው የነበሩ የኦሮሚያ ክልል የፖሊስ አባላት ከተኩሱ በፊት ቀድመው ሻወር ልንወስድ ነው በሚል መሸሻቸውንና ሚሊሻዎችን ለማገዝ በሚል የተነሱ ታጣቂዎችን ተመለሱ የማለታቸውን ጉዳይ ግን ለምን ? ሲሉ በጥርጣሬ እንደሚመለከቱት ጠቁመዋል።