>
3:44 pm - Friday March 31, 2023

ምርጫ እና እሪባን ቆረጣ...!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

ምርጫ እና እሪባን ቆረጣ…!!!

ያሬድ ሀይለማርያም

በምርጫ ዋዜማ የገዢው ፖርት ሹማምንት ከጠዋት እስከ ማት፤ በየቀኑ ከፋብሪካ እስከ ውሃ መውረጃ ቱቦ እያስመረቁ እሪባን ሲቆርጡ መዋላቸው ወደው እንዳይመስላችሁ። በምርጫ ክርክር ሊያማልሉት ያልቻሉትን ሕዝብ እነሱን እንዲመርጥ ተጽዕኖ ሊፈጥሩበት የሚችሉት ብቸኛ እና የቀሩዋቸውን መንገዶች እየተጠቀሙ ይመስላል። እነዚህ እድሎች ለተፎካካሪ ፖርቲዎች ክፍት አይደሉም። ሊሆኑም አይችሉም። የተቃዋሚዎች ስስ ብለት፤  እነሱ ሊጠቀሙባቸው አይችሉም።
የመጀመሪያው ስልት፤ የልማት ተቋማትን፣ መንገድ፣ ትምህርት ቤት፣ ጤና ጣቢያ እና የመሳሰሉ ቀድሞ የተጀመሩ ሥራዎችን ከምርጫው በፉት አጣድፎ፤ ሥራው እንኳ ባያልቅ እንዳለቀም አድርጎ መመረቅ ነው። በዚህ ሰሞን ከክልል ሹማምንት አንስቶ እስከ ቀዳማዊ እመቤት ድረስ የሹሞቹ ውሎ በምርጫ ቅስቀሳ የምርቃት ዜናዎች ላይ ያተኮሩ ናቸው (እዚህ ላይ ለቀዳማዊ እመቤቷ ድንቅ ስራዎች ያለኝ አክብሮት እንደተጠበቀ ነው)። በአንድ ቀን ብቻ የአዲስ አበባ ም/ከንቲባዋ ስንት መንገድ አስመረቁ ነበር የተባለው?
ሁለተኛው ስልት፤ ነገ ሊሰሩ የሚችሉ እና በሕዝቡ ህይወት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊፈጥሩ ይችላሉ ቀሚባሉ ጉዳዬች ላይ ተስፋ የሚያጭሩ ስምምነቶችን ከመፈረም አንስቶ የመሰረት ድንጋይ መጣል ነው። 500,000 ቤቶች እንገነባለን ከሚል ስምምነት አንስቶ የሆስፒታል፣ የትምህርት ቤት፣ የመንገድ እና ሌሎች የልማት ሥራዎች መጀመራቸውን የሚያሳዩ የመሰረት ድንጋዮችን በሚዲያዎች ተከቦ መጣል እና ስምምነቶችን መፈራረም። ይሄንም ተቃዋሚዎች ሊያደርጉት አይችሉም።
ሦስተኛው ስልት ሕዝብን ጥልቅ ስጋት ውስጥ መጨመር ነው። ይሄን ስልት ብዙ አንባገነን ፖለቲከኞች የሚጠቀሙበት ነው። እየደጋገሙ አገሪቷ እና ሕዝቡ በውጭና በውስጥ ጠላቶች እንደተከበቡ፣ መተላለቅ ሊከሰት እንደሚችል እና ሕዝብ ከመንግስት ጎን ካልቆመ የምጽአት ቀን መቅረቡን የሚያሳዩ ዛቻና ማስፈራሪያዎች ነጋ ጠባ በመንግስት መገናኛ ብዙሃን ማዥጎድጎድ። ለዚህም የጠቅላዮን፤ የባንዳና የባዳ ትርክት ልብ ይለዋል። እርግጥ ነው ኢትዮጵያ ዛሬ በብዙ አደጋዎች ተከባለች። ከከበቧት አደጋዎች አብዛኛዎቹ በራሱ በአገዛዝ ሥርዓቱ ክሽፈት የተፈጠሩ ናቸው። የአደጋዎቹ መጠን እና ግዙፍነት ጠንካራ የሆነ የጸጥታና የአገር መከላከያ ሠራዊት መኖርን የግድ የሚሉ ናቸው። እነዚህ አካላት ደግሞ በገዢው ፖርቲ አምሳያ የተቀረጹ እና ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታም በገዥው ፖርቱ ቁጥጥር ስር ያሉ አካላት ናቸው። ስለዚህ አደጋ ይመጣል ብሎ ለደህንነቱ የሚሰጋ ዜጋ ቢያንስ ይችን ቀን ለማለፍ የደህንነት እና በመከላከያ ጡንቻው የፈረጠመውን ብልጽግናን የሙጥኝ ቢል አይፈረድበትም። ከመሞት መሰንበት እንዲሉ።
የሚያሳዝነው የመገናኛ ብዙሀኑም ሙሉ ቀን የሹማምንቱን ጭራ በየጥሻው ጭምር እየተከተሉ ቱቦ፣ ድልድይ፣ መንገድ፣ ወዘተ ሲያስመርቁ እና የብልጽግናን ግስጋሴና ከሹሞቹ ኪስ በተገኘ ገንዘብ የተሰራ እስኪመስል ልግስናቸውን ሲያነሱ ሲጥሉ ያመሻሉ። ለአንዳፍታ ደግሞ ምርጫ ቦርድ ለክርክር በመደበው አጭር ሰዓት ገዢው ፖርቲ ሰዓት ተሰጥቶት ሲከራከር ይታያል።
ከላይ የጠቀስኳቸው ነገሮች የምርጫው ትኩረት በሰላም መጠናቀቅ መቻሉ ላይ ብቻ እንድናተኩር ያደርጋል። ፍትሐዊና ነጻ ምርጫ ከስንት አመት በኋላ እንቀዳጃቸው ይሆን የሚል ጥያቄም ያስነሳል።
ቸር እንሰንብት!
Filed in: Amharic