>

አገር እናድን ማለት አብይን እናድን ማለት ነውን ?..... (ታጠቅ መ.ዙርጋ)

አገር እናድን ማለት አብይ እናድን ማለት ነውን ?  አገር  እናድን ማለት  የብልጽግና ሥልጣን እናድን ፣እናጠናክር ማለት ነውን ? 

ታጠቅ መ.ዙርጋ


እነዚህ ጥያቄዎች በበርካታ ኢትዮጵያውያን እንደተጠየቁ ወይም እንድተነሱ ብገምትም ፣ ከሌላ ሰው አእምሮ የተተነፈሰ ሃሳብ ፣ ከእኔ አእምሮ እንድተተነፈስ ስለማይሆኝልኝ ፤ በዚህ ጉዳይ በቁንጽሉም ቢሆን አእምሮዬን ማስተንፈስ  እፈልጋለሁ  ።  

ኢትዮጵያ ለአንድ ምዕተ ዓመት (መቶ ዓመታት) የመግዛት  እቅዳቸውና ምኞታቸው  ቢከሸፍባቸውም  መልሰው ለማንሰራራት ከአገር ውጭኛና  ከውስጥ የሚፍጨረጨሩትን የትህነግ  አሸባሪዎች፣ የኦነግ አሸባሪዮች ፣ የቅርብ  ታሪካዊ  ጠላቶቻችን – በአሜሪካና  አጋሮቹ  እገዛና አይዟችሁ ባይነት ፣ አገራችን ኢትዮጵያ ለማፈራረስ የሚያደርጉትን ዘመቻ  ለመቃውም ፣ በባዕዳን አገራት ዋና ዋና  ከተማዎች በሚደ ረጉ  የስልፍ ጥሪዮችና ሰልፎች አብይና  አገር ፣ ብልፅግናና  አገር አለመለየት ይስተዋላል/ይንፀባረቃል ። 

ከሰዓት በፊት አገራችን እናድን የሚለው ቡድን በተሰለፈበት አደባባይ ከሰዓት በኋላ  ወይም በማግሥቱ በዛው አደባባይ ውይም በሌላ አደባባይ  አብይ ይውደም ! የሚል ቡድን’ ሲሰለፍ ይታያል ። የዚህ ዓይነት አካሄድ ምክንያታዊነት ግልጽ ስላልሆነልኝ የሚከተሉትን ነጥቦች ለማንሳት ተገደድኩ                   ፦

 

  • የአገራችን ነባራዊ ቀውሶችና በፀረ- ኢትዮጵያ መርህ የሚንቀሳቀሱትን ሃይሎች ሁሉ ምክንያቶች አብይ ነው ለማለት ነውን ?
  • በሉዓላዊነታችን የዘመቱብን ሃይሎች ሁሉ ሊዘምቱብን የቻሉት በአብይ ጠብ አጫሪነት ነውን?
  •  የአብይ መውድም ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ከተነሱብን ጠላቶቻን  ያድነናል ለማለት ነውን ?
  • የአገር ኅልውና  የሚያሰጉትን  ጠላቶች  መቃወምና እነሱን መታገል  መቅደም አለበት ወይስ እነዚህን ጠላቶች የአገሬም  የእኔም ጠላቶች ናቸው ብሎ የሚታገል ገዢ/መሪ  መቃወምና  ማውገዝ  መቅደም አለበት ?
  • በእንዲህ አገረ በውስጥና በውጭ ጠላቶች ህብረት በተከበበት ውቅት የተሻለና  አስተማማኝ አማራጭ ሳይዘጋጅ  በገዢያችን /መሪ ላይ ማመጽ አገራችንን ለቀውስ ለመዳረግ ከተነሱብን ጠላቶቻችኝ ጎን አያሰልፈንምን ?
  • በቅራኔ አሰላለፍስ – ማነው የመጀመርያ /ተቀዳሚ ጠላታችን? ማነው ሁለተኛ/መለስተኛ ጠላታችን ብሎ መጠየቅ አያስፈልገንምን? አሁን የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን ዋኝኛ /ቀንደኛ ጠላት ፦ {የአሸባሪዩ ትህነግ  ርዥራዦች ? የኦነግ አሽባሪዮች ? የጎረቤት ታሪካዊ ጠላቶቻችን ? ፤

 

የአሸባሪዩ  ትህነግ እንጥፍጣፊዮች   ከተበተኑበት አሰባስበው  የሀገረ ትግሬ መንግሥት እንዲመሰርቱ የሚጥሩ አሜሪካና  አጋሮቹ ? ይህ ካልተሳካ እዚህ ጋ የጠቀስኳቸውን ሁሉ አስባስበው በኢትዮጵያ ላይ ለመዝመት የተዘጋጁትን ሃይሎች }? ወይስ አብይ አህመድ ?

 

  • ከአብይ ጋር ያለንን  ቅራኔ የሁለተኛ ደረጃ/መለስተኛ ቅራኔ መሆን የለበትምን ? ከላይ የጠቀስኳቸው ሃይሎች የቃጡብንን አደጋ በጋራና በአንድነት ቆመን ካስወገድን /ድል ከመታን በኋላ ከአብይ ጋር ወደ አለን ቅራኔ ማለት የውስጥ ችግሮቻችንን መፍትሄ ወደ መፈለግ ትግል መዞር አይኖርብንም ? ይህ በዚህ እንዳለ  -በጠ/ሚኒስተር አብይ አገዛዝ  ምክንያት ለአንድነታችን ጠንቅ የሆኑ ነገሮች አስተካክል ማለት አይኖርብን  ማለት አይደለም ። 
  • አሜሪካና አጋሮቹ በእኛ ላይ እየመጡ መሆኑን እያየን ቶሎ ኑልን ! ጫና አድርጉብን ! አብይ አውድሙልን ! ችግራችን ፍቱልን ! ዓይነት መፈክርና ልመና  ምን ይባላል ?{አንዳንድ ሰልፈኞችና ፕሮፌሰር መረራ } እንዳደረጉት ።

 

 

  • ሁላችንም እንደምናውቀው  ወያኔ/ትህነግ ኢትዮጵያ  ለ 27 ዓመታት ሲገዛ  በኢትዮጵያውያን ላይ አስከፊ  ጭቆናና  ግፍ ፈጽሞዋል ።  በብሄርና በጎሳ ከፋፍሎ አንዱ በሌላው  ላይ አዝምቶ አፋጅቷል ፣  በብዙ ሺዮች የሚቆጠሩ አመሮች በብሄር ማንነታቸው  ጨፍጭፏል ፤ ብዙ ሺዮች  ከጋራ ሙለታ ፣ ከወተር ፣ ከጉራ ፈርዳ ፣ ከወልቃይት ፣ ከጉሙዝ ወዘተርፈ ከቄያቸው  አፈናቅሎዋል  ፣ {የፖለቲካዊ ፣  የሰብአዊ እና  የሃይማኖታዊ  መብቶች ታጋይ ፦ አክትቪስቶች ፣ ጋዜጠኞች ፣ ተማሪዮች ፣ ዲሞክራትና አገር ወዳድ ሃይሎችን -በስውርና በጠራራ ፀሃይ  ረሽኗል ፣ አስሮ ስቆቃ <torture> እና  ግብረ ሰዶም  አስፈጽሞባቸዋል  ወዘተርፈ ።  

 

እነዚያ ኢ-ሰብአዊና ኢ-ፍትህአዊ  ግፎች  በመቃወም  ለ 27 ዓመታት ፦ በአሜሪካ ፣ በአውሮፓ ፣ በካናዳ ፣በአውስትራሊያ ፣ በኒዩዘላንድ  ወዘተርፈ ዋና ዋና ከተማዎች ፣ፓርላማዎች ፣ኢምባሲዮች  ወዘተርፈ እንደ ቁራ ጩኽናል ፣ተጽኖ አድርጉ ብለን ተማጽነናል ። ወያኔ/ህወሃት በአፍሪካ ቀንድና በሃጉሩ  የእነሱ ተላላኪና ለነሱ ወታደሮች  የህይወት መሰዋትነት የሚያስከፍሉ ተልዕክዎች/ሚሽን ተርክቦ ይሰራላቸው  ስለነበረ ፤ ጆሮ ዳባ ብለውናል ፤ ተው  ሊሉት አልፈለጉም ። ይልቁንም የትህነግ መሪ የአፍሪክ ሞዴል/ናሙና መሪ ፣የትህነግ አገዛዝ የአፍሪካ ዲሞክራትና የድገት አገዛዝ  እያሉ ያሟክሹ/ያዳንቁ ነበረ ።

እንደ ‘ሳይልኩት ወዴት ፣ ሳይጠሩት አቤት’ አባባል ፣ ዛሬ ከተለያዩ አቅጣጫዎች  በጠላት እንድንወጠር  ፦ ያመቻቸው  ፣ የጀመሩና  ያስጀመሩ  አሸባሪዩ ህወሃት ተንኮታኮቶ  ከተበተነበት ሰብስበው ነፍስ ሊዘሩለት ለሚያደርጉት ሩጫ ፣አጋር ለማግኘት  -ምን እናድርግላችሁ ? በምን እንተባበራችሁ ? ምን እንታዘዛችሁን ? ወዘተርፈ ዓይነት አቅራረባቸው እንደጤናማ አድርጎ መቀበል ፤ የፖለቲክ ምልከታ ብቃታችን ይፈታተናል {አንዳንድ ሰልፈኞችና ፕሮፌሰር መረራ ዓይነት } ይመለከታል ። 

 

  • እ ኤ አ በ 7-06-2021  ከዚያና  ከዚህ በተሰኘ አምድ –  አዜብ በተባለች ጋዜጠኛ አስተናጋጅነት 

 

“ የአብይና የኢሳያስ ግንኙነት ትሩፋት ወይስ  መዘዝ” በተሰኘ አርእስት ላይ  ካወያየቻቸው  አራት ምሁራን  አንዱ   ‘ የውጭ ጉዳይ መስርያ ቤትም ሰርቼአለሁ ፣ የፖለቲክ ሳይንስም ተምሬያለሁ ፣ የውጭ ችግር የሚከሰተው  የውስጥ ችግር ሲኖር ነው ፣ ከውጭ የሚመጡብን ችግሮች ለማስቆም መጀመርያ አብይ አስወግደን የውስጥ ችግራችንን መፍታት ነው’ የሚል አስተያየት ሰነዝሯል ። 

በርግጥ  አንድ አገር/ብሄር ከውስጥ ሲዳከም ፦ (1)  ለውጭ ጠላትና  ለውስጥ ተገንጣይ ሃይሎች ይጋለጣል (2) አምባገ ነን ገዢዮች በውስጥ  ከስነ-አስተዳደር ጉድለት  ከሰፊው ሕዝብ ጋር በቅራኔ/ዎች ሲወጠሩ  ያንን ውጥረት ለመቀልበስ በሌላ አገር ላይ  በተለይም  በጎረቤት አገር ላይ ጠብ በመጫር ጦርነት ይጋብዛሉ ። ታዲያ አሁን ከውስጥና ከውጭ የተነሱብን ፀረ-ኢትዮጵያ ሃይሎች ጠብ ፣በአብይ ጠብ አጫሪነትና ከአብይ አስተዳደር ድክመት የመነጩ ናቸው ብሎ ለመከራከር አይክብድምን ? ለአንድ ምዕተ ዓመት እኛ ካልገዛናችሁ ሉዓላዊ ኢትዮጵያ የሚባል ነገር የለም ፣ አባይ ወንዝ ገድቦ የመጠቀም መብት የላችሁም ፣ መገንጠል አለብን ፣ የወልቃይት መሬት ወደ ትግሬ መመለስ አለበት ፣ የአማራ ሚሊሽያ ከትግራይ መወጣት አለበት ፣ ከምትና ከሞት  የተረፉትን ህወሃቶች መልሰው ይደራጁ ወዘተርፈ       ምክንያቶች – ከላይ በጠቀስኩት አርእስት ከተወያዩት ምሁራን አንደኛው  ሰንዝሮታል ካልኩት አስተያየትና እኔም (1-2) ቁጥር ካስጨበጥኳቸው ይሁንታዎች ጋር ይዛመዳሉን ? የአበባና  የሳር ልዩነት በያንዳንዳችን እይታ ይተርጎማል/ይዳኛል ።

ችግሩ ከጠ/ሚኒስተር  አብይ ነው  ቢባል እንኳን ፣ አጼ ምኒሊክ በአደዋ ፣አጼ ሃይለሥላሴ በማይጨው ቀጥሎም በሌሎች ከተሞቻችንና ገጠሮቻችን የጣሊያን ወረራ ለመመከት ሆይ ብሎ የተሰለፈው የኢትዮጵያ  ሕዝብ በመሪዮቹ  ምንም ዓይነት ቅራኔ አልነበረውም  ማለት አይቻልም ። የእኔም አባት የሁለተኛው የጣሊያን ወረራ ከተጋፈጡት አርበኞች አንዱ ነበር ፣ስለሆነም በኩራት አስታውሰዋለሁ ፣በኩራት ስሙን አንሳለሁ  (መንጂ ዙርጋ ይባል ነበር) ። 

የመልዕክቴ መርህ – አገር እናድን ማለት አብይ እናድን ማለት አይደለም  ፣ አገር  እናድን ማለት የብልጽግና ሥልጣን እናድን ፤ እናጠናክር ማለት ስላልሆነ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ላይ የተቃጣብንን ጥቃት በአንድነት ቆመን  እንመክት የሚል ነው ። 

እኔ አፍቅሮተ አብይ አይደለሁም ፤ ፍጹም አፍቅሮተ ኢትዮጵያና ኢትትዮጵያውን ነኝ ። ይህንን የጻፍኩት በማንም ተጽኖ  ባልታቀቡ ነጻ ኅሊናዬና ነጻ አእምሮዬ  ግድ ስላሉኝ ነው ።

Filed in: Amharic