እውነትም ቤተ ክርስቲያን ስደት ላይ ናት…!!!
በዲ/ን አባይነህ ካሴ
የቅዱስ ሲኖዶስን ውሣኔ ተከትሎ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጠንካራ ደብዳቤ ለስድስት መንግሥታዊ አካላት በአድራሻ ለሌሎች ደግሞ በግልባጭ ጽፏል። ደብዳቤው ከጠቀሳቸው ጉዳዮች አንደኛው የመስቀል ዐደባባይን ባለቤትነት እና ክብር ይመለከታል።
የቤተ ክርስቲያንን ተቃራኒ ማድረግ ይኹነኝ ብሎ የተያያዘው የዐዲስ አበባ አስተዳደር ደግሞ በዓለ ዕርገትን ለማክበር የተጠራውን የመስቀል ዐደባባይ ጉባኤ “ሕገ ወጥ” በማለት በፖሊስ ኮሚሽኑ በኩል መግለጫ አውጥቷል።
፩ኛ. ራሱ ኮሚሽኑ ሲነጋገር የሰነበተው ከሕገ ወጥ አካል ነበርን? ከአንዴም ኹለት ሦስት ጊዜ ከዚያም በላይ በቢሮው እየጋበዘ ሲለው በማስፈራራት ሲለው በመለማመጥ ሲያነጋግራቸው የነበሩትን አመራሮች ድንገት ተገልብጦ በዚህ ስም መጥራቱ ሊያሳፍረው ይገባል። ይህ የሰላምና የጸጥታ ቢሮውንም ይመለከታል።
፪ኛ. የሰላምና ጸጥታው ኃላፊ አቶ ባዩ ከአመራሩ ጋር የግል ጠብ ያላቸው ይመስል እንተያያለን እያሉ ሲዝቱ ሰንብተዋል። ሌሎች የእምነት ተከታዮች በዐደባባያችን ላይ ያሰቡትን ለመፈጸም ላቀረቡት ጥያቄ ጠብ እርግፍ ብለው ሲታዘዙ እንዳልሰነበቱ በደረቁ ኾነብኝ ብለው ይመስላል አምርረው ለቤተ ክርስቲያን ያላቸውን ጥላቻ ለመግለጥ ያልፈነቀሉት የለም።
ከእኒህ ግለሰብ ጋር የማኅበራት ኅብረቱ አመራሮች የሔዱባቸውን ልጥቀስ ፡ –
– [ ] መጀመሪያ ጉባኤውን ዐውቀው ተገቢውን ተቋማዊ ድጋፍ እንዲሰጡ ተጠየቁ፣
– [ ] የግንቦት ፲፯ቱ የቅዱስ ሲኖዶስ መክፈቻ መርሐ ግብር ያን ሁሉ ዛቻ እና ማስፈራሪያቸውን አልፈው ለቤተ ክርስቲያናቸው በጥብዐት መቆማቸው በጣም ስላበሳጫቸው በከፍተኛ የቂም በቀል መንፈስ ይኽኛው ጉባኤ እንዲጨናገፍ ያለመታከት ተንቀሳቀሱ፣
– [ ] መጀመሪያ ፈቃድ ስለሌላችሁ አይካሔድም ብለው የፈረጠመ አቋም አሳዩ። በእርሳቸው ካለው በላይ አመራሮቹ ቆፍጠን ማለታቸውን ሲያዩ ሰላም ሚንስቴር ይፍቀድላችሁ እንጅ ችግር የለም አሉ።
– [ ] ይኽንን የሰሙት አመራሮች ለሰላም ሚንስቴር ማመልከቻ አቀረቡ። ሰላም ሚንስቴርም በመስቀል ዐደባባይ ተብሎ የተጠየቀውን ቀድሞ ለሌሎች ስብሰባዎች በተዘጋጀ የደብዳቤ ቅጽ ላይ መስቀል ዐደባባይ ሳይል አዳራሽ ብሎ በመጻፍ ሊከበሩ የሚገባቸውን ነጥቦች ጠቅሶ በጉባኤው መካሔድ መስማማቱን ገልጾ ጻፈ።
– [ ] ይህንን ይዘው ይኸው ስምምነቱን ገልጧል ሲሉ አቶ ባዩ የለም አዳራሽ እንጅ መስቀል ዐደባባይ አልተባለም አሉ። መስቀል ሸደባባይ ተብሎ ከተጠቀሰ እንተባበራለን በማለት በድጋሚ አረጋገጡ።
– [ ] በስምምነት መቀጠሉን አብዝተው የሚሹት አመራሮች እንደገና የሰላም ሚንስቴር መስቀል ዐደባባይን ጠቅሶ እንዲጽፍ ጠየቁ። እርሱም ተስማምቶ ጻፈ።
– [ ] ይኽንን ይዘው ሲቀርቡ ሰውዬው ምርጫው ይለፍና ታደርጋላችሁ ወደሚል ሌላ ሜዳ ሽምጥ ጋለቡ።
የሰውዬውን ውኃ ቅዳ ውኃ መልስ በትዕግስት ያስተናገደው አመራር እንዳለፈው ሁሉ ሳይግባባ ከእርሳቸው ተለየ። ይኽን ያኽል ከአንዱ የመንግሥት ቢሮ ወደ ሌላው እየተመላለሰ የደከመን አካል ድንገት የዳቦ ስም መስጠት ሊበሏት ያሰቧትን ነው።
፫ኛ. ከሰላም ሚንስቴር ጋር ፕሮቶኮል በጠበቀ ደረጃ ደብዳቤ ሲመላለስ የነበረን አካል ደርሶ ሕገ ወጥ ማለት አደገኛ ፍረጃን ያሳያል።
፬ኛ. በራሱ ቤት ጉባኤ ላድርግ ያለን አካል በቤቱ ገብቶ አትችልም ማለትን ምን አመጣው? በዚህ ኹኔታ ሕገ ወጡስ ማን ነው?
መስቀል ዐደባባያችንን ዐይናችን እያየ ስትነጥቁን ቆመን አንመለከታችሁም። በቃችሁ!!!
ጉባኤው ይካሔዳል። መልኩና ቅርጹ በተፈለገው መጠን ላይኾን ቢችልም የእግዚአብሔርን ጉባኤ ልትከለክሉ ሥልጣን የላችሁም። ማስፈራሪያችሁ ብርታታችን እንጅ ፍርሃታችን አይደለም። ያረጋገጣችሁልን ቢኖር ቤተ ክርስቲያን ስደት ላይ መኾኗን ነው። አሳዳጆችም እናንተ።
ቤተ ክርስቲያን በጻፈችው ደብዳቤም መጠቃቷ የተደራጀ መዋቅራዊና መንግሥታዊ መልክ አለው ብላለች። እናንተ ጥይቶቻችሁን እኛ እግዚአብሔርን አምነን እንወጣለን። አንገት ማስደፋታችሁ ከበቂ በላይ አንገሽግሾናል።
– [ ] የሁሉም ሰው ሞባይሎች ቪድዮ በመቅረጽ ይሥሩ
– [ ] ማንም ኃይል የተላበሰ እንቅስቃሴ ከማድረግ ይታቀብ
– [ ] መንገዳችን በዝማሬ ብቻ ይኹን