>

ለዚህ ብሔራዊ ውርደት ተጠያቂው ማነው!?! (ያሬድ ሀይለማርያም)

ለዚህ ብሔራዊ ውርደት ማነው ተጠያቂው? 1408 ሴቶች በላይ በትግራይ በአሰቃቂ ሁኔታ ተደፍረዋል…!!!
ያሬድ ሀይለማርያም

በትግራይ የተካሄደውን ጦርነት ተከትሎ ክ1400 በላይ የሚጠጉ ሴቶች በአሰቃቂ ሁኔታ የመደፈር ጥቃት የደረሰባቸው መሆኑን፣ ብዙዎቹ በደቦ የተደፈሩ መሆኑን፣ የተወሰኑት ከመደፈርም አልፎ በአሲድ የመቃጠል፣ የመደብደብ እና ከፍተኛ የአካል ጉዳይ የደረሰባቸው ስለመሆኑ እና ይሄም በህክምና ጭምር መረጋገጡ ቪኦኤ የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር እና ሆስፒታሎችን በማነጋገር ዘግቧል።
የሚያሳዝነው ጥቃቱ አሁንም ድረስ አለመቆሙ ነው። በዚህ አስነዋሪ የወንጀል ተግባር የተሳተፉት በዋነኝነት የኤርትራ ጦር፤ እንዲሁም አንዳንድ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት እና የአማራ ልዩ ኃይል አባልት መሆናቸውም በዘገባው ተደጋግሞ ተገልጿል። ለዚህ አሰቃቂ እና ወደር ለማይገኝለት የነውር ተግባር፣ የወንጀል አድራጎት እና ብሔራዊ ውርደትን ሊያስከትል ለሚችል አድራጎት ድርጊቱን በቀጥታ የፈጸሙት ወታደሮች ብቻ ሳይሆኑ አገሪቷን ለዚህ አይነት ውርደት የዳረጓት፣ ዜጎችን ለዚህ አይነት ስቃይ የዳረጉት እና ለዜጎች ጥበቃ ማድረግ ያልቻሉት አካላትም እኩል ተጠያቂዎች ናቸው። በትግራይ ላይ ከሰሜን ዕዝ፣ ከማይካድራ እስከ አክሱም በንጹሃን ዜጎች ላይ ለደረሰው ሰቆቃ፤ በተለይም በእነዚህ ሴቶች ላይ ለተፈጸመው አሰቃቂ የጽኦታ ጥቃት፤ የወያኔ ሹማምንት፣ የአብይ አስተዳደር እና የኤርትራ መንግስት ቀጥተኛ ተጠያቂዎች ናቸው። ፍትህ ቀን ሲወጣላት እነዚህ አካላት ሁሉ ተጣምረው በሕግ ሊጠየቁ ይገባል።
እናንት የሴቶች ጥቃት የሚያንገበግባችሁ እና እናንት የመብት ተሟጋች ድርጅቶች  በዚህ ጉዳይ ላይ ድምጻችሁን ካላሰማችሁ መኖራችሁ ለምን ይሆን? እናንት የባለሥልጣናት ቪዛ ተከለከለ ብላችሁ ‘አገራችንን እንደ መድፈር ይቆጠራ’ በማለት ትንታኔ ስትሰጡ የነበራችሁ ጋዜጠኞች፣ ምሁራን እና ፖለቲከኞች ከወዴት አላችሁ? በአደባባይ ምዕራባዊያንን ልታብጠለጥሉ እና በዲፕሎማሲውም ልትፋለሙ አደባባይ የወጣችሁ አገር ወዳድ ወገኖች ይህን የቤታችንን ጉድ ስትሰሙ ምን ተሰማችሁ? አገር መውደድ ማለት፣ የአገር ክብር መደፈር ማለት ለእናንተ ትርጉሙ ምን ይሆን? ቪዛ መከልከል አይደለም ፍርድ ቤት ቆመው በሕግ መጠየቅ የሚገባቸውን ሹሞች ገበና በጩኸት እና በሰልፍ ማስቀረት ይቻላል ወይ?
ለምዕራባዊያኑ የተንኮል ፖለቲካስ አጋልጠው የሰጡን፣ የአለም ሚዲያዎች መጠቋቆሚያ ያደረጉን፣ በአለም አደባባይ ኢትዮጵያ እንድትዋረድ ያደረጉት፣ የሰከነ ፖለቲካ መሥራት አቅቷቸው በእነሱ ክሽፈት አገሪቱን ወደ ጦርነት የዶሉ እና ለብዙ ዜጎች እልቂት ምክንያት የሆኑ እነዚህ ቪዛ የተከለከሉት ሹማምንቶች አይደሉም ወይ? በአገር ሉዓላዊነት ስም የሹማምንቶቹን ገበና እና ክሽፈት ለመሸፈን ከምንጥር ኢትዮጵያ ውስጥ ሞልቶ የሚፈሰውን የግፍ ጽዋ ብናነጥፍ ኢትዮጵያም ትከበራለች፣ ሉዓላዊነቷንም መዳፈር ለሚመኙ የማትመች ታላቅ እና ኩሩ አገር ትሆናለች።
ከ4 ዓመት ህጻን እስከ 80 ዓመት አሮጊት በወታደሮች ሊያውም በደቦ የሚደፈሩበት፣ በመቶዎች በአንድ ሌሊት ታርደው የሚያድሩበት (ማይካድራ)፣ ወታደሮች አገር አማን ነው ብለው በተኙበት የሚፈጁበት-ሰሜን እዝ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች በማንነታቸው እየታደኑ ከቀያቸው የሚፈናቀሉበት አገር እና አስነዋሪ ገበና ይዘን ከምዕራቡ አለም ጋር ግብግብ መፍጠር ብዙ እርቀት አያስኬደንም። መጀመሪያ ቤታችንን፣ ገበናችንን እናጽዳ። ሞልቶ እየፈሰሰ ያለውን ግፍ እናንጥፍ። ኢትዮጵያ የግፈኞች አገር መሆኗን እንዲያከትም እንታገል። ተጠያቂነትን እናስፍን።
ይህን የቬኦኤን ሪፖርት አድምጣችሁ ፍረዱ። እኔ የተሰማኝ ካልተሰማችሁ እኔጋ ችግር አለ ማለት ነው።
Filed in: Amharic