አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫ
በአገራችን የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ላይ የቀጠለው የኢሰመጉ ውትወታ!
ሰኔ 3 ቀን 2013 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ፡- ኢሰመጉ ከተቋቋመበት በ1984 ዓ.ም ጀምሮ ላለፉት 29 ዓመታት ከማንኛውም የፖለቲካ ቡድን፣ ሃይማኖት፣ ብሔር እና ጎሳ ተፅዕኖ ነፃ በመሆን ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መጎልበት፣ ለሕግ የበላይነት
መስፈንና ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ሲታገል ቆይቷል፡፡ በዚህም የአገራችንን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ በየጊዜው በመከታተልና ምርመራ በማድረግ ለሕዝብና ለሚመለከታቸው አካላት ሪፖርትና ምክረ-ኃሳብ ያቀርባል፡፡
በየጊዜው ከሚሰራቸው የሰብአዊ መብቶቸ ሁኔታ ክትትሎች የሚያገኛቸውን መረጃዎች መነሻ በማድረግ በአገራችን የሰብአዊ
መብቶች ሁኔታ አሁንም አደጋ እንደተጋረጠበት ለመረዳት ችሏል፡፡
1. በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደህንነትና ነፃነት እንዲሁም የንብረት መብቶች ሁኔታን በተመለከተ
ኦሮሚያ ክልል
በዳምቢ ዶሎ ከተማ በቀን 3/9/2013ዓ.ም በኦሮሚያ ልዩ ኃይል በአደባባይ የተገደለዉ የወጣት አማኑኤል ወንድሙ
ቤተሰቦችና ዘመዶች በ4/9/2013ዓ.ም ሀዘን ከተቀመጡበት ተይዘዉ እየተደበደቡ በደምቢዶሎ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ ተወስደዉ እንደታሠሩ፣ በተመሳሳይ የኦሮሚያ ልዩ ኃይሎች፤ በምዕራብ ወለጋ ዞን በቦጂ ድርመጂ ወረዳ በቀን
08/9/2013ዓ.ም ገመቺስ መላኩ የሚባል ግለሰብን ከቤቱ በማስወጣት በጥይት ገድለዉ ጫካ ዉስጥ እንደጣሉትና ቤተሰቦቹ ላይ እንግልት እንደፈፀሙ፣ እንዲሁም በሆሮ ጉዱሩ ዞን በአባይ ጮመን ወረዳ በፊንጫዓ ፖሊስ ጣብያ ሰዎች
ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ለብዙ ቀናት እንደሚታሰሩ ለኢሰመጉ የደረሱ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
ትግራይ ክልል
በትግራይ ክልል በንፁኃን ሰዎችና በተለያዩ አካባቢዎች በጊዜያዊ አስተዳደሩ ተመድበው የሚሰሩ ኃላፊዎች ላይ አሁንም
ግድያ እየተፈፀመ እንደሆነ፣ በመቀሌ ከተማ በሚፈፀም ዝርፊያ ነዋሪው ንብረቱን እያጣና በከፍተኛ ሥጋት ውስጥ እንዳለ እንዲሁም ባለው የፀጥታ ስጋት እንደልብ ለመንቀሳቀስ አስቸጋሪ መሆኑንና በአጠቃላይ በትግራይ ክልል ሕዝቡ
የተረጋጋና ሰላማዊ ኑሮ ለመኖር መቸገሩን ኢሰመጉ ከሚያደርገው ክትትል ለመገንዘብ ችሏል፡፡
ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል
ከየካቲት 12/2013ዓ.ም ጀምሮ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ቤንች ሸኮ ዞን ጉራፈርዳ ወረዳ ታጣቂዎች በሚፈፅሙት ጥቃት…
በኩኪ ሰፈራ በቀን 14/09/2013ዓ.ም አራት ሰዎች፣ በቀን 16/09/2013ዓ.ም ሁለት ሰዎች፣ በቀን 21/09/2013ዓ.ም DMT ኢንቨስትመንት ሁለት ሰራተኞች መገደላቸውን እና የግሩም ኢንቨሰትመንት ስራ አስኪያጅ
የሆኑት አቶ ተክላይ ገብረማሪያም 23/09/13ዓ.ም ተገድለው እስከ 26/09/2013ዓ.ም ድረስ አስክሬናቸው እንዳልተነሳ እንዲሁም በገሊት ሰፈራ ገልማ እና ሙልሙል ቀበሌ አስራ ስድስት ሰዎች እንደተገደሉ ኢሰመጉ ባደረገው ከትትል
መረጃ ደርሶታል፡፡
አማራ ክልል
ጎንደርና አካባቢው ባለው ከፍተኛ የሆነ የፀጥታ ስጋት የሰብአዊ መብቶች አሳሳቢ ደረጃ ላይ ያሉበት አካባቢ መሆኑን ኢሰመጉ ባደረገው ክትትል ለመረዳት ችሏል፡፡ በዚህም በ15/09/2013ዓ.ም ከምሽቱ 4፡00 ስዓት በተለምዶ አብሮ አደግ
ተብሎ በሚጠራው አካባቢ አጋቾች የሄርፋዚ ሪዞርት ሰርቪስን በማስቆም ሹፌሩንና አስተናጋጅ አግተው ከወሰዷቸው በኋላ ገንዘብ ተዋጥቶ ለአጋቾች ከተከፈለ በኋላ እንደተለቀቁ፣ አንድ የባጃጅ ሹፌር ለማገት ፈልገው ለማምለጥ ሙከራ ሲያደርግ በጥይት ተኩሰው እንደገደሉት እንዲሁም አብሮት ባጃጅ ውስጥ የነበረን አንድ ተሳፋሪ አግተው
መውሰዳቸውን፣ በአጠቃላይ ይህ አይነቱ ድርጊት በከፍተኛ ሁኔታ እየተፈፀመና የተለመደ እየሆነ መምጣቱን፣ በከተማው ከምሽቱ 2፡00 በኋላ እንደልብ መንቀሳቀስ እንደማይቻል፣ በተመሳሳይ በቀን 18/9/2013ዓ.ም በጎንደርና አካባቢው፤ በተለይ ቁስቋምና ቀበሌ 16 አካባቢ በነበረው የፀጥታ መደፍረስ በርካታ ንፁኃን ሰዎች መገደላቸውን እና ቤቶች መቃጠላቸውን ለኢሰመጉ የደረሱ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል
በመተከል ዞን አሁንም ንጹሃን ሰዎች እንደሚገደሉ፣ እንደሚፈናቀሉ እና ንብረታቸዉ እንደሚዘረፍ ኢሰመጉ ካደረገው ክትትል ተረድቷል፡፡ በዚህም በ26/09/2013ዓ.ም በፓዊ ወረዳ መንደር 49 ተብሎ በሚጠራዉ አካባቢ ታጣቂዎች በንፁሃን ነዋሪዎቹ ላይ ተኩስ በመክፈት ከመቶ በላይ የእርሻ በሬዎቻቸዉን ዘርፈዉ መዉሰዳቸዉን፣ በዞኑ ቡለን ወረዳ ጎንጓ ቀበሌ ታጣቂዎች ሁለት የቀበሌዉ ነዋሪዎችን አግተዉ መውሰዳቸውን፣ በ21/09/2013ዓ.ም በድባጤ ወረዳ
ፓርዘይት ቀበሌ የ13 ዓመት ህፃን ከብት እየጠበቀ በነበረበት ወቅት በታጣቂዎች ከተገደለ በኋላ ይጠብቃቸዉ የነበሩ ከብቶችን መውሰዳቸዉን እና በእዛዉ ዕለት እንድ ሰው በጥይት ተደብድቦ በከፍተኛ ሁኔታ እንደቆሰለ እንዲሁም
በ19/9/2013ዓ.ም በፓዌ ወረዳ መንደር 2 ተብሎ በሚጠራዉ አካባቢ ከብት ሲጠብቅ የነበረን ግለሰብ ታጣቂ ሃይሎቹ
በቀስት ክፉኛ አንዳቆሰሉት በክትትሉ የተገኙ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
2. የመዘዋወር ነፃነትና የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ሁኔታን በተመለከተ ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል
ከየካቲት 12/2013ዓ.ም ጀምሮ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ቤንች ሸኮ ዞን ጉራፈርዳ ወረዳ ታጣቂዎች
በሚፈፅሙት ጥቃት ምክንያት በአሮ ገብራን ክላስተር ስር ከሚገኙ ሱቂ፣ ገሊቃ እና ኮጀንታ ከተባሉ ቀበሌዎች ሕዝቡ
ሙሉ ለሙሉ መፈናቀሉን፣ ገሊቃ እና ኮጀንታ ከተባሉ ቀበሌዎች እንደሁም ከሚታ፣ ኩኪ፣ ጋሊቃ እና ተመርታ በተባሉ የሰፈራ ጣቢያዎች ሰፈረው የነበሩ ሙሉ በሙሉ እንደተፈናቀሉ፣ በከነዓን፣ ነባሩ ኩኪ እና ዲቢታ ሰፈራዎች ላይ ይኖሩ ከነበሩት አብዛኞቹ እንደተፈናቀሉ፣ በገሊካ እና አጋንታ ቀበሌዎች ላይ በ1977 ዓ.ም ሰፍረው የነበሩ አርሶ አደሮች ሙሉ
በሙሉ ከአካባቢው እንደተፈናቀሉና ለመሰረታዊ ፍላጎት አቅርቦት ችግር እንደተጋለጡ ኢሰመጉ ባደረገው ክትትል
መረጃ አግኝቷል፡፡