>

ኢትዮጵያ ታላቅ ልጇን አጣች! (አቻምየለህ ታምሩ)

ኢትዮጵያ ታላቅ ልጇን አጣች!

አቻምየለህ ታምሩ

ኢትዮጵያ ዛሬ ቅርሷ፤ የጥንታቂ ቋንቋዋ ሊቅ፤ የጽሑፎቿ ሰብሳቢ፣ ጥልቅ ተመራማሪና የእውቀቶቿ ተርጓሚ፤ በሴሜቲክ ጥናት ዘርፍም በዓለም ላይ ወደር የማይገኝለት ጠቢቧን፤ በርካታ መጽሐፍትንና በመቶዎች የሚቆጠሩ የታሪክ፣ የቋንቋና የሥነ ጽሑፍ  ምርምሮችን ያሳተመ የስነ ጽሑፍና የታሪክ ተመራማሪ፤ የአገር ተቆርቋሪ፣ የፍትሕ፣ የነፃነትና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የሆነውን ታላቁን  ልጇን ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌን አጥታለች።
ፕሮፈሰር ጌታቸው ኃይሌ በሕይዎት ዘመኔ ካገኘኋቸው፣ እድሜ ዘመናቸውን ካካበቱት እውቀታቸው ትንሽም ቢሆን የተማርሁባቸው፣ ሥርዓት በተላበሰ ሥነ ዘዴ የሞገትኋቸውና የተጣራ የታሪክ ማስረጃ ሲቀርብላቸውም [አንዱን ይህን በመጫን ይመለከቷል https://www.facebook.com/achamyeleh.tamiru.3/posts/3357343314287594] ለዘመናት ደክመው የጻፉትን መጽሐፍ ሳይቀር ለማረም ዝግጁ  እንደሆኑ ካየኋቸው ታላላላቅ የአገራችን ምሑራን መካክል በአንደኛ ደረጃ የማስቀምጣቸው ታላቅ ሰው ነበሩ።  እኔና ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ በተለያየ ካካሄድናቸውና ተቀድተው ለሕዝብ ይፋ እንዲሆን ከፈቀዷቸው ውይይቶቻችን መካከል የተሰወኑትን ወደፊት እዚህ ለመለጠፍ እሞክራለሁ።
ከፕሮፈሰር ጌታቸው ጋር ለመጨረሻ ጊዜ ያወራሁት መታመማቸው ሰምቼ ለመጠየቅ ከወራት በፊት በደወልሁበት ወቅት ነበር። በዚህ ከወራት በፊት በነበረን የስልክ ውይይት [ከታች ተያይዟል] ብዙም ጤና እንደሌላቸው፣ መተንፈስ እንደተቸገሩና አንድ ቀን የእስትንፋሳቸው መጨረሻ እንደሚሆን በሚያሳዝን ድምጽት ነግረውኝ ነበር። በዚህ አባባላቸው ምንም  ልቤ ቢሰበርም ላበረታቸው ስለፈለግሁ ገና ከሳቸው ብዙ እንደምንጠብቅና እንደሚሻላቸው ተስፋዬን ገልጨላቸው ነበር።
ከዚህ ውይይታችን በኋላ ላገኛቸውና ስለ ጤናቸው ደግሜ ልጠይቃቸው በተደጋጋሚ ወደ እጅ ስልካቸው ብደውልም ስልካቸው አይነሳም። ይህ ከፕሮፌሰር ጌታቸው ጋር የነበረኝ የስልክ ቆይታ የመጨረሻው ይሆናል ብዬ አላሰብሁም ነበር። ሆኖም ግን  በሰው ላይ ሞትን የሚያህል እዳ አለና የኔታ የነገሩኝንና ያሰቡትን ሁሉ ለመፈጸም ሳይችሉ አንድ ቀን የእስትንፋሴ መጨረሻ ይሆናል ያሉት ቀን ደረሰ። እጅግ ያሳዝናል።
ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ስለሰጡን ሁሉ እናመሰግንዎታለን! በሰላም ይረፉ! እግዚአብሔር ነፍስዎን በአጸደ ገነት ያኑራት። ለቤተሰባቸው በሙሉ ጽናትንና ብርታትን ፈጣሪ ይሰጣቸው ዘንድ ከልብ እመኛለሁ።
Filed in: Amharic