>

ብልጽግና ኢህአዴጋዊ መሰረቱን አልለቀቀም ፤ አይለቅምም...!!! (አበበ ገላው)

ብልጽግና ኢህአዴጋዊ መሰረቱን አልለቀቀም ፤ አይለቅምም…!!!

አበበ ገላው

ዛሬም የጥላቻና የሴራ ፖለቲካ ከውጭም ከውስጥም ህዝቡን ግራ አጋብቶታል!!!
ህወሃቶች ያባከኑት እድል ተዘርዝሮ አያልቅም። አንዱና ትልቁ ስህተታቸው በኢትዮጵያ አስተማማኝና ዘላቂ እርቅ፣ ሰላምና አንድነትን ለማስፈን ፈጽሞ አለመፈለጋቸው ነበር። እነ መለስ ዜናዊ ህዝብን በመሳሪያ ሃይል አንበርክከው እንደፈለጋቸው በዘር ከፋፍለው እየገደሉ፣ እያሰቃዩ፣ እየመዘበሩና በገፍ እያሰሩ የስልጣን ዘመናቸውን ማራዘም የሚችሉ መስሏቸው ነበር። አልተሳካም!
ዛሬም ታሪክ እራሷን እየደገመች ይመስላል። አገሪቷ በዘር በተቧደኑ ልሂቃንና ጽንፈኞች ተወጥራ በተያዘችበት በዚህ ፈታኝ ጊዜ ለዘላቂ ሰላም፣ እርቅ ብሄራዊ መግባባትና አንድነት ፈጽሞ ትኩረት አልተሰጠውም። አሁንም ሃይል ብቻውን የችግር መፍቻ ተደርጎ እየተወሰደ ነው። የጥላቻና የሴራ ፖለቲካ ከውጭም ከውስጥም ህዝቡን ግራ አጋብቶታል።
ለውጡ ብዙም እርቆ አልሄደም። ብልጽግናም ያው ኢህአዴጋዊ መሰረቱን አለቀቀም። ዛሬም አገሪቷን ከላይ እስከታች የሚመሩት ህዝብ ሲያስለቅሱ የነበሩ ኢህአዴጋውያን ናቸው። ስማቸው ቢቀየርም አስተሳሰባቸውና ምግባራቸው አልተቀየረም። ህዝቡ ዛሬም በየቦታው ዘሩ እየትቆጠረ ይታረዳል፣ ይፈናቀላል፣ ለችግርና መከራ ይዳረጋል። የተረፈውና በየሜዳው የወደቀው ምስኪን የሚደርስለት አጥቷል። የተረፈውም ከዛሬ ነገ ከእነ ቤተሰቤ እፈጃለሁ በሚል ስጋት በአገሩ ላይ ተሸማቆ በስጋት የመጨረሻዋን ሰአት እየጠበቀ ይኖራል።
ምንም እንኳ በህወሃት ላይ የተገኘው ድል ታሪካዊ ሊባል የሚችል ቢሆንም ድሉ መባከኑ ግን አያወዛግብም። ጦርነቱ በሚቻል አቅም ሰላማዊውን ህዝብ እንዳይጎዳ ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ ቢኖርበትም ያ ሳይሆን ቀርቷል። ህዝቡ ከህወሃት ጭቆናና ምዝበራ በመገላገሉ እፎይ ሊል ሲገባው ለከፋ ችግርና መከራ ተጋልጣል። ይሄ ደግሞ ነገን የበለጠ ያጨልማል እንጂ ተስፋ አይፈነጥቅም።
አብይም ይሁን ሌሎቹ ባለስልጣናት ጊዚያቸውን ጠብቀው ከስልጣን መንበራቸው ይሰናበታሉ። ትልቁ ችግር እነርሱ ያልፈቱት የፖለከቲካ ችግር ነገ ህዝብ እንዲፋጅና እንዲተላለቅ ምክንያት ሊሆን አይገባውም። መሪዎች ይመጣሉ፣ መሪዎች ይሄዳሉ።
ህዝቡ ግን አብሮ መቀጠሉ አይቀሬ ነው። ዛሬ ያልተፈታው ቅራኔ ነገ ወደ እርስ በርስ ጦርነት እንዳያመራ ዛሬውኑ ሊሰራበት ይገባል። የገዢዎችንና የጽንፈኛ ልህቃንን እዳ ድሃው ህዝብ መክፈል አይገባውም።
Filed in: Amharic