>

እያደነቅን ስጋታችንንም እንገልጻለን!!! አቧራው፤  መሬት ላይ ያለ ግፍ፤ ሃሜቱም ሃቅ ነው...!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

እያደነቅን ስጋታችንንም እንገልጻለን!!!

አቧራው፤  መሬት ላይ ያለ ግፍ፤ ሃሜቱም ሃቅ ነው…!!!
ያሬድ ሀይለማርያም

ጠቅላዮ በአዲስ አበባ የሰሯቸውን እና እየሰሯቸው ያሉ ድንቅ ነገሮችን አደንቃለሁ። ለዚህ ስራቸው ሊመሰገኑ ይገባል። ከሰሯቸው ስራዎቹ አንዱ የሆነውን የእንጦጦ ፖርክን የመጎብኘት እድል ገጥሞኛል። የሚያስደምም ድንቅ ሥራ ነው።
ከትላንት መግለጫቸውም ሁለት ነገር መረዳት ይቻላል። አንደኛው አገር ለማልማት በዙ እቅድ እና ህልም እንዳላቸው ነው። ሁለተኛው ደግሞ ይህን ህልማቸውን እውን ለማድረግ አንባገነን እሰከመሆን የሚሄዱ መሆናቸውን ነው። አገሪቱ አሁን ያለችበትን ውጥንቅጥ እና አሳሳቢ ችግር፣ የተቃዋሚዎቻቸውን ቅሬታ እና በመንግስታቸው ላይ የሚሰነዘሩ ቅሬታዎችን ‘አቧራ’ በሚል ገልጸውታል። “ሃሜት አቧራ እንጂ አሻራ መሆን አይችልም። አቧራውን ንቀን አሻራ ማኖራችንን እንቀጥላለን” የምትለዋ ንግግራቸው አለቃቸው የነበሩትን መለስን አስታወሱኝ። ባጭሩ የመለስን የመታበይ ንግግር ነው የደገሙት። መለስ  ‘ውሾቹ ይጮኻሉ፤ ግመሎቹም ጉዟቸውን ይቀጥላሉ’ ነበር ያሉት?
ታቃዋሚዎቻቸውን ውሻ አድርገው እና ተቋውሟቸውንም እንደ ውሻ ጩኸት ቆጥረው እሳቸው ከጉዟቸው ምንም አይነት ምድራዊ ሃይል እንደማያስቆማቸው ሊያውም በፓርላማ ፎክረው ነበር። የመሰረት ድንጋይ ጥለው ያስጀመሩትን የህዳሴ ግድ መጨረሻ ለማየትና እሪባን ለመቁረጥ ግን አልታደሉም። ግመሎቹስ ዛሬ ወዴት አሉ? አብይም ያች በሽታ እየታየችበት ነው። አገሪቱ ውስጥ ያለውን ያፈጠጠ እና አሳሳቢ ችግር እንደ አቧራ መቁጠር መጥፎ መታበይ ነው። አቧራው እንዲሰክን የሚቀርቡ ምክርና ወቀሳዎችንም እንደ ሀሜት መቁጠር ሌላው አሳሳቢ የክሽፈት ምልክት ነው።
ሕዝብ እየተራበ ነው፣ የኑሮ ውድነት ሌላ የቀውስ ምንጭ ነው፣ ያልተረጋጋ ፖለቲካም የልማት ጸር ነው፣ ጦርነትም አውዳሚ ነው፣ የመብት ጥሰቶች መበራከት የአፈና ሥርዓት መሳለጫ ነው። እነዚህ ችግሮች አቧራ አይደሉም። በእነዚህ ጉዳዮች ዙሪያ የሚቀርብብዎት ወቀሳና ነቀፌታዎች ሃሜት አይደለም። ልማቱን ግፉበት፤ መታበይዎን አቁመው ለዲሞክራሲ፣ ለሕግ የበላይነት፣ ለሰብአዊ መብቶች እና ለፍትህ ቀናዕይ በመሆን እንደ ልማቱ አፋጣኝ መልስ ይስጡ። ካልሆነ ግን መካር እንደሌለው ንጉስ … ይሆናሉ።
Filed in: Amharic