>

የብሽሽቅና የጥላቻ ገመድ ጉተታ ፖለቲካችን ቢያበቃስ . . . ?!? (አሰፋ ሀይሉ)

የብሽሽቅና የጥላቻ ገመድ ጉተታ ፖለቲካችን ቢያበቃስ . . . ?!?

አሰፋ ሀይሉ
*… የጨነገፈ ምክር፣ የመከነ ተስፋ…! የሆነው ያሳዝናል! ይህ ክፉ ትውስታ ዓመቱን ቆጥሮ   ውል ባይለኝ እስኪ  አሁን.. ምን ነበረበት?
 
ዛሬ ታሪክ ተቀይሮ እያስተዋልነው የምንገኘው የህወኀቱ ቡድን “ምርጫ ላካሂድ!” – እና የማዕከሉ ቡድን “የለም አታካሂድም!” ንትርክ ቀላል ጉዳይ አይደለም! ትልቅ ታሪካዊ መፍትሄ የሚያሻው ታሪካዊ ጥያቄና መልስ ነው! ዲሞክራሲያዊ እሰጥ አገባዎችን በአፈና ሳይሆን በቅን ህዝባዊ መንገድ ለመፍታት አበክረን ማሰብ ያለብን ጊዜ ላይ ነን! ከመውደድና ከመጥላት ስሜት ውጪ በጥልቅ መታየት ያለባቸው መሠረታዊ ፍሬነገሮች እንዳሉ አለመርሳት አስተዋይነት ነው! ነግ በኔን ብናስብ፣ ከስሜት ስሌትን ብናስቀድም፣ አምባገነነትነትን ከተላበሰ ውሳኔ የሕዝብን ትክክለኛ ውሳኔ ለማክበርና ለማስከበር ዝንባሌ ብናሳድር – መልካም ይመስለኛል!
“እገሌና እገሌ ቦታ ቢለዋወጡስ ኖሮ ሀሳባችን ይቀየር ነበር ወይ?” ብለን መርሃችንን ደጋግመን መፈተሽ – የወደፊት ጎዳናን በፅኑ መሠረት ላይ ይገነባል! ዝንተ ዓለም ሳይለወጥ የሚቀጥል ነገር እንደሌለም መገንዘብ ከብዙ የስህተት ድምዳሜ ያድናል! በየትኛውም ፋሺስታዊ ኃይል የመነጨ ፍላጎት ቢሆን ለሕዝብ ፈቃድ ተገዢ ለመሆን የተደረገን ተነሳሽነት በደፈናው ማጣጣል፣ ወደ ትክክለኛ መስመር የሚደረግን ጉዞ ለማገዝ ፈቃደኛና ተባባሪ አለመሆን፣ ውሎ አድሮ ሀገራዊ መዘዙ እጅግ ከባድ ነው፡፡ በተነከርንበት የብሽሽቅና የጥላቻ ገመድ ጉተታ ፖለቲካችን የተነሣ መልካም ታሪካዊ ዕድሎችን ለሕዝባችን እንዳናመክንበት ታላቅ ሥጋት አለኝ! ያለመግባባት መፍትሄው ያለመግባባትን ገደል አስፍቶ መቆፈር አይደለም! ላለመግባባት መፍትሄው ደግሞ ደጋግሞ ወደ መተማመን የሚወስድ ውይይት ነው፡፡ ለመራራቅ መፍትሄው መቀራረብ ነው፡፡
እና ለሀገራችን “የድህነት ጌቶች”ም ለሀገራችን “የለውጥ አዋላጆች”ም በፈጣሪ ስም የማቀርበው ልመና፡- ለተደቀኑብን ችግሮች ማንአህሎኝነት መፍትሄ እንዳልሆነ ከቅርብ ታሪካችን ብንረዳ፣ ለሠላማዊ መፍትሄዎች ፈጽሞ ዕድልን ባንዘጋ! ይሄኛው መንገድ ተዘጋ? ሌሎችም እልፍ መንገዶች እንዳሉ ባንዘነጋ!
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!
Filed in: Amharic