>
5:13 pm - Thursday April 19, 4187

የፖሊስ እንስሳዊ የጭካኔ በትሩ በኦርቶዶክስ ላይ ይበረታል፣ (ቀሲስ ኤፍሬም እሸቴ)

እርስበርሷ የተለያየች …..!!!

(ቀሲስ ኤፍሬም እሸቴ)

* የፖለቲካ መጠቀሚያ እየሆንን ነው፤
* የግል ጥቅም ነጋዴዎችና የመከራ ሸቃጮች መጠቀሚያ እየሆንን ነው፤
* የፖሊስ እንስሳዊ የጭካኔ በትሩ በኦርቶዶክስ ላይ ይበረታል፣
* ይህንን ክፉ ጊዜ እንድናልፈው ምን ማድረግ ይገባናል፣ ጎበዝ?
———–
አጠቃላይ ዳራ:-
በመስቀል አደባባይ ሊደረግ የነበረ ጉባኤ በፖሊስ መታገዱን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ጉባኤውን ለማድረግ ፈቃድ ያወጣው የመንፈሳውያን ወጣቶችና ጎልማሶች ማኅበራት ሕብረት ሲሆን አስፈላጊውን ሕጋዊ መንገድ ተከትሎ በደብዳቤ ጭምር ፈቃዱ ተሰጥቶት ነበር። ከዚያም ረቡእ፣ ለሐሙሱ ዝግጅት ዋዜማ፣ ፖሊስ ጉባኤውን “ሕገ ወጥ” እና “ጸረ ሰላም ኃይሎች የጠሩት ነው” በማለት ዝግጅቱን አግዶታል።
በዚሁ ቀን ደግሞ በጠ/ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ በብፁዕ አቡነ ያሬድ በተጻፈ ደብዳቤ በጃንሜዳ ሌላ ዝግጅት ለሰኔ 6 መፈቀዱ ተገልጿል። የመስቀል አደባባዩ ምትክ ይሁን ወይም ማካካሻ ግልጽ አይደለም። አዘጋጁ የማ/ቅዱሳን የአዲስ አበባ ማዕከል ከሌሎች ማኅበራት ጋራ በመተባበር መሆኑ በብፁዕነታቸው ደብዳቤ ላይ ተገልጿል።
ዛሬ ሐሙስ ወደ መስቀል አደባባይ የሄዱ ወጣቶች ታስረዋል። ክፉኛ በፖሊስ ሲደበደቡ የሚያሳይ ቪዲዮ ወጥቷል። የመንፈሳውያን ወጣቶችና ጎልማሶች ማኅበራት ሕብረት አመራሮች ከታሰሩ በኋላ መለቀቃቸው ታውቋል።
በነገራችን ላይ የመስቀል አደባባዩ ዝግጅት የሰላም ሚኒስቴር የፈቀደው ነው። በደብዳቤው ላይ “አዳራሽ” የሚል ቃል በመጠቀሙ የበለጠ ማብራሪያ ፍለጋ ለሔዱት የመንፈሳውያን ወጣቶችና ጎልማሶች ማኅበራት ሕብረት ሁለተኛ ደብዳቤም ጽፎ ነበር ሰላም ሚኒስቴር። ፖሊስ ሁለቱም ደብዳቤዎች አሉት። ነገር ግን ደብዳቤውን የጻፈውን የመንግሥት አካል ከመጠየቅ ይልቅ ሰውን በቆመጥ ወደመቀጥቀጥ እና ወደ ማሰር ሄዷል። ይህ ደግሞ በጭራሽ ተቀባይነት የለውም። It is unacceptable.
አንድ ቤተ ክህነት ብዙ ድምፆች
*******
ቤተ ክህነት በማን ነው የሚወከለው? ታላላቅ ጉባኤዎችን ለማድረግ ከመንግሥት ጋራ የሚወያየው ማን ነው? “የቤተ ክርስቲያን የተለያዩ ይዞታዎችን፣ (ደመራና ከተራን ጨምሮ) በዓላት ማክበሪያዎች ሕጋዊ የሆነ የይዞታ ማረጋገጫ እንዲሰጣቸው የሚከራከረው፣ የሚደራደረው ማን ነው?” የሚለው ጉዳይ አሁንም ግልጽ እና ጥርት ብሎ መልስ አልተገኘለትም። እስካሁን ባየነው ከሆነ እነዚህን ሁሉ ሥራዎች ቤተ ክህነቱ እየሠራቸው አይደለም። የተለያዩ ማኅበራት ሊሠሩ ሲሞክሩ ግን እያየን ነው። የቤተ ክርስቲያን ይዞታዎችን በተመለከተ ጴጥሮሳውያን የተባለው የማኅበራት ስብስብ፣ የበዓል ዝግጅቶችን በተመለከተ ደግሞ የመንፈሳውያን ወጣቶችና ጎልማሶች ማኅበራት ሕብረት በስፋት ሲሳተፉ አይተናል።ቤተ ክርስቲያን አንድ አካል ናት ነገር ግን ስለ እርስዋ የሚናገሩት እርስበርሳቸው የማይደማመጡ ብዙ ድምፆች ናቸውጢ።
ተከፋፍሎ መቆም፣ ተነጣጥሎ መበላት
*****
ብዙ ምእመናን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላይ ብቻ ያነጣጠረ መንግሥታዊ አድልዎና መገለል እንዳለ ያምናሉ። ሌሎች ምሳሌዎችን እንኳን ብንተው የበዓለ ዕርገት ዝግጅት በሰሳም ሚኒስቴር ከተፈቀደ በኋላ መከልከሉን፣ ዛሬ ሐሙስ ጭምር ምእመናን መደብደባቸውን እንደ ምሳሌ ይጠቅሳሉ። በኦሮሚያ እና በደቡብ የተለያዩ አካባቢዎች የአካባቢው መንግሥታዊ መዋቅሮች የሚፈጽሙትን ለቁጥር የሚታክት የመብት ጥሰት አደባባይ ሚዲያ ለረዥም ጊዜ ስትዘግበው እንደቆየች ይታወቃል።
ኦሮሚያ ክልላዊ መስተዳድርን እና የኦሮሚያ ብልጽግናን በመሳሰሉ ተቋማት ኦርቶዶክሳዊነትን በጠላትነት የመፈረጁ አስተሳሰብ ሥር የሰደደ መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው። 
አሁን አሁን ደግሞ በራሱ በፌዴራል መንግሥቱም ሚዛናዊ ያልሆነና ወደ አንድ ወገን ያጋደለ የእምነት ተጽዕኖ እየታየ መምጣቱ የሚያሳስባቸው አያሌ ምራቃቸውን የዋጡ ዜጎች ሥጋታቸውን እየጠቆሙ ነው። “ብልጽግና ፓርቲ የብልጽግና ወንጌል ቅጥያ ነው፣ ፕሮቴስታንታዊ መንግሥት ለማቋቋም እየተሠራ ነው” የሚሉ ድምፆች እየበረከቱ ነው። በዚህ ውስጥ ሁሉ የቤተ ክርስቲያናችን ድምፅ አንድና ጠንካራ መሆን ሲገባው የተከፋለ፣ የተለያየ እና በጎበዝ አለቃ የሚመሩ ኃይሎች የተቆጣጠሩት መስሎ ተቀምጧል።
ለወደፊቱስ? አሁንም በፖሊስ እየተደበደብን እንቀጥላለን?
******
ቤተ ክህነት እና ምእመናኑን እንመራለን የሚሉ አካላት ሕዝቡን ለአደጋ እያጋለጡ ነው። ቤተ ክህነቱ ለወጣቶቹ ከለላ መሆን ነበረበት። አለበትም። ወጣቶቹም በስሜት ወደ እሳት እንዲገቡ የሚገፏቸውን ሰዎች ተንኮል መረዳት አለባቸው። የእባብ ጉድጓድን በእነርሱ እጅ ሊለኩ ለሚፈልጉ ብልጣብልጥ ሰዎች መጠቀሚያ መሆን የለባቸውም። ለራሳቸው የልብሳቸው ጥለት እንኳን በወላፈኑ እንደማይነካ የሚያውቁ ሰዎች በርቀት ሆነው “ውረድ ተዋረድ፣ ያዘው በለው” እያሉ የሚያሰማሩ የድል አጥቢያ አርበኞችን መስማት የለበትም። መቸም ዘመኑ የአክራሪዎች እና በስሜት የሚነዱ የስሜት ነጋዴዎች የገነኑበት በመሆኑ ልጆቻችን ለአደጋ እየተጋለጡ ነው።
ከምንም በፊት የሀገር ሰላም ይቅደም!!!!!
******
ሀገራችን በጣም ወሳኝ ወቅት ላይ ትገኛለች። በውስጥም በውጪም ተወጥራ ያለችበት ወቅት ነው። መንግሥትን እና የሚከተለውን ፖሊሲውን እንዲሁም መሪዎቹን ላንወዳቸው እንችላለን። ነገር ግን ሀገራችን አደጋ ላይ ስትወድቅ መመልከት የለብንምና አሁንም የሀገራችንን ሁኔታ በቅጡ እንመርምር። የላይ ፈሪ የታች ፈሪ እያሉ የሀገራችን ውስጣዊ ሰላም እንዲናጋ ለሚሠሩ አካላት ዕድል አንስጣቸው። የውጪ ወራሪዎች ድንበራችን ላይ አሰፍስፈው ቆመዋል። ምዕራባውያን መንግሥታት በየቀኑ የስብሰባቸው አጀንዳ አድርገውናል። የታጠቁ ቡድኖች በሁሉም አቅጣጫ ጦር ሰብቀውብናል።
በዚህ ጊዜ ክርስቲያኑ ወደበለጠ መለያየት የማይወስደውን መንገድ መከተል አለበት
 ማኅበራት ከቤተ ክህነት ጋራ የበለጠ መቀራረቢያው ጊዜ አሁን ነበር። ማኅበራቱ (ለቅዱስ ፓትርያርኩ ባሳዩት ወገንተኝነት እንደታየው) ለቤተ ክህነቱ ትልቅ ጉልበት መሆን ይችላሉ። ቤተ ክህነቱን ለሃይማኖቱ ግድ የማይሰጠው፣ እኛ ብቻ ቤተ ክርስቲያናችንን የምንወድ አድርጎ ራስን መቁጠር ውጤቱ ጥሩ አይሆንም። ያለን ቤተ ክህነት ደካማ ቢሆን እናበርታው። ፈሪ ከሆነ እናጀግነው፣ ጉልበት ካነሰው ጉልበት እንሁነው። እርስበርሷ የተለያየች ማኅበር መጨረሻዋ ምንድር ነው? መፍረስ!!!!!!
Filed in: Amharic