>

ታላቅ ሁን ሲባል ጥቃቅን አነስተኛ ካልሆንኩ ባዩ የአብይ መንግስት...!!! (ጎዳና ያእቆብ)

ታላቅ ሁን ሲባል ጥቃቅን አነስተኛ ካልሆንኩ ባዩ የአብይ መንግስት…!!!

ጎዳና ያእቆብ

    ረሀብን እንደ ጦር መሳሪያነት የኢትዮጵያ መንግስት እየተጠቀመበት ነው ሲባል የኢትዮጵያ መንግስት የጦር ወንጀል እየፈፀመ ነው የሚል በአለም አቀፍ ህግ ተጠያቂነት የሚያስከትል መሆኑን መንግስት መረዳት አለመቻሉ እና ነገሩን አቃሎ ማየት የሚያስደንቅ ነው::
ህዋሃት ጣርነቱን ጀመረው ከሚለው ወደ ሁለቱም (የአብይ መንግስት እና ህዋሃት) እነሱ ናቸው እነሱ ናቸው በሚል እየተካሰሱ ነው ወደሚል ተቀይሯል:: 350,000 በረሀብ አለንጋ እየተገረፉ ነው:: ከ90% በላይ የሚሆን የትግራዋይ ደግሞ ሰው ሰራሽ የረሀብ አደጋ ላይ ነው::
የአብይ አስተዳደር ይህን የተጋረጠበት የወንጀል ተጠያቂነት በምርጫ: በዶክመንተሪ ጋጋታ እና ክብ ሰርቶ በመቀመጥ ሊሻገረው አይችልም:: ያለው አንድ አማራጭ እልኸኛነቱን ትቶ ምክኒያታዊ የሆነ የአካሄድ ማሻሻያ መድረግ ብቻ ነው:: በኔ እይታ ያ እንኳን መንበሩን የሚያፀናለት አይመስለኝም::
የአለም አቀፍ ማኅበረሰብ ደግነት ከተሰማ ለዘላቂ ሰላም ሲል የወንጀል ተጠያቂነቱን ለጊዜው ሊያቀልለት ይችላል:: ነገር ግን የጦር ወንጀልና በሰብአዊነት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ይርጋ የማያግዳቸው ስለሆነ የሀገርን ጥቅም እንኳን በሚነካ መንገድ ሊያሾሩት ስለሚችሉ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በትመለከት liability እንጂ asset ሊሆን አይችልም:: Compromised ሆኖአል:: እዚህ ደረጃ ላይ እንዳይደርስ ነበር ተው ረጋ በል ሲባል የነበረው::
መካሪ የሌለው ንጉስ ካለአንድ አመት አይነግስ እንዲሉ እራሱን በዚህ ደረጃ አውርዷል:: ታላቅ ሁን ሲባል ጥቃቅንና አነስተኛ ካልሆንኩ ብሎ አንዴ ወደ ጎጥ ከረጢት ስገባ ሌላ ጊዜ ደግሞ ዘምኑ ካለፈበት አምባገነን ኢሳያስ አፍወርቂ ጋር አንድ አካል አንድ አምሳል ካልሆንኩ በማለት ታላቅም ትልቅም መሆን አቅቶት ስጋት ሊገድለኝ ነውና ከባችሁ አይዞህ በሉኝ: ጠብቁኝ ማለት ጀምሯል:: የውስጥ አንድነትን ጠብቆ ቢሆን ኖሮና የህዝብ ድጋፍን ይዞ ቆይቶ ቢሆን ኖሮ ክበቡ. ማለት ባላስፈለገው ነበር::
በኦሮሞ ወጣቶችን በእስር ቤት ሞልቶና ካለምንም ተጠያቂነት ሲገድል ከርሞ የጨነቀ ለት በኦሮሞ ማኅበረሰብ ውስጥ መደበቅ የማይታስብ ነው:: የኦሮሞ ማኅበረሰብ ከአብይ ልቡን ካሸፈተ አመታት ተቆጥረዋል:: የአማራው ማኅበረሰብ የደረሰበት ሰቆቃ የማይነገር ግፍና ጭፍጨፋ #በቃን! አስብሎት በአደባባይ ተቃውሞውን ካሰማ ቆየ:: የአዲስ አበቤ ነገር ግልፅና ማብራሪያ የማያስፈልገው ነው:: ረሀብን እንደጦር መሳሪያ ሲጠቀም: በባእድና በቀለኛ ሰራዊት ተጠቅሞ ትግራይን የጦርነት አውድማ ሲያደርግ የትግራይ ማኅበረሰብ ከአብይ ልቡ ሸፍቷል:: ወላይታም በሰላም ህገ መንግስታዊ መብታቸው የሆነውን የክልልነት ጥያቄ ለመድፈቅ መከላከያ አሰማርቶ ሲያስገድልና አመራሮቻቸውን ፍርድ ቤት ልውፍርድ ቤት ሲያንከራትት ልባቸውን ምን ያህል ከሱ ሊያርቁ እንደሚችሉ ማሰብ አያዳግትም:: ደቡብ ነው? ጌዲዮ ነው? ማን ነው ዛሬ ክብ የሚሰራለትና የሚጠብቀው?
የሰላም የተስፋ የፍቅር መሀረቡን በእብሪት ጥሎ ሲያበቃ ክብ ሰርታችሁልኝ መሀረቤን ያያችሁ ልበል ሲል too little, too late እንጂ ምን ይባላል:: ማንም የቆመ ቢመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ የሚለውን የቅዱሱን መፅሀፍ መልካም ምክር ንቆ በእብሪት ሲራመድ ትእቢት ውድቀትን ትቀድማለች የሚለውን ማሳሰብ ግድ ይላል::
የአብይ አህመድ መንግስት እንኳን በምርጫ ቀርቶ በመለኮታዊ ጣልቃ ገብነት የማይድንበት ወሳኝ ሰአት ላይ ደርሷል:: ለዚህም ታልቅ ውድቀት ከራሱ ውጪ ማንም ሊወንቅስ አይችልም:: ከጎሮቤት ሀገረ ኤርትራ ጋር ቤተሰባዊ ግንኙነት ነው ያለን የሚል መርህ አልባ የቂል ግንኙነት ከሰላም ሎሬትነት ወደ የጦር ወንጀለኛነት ነድቶ አድርሶታል::
የኢትዮጵያ ህዝብ አክብሮ የሰጠውን ትልቅነት ወደ ሀገራዊ ታላቅነት መቀየር ተስኖት አጥር እጠሩልኝ:: ክበቡኝ:: ጠብቁኝ የሚል ሆኗል:: ሆዳቸው እስከሞላ ድረስ አድር ባይና በላተኛው እንደሚከበው ግልፅ ነው:: አድር ባይ ግን በባህሪው በሞቀበት የሚያሞቅ እንጂ ብርድ ብርድ አለኝ ክበብኝ ከሚል ጋር የሚሰለፍ የችግር ቀን ወዳጅ አይደለም:: ምእመናኖቹም እስከ ጊዜው ድረስ አብረው ቆይተው እንደ ኤማሆስ መንገደኞች እንዲህና እንዲያ የሚያደርግ መስሎን ነበር ብለው በሀዘን መበታተናቸው አይቀሬ ነው::
ትንሽ አብረውት የሚያዘግሙት ካፈርኩ አይመልሰኝ ባዮችና አብረውት በፍርድ ወንበር ላይ የሚቆሙ ካድሬዎች ናቸው:: በመጨረሻው ግን አምባገነኖችና ጨቋኞች ሁሌም እንደሚያደርጉት ወይ ዘርፎ ሀገር ለቆ ይሰደዳል:: ካልሆነም ከሆነ ጉድጓድ ይጎተታል:: አብይን እረሱን ካስገባበት አዘቅት ሊያወጣው የሚችል ምድራዊ ሀይል የለም::
ጥያቄው እራሱን ችሎ ይወድቃል ወይስ ሀገራችንን እሱ የገባበት አዘቅት ውስጥ ይዞት ይዘፈቃል የሚለው ነው::
Filed in: Amharic