>
5:13 pm - Sunday April 19, 1964

“ጎንደር ተበላሸ!” ማለትስ አሁን ነው (ዳግማዊ ጉዱ ካሣ)

“ጎንደር ተበላሸ!” ማለትስ አሁን ነው

ዳግማዊ ጉዱ ካሣ

martyrof2011@gmail.com

 


አንድ ሰው ተወልዶ እስኪሞት የሀዘንና የደስታ ፍርርቆች ውስጥ መኖሩ የማያሻማ ግልጽ አውነት ነው፡፡ ተመጣጥኖው ግን እንደሰውዬው ዕድልና የጥረት መጠን ሊለያይ ይችላል፡፡ ሀዘን የሚበዛበት ይኖራል፤ ደስታው የሚያይልም እንደዚሁ፡፡  ደስታና ዘሀን ደግሞ በገንዘብ መሙላትና ማጠጥ አይወሰኑም፡፡ ለሀዘንም ሆነ ለደስታ የገንዘብ ሚና አንድ ግብኣት እንጂ ብቸኛው ወሳኝ ነገር አይደለም፡፡ በአእምሮ እንጂ በገንዘብ ድህነትህ ብዙም አትከፋ ታዲያ – የእግረ መንገድ ማስታወሻ ነው፡፡ የገንዘብ ድህነትህ ስትሞት ይጠፋል፤ የአእምሮ ድህነትህ ግን ስትሞት ይበልጥ ይገናል፡፡ “ገንዘብ የኃጢኣት ምንጭ ነው” መባሉ ለኔ ቢጤዎች ያለው መጽናኛነት በበጎ ጎኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ያዘለውን እውነት ካለይሉኝታ መቀበሉ ከብዙ ቁሣዊና መንፈሣዊ ውጣ ውረድ ይታደጋል፡፡  

በሕይወት ዘመኔ እንደዚች ቅጽበት ያዝንኩበትን አጋጣሚ ብፈልግ አጣሁ – ብዙ ጊዜ አዝኛለሁ፤ ደስ ለመሰኘት ሞክሬያለሁም፡፡ በጎንደር የብል(ጽ)ግና የድጋፍ ሰልፍ ምክንያት መፈጠሬን እስክራገምና ኢትዮጵያዊነትን እስክጸየፍ ክፉኛ አዝኛለሁ፡፡ ኢትዮጵያ እውነትም ሰው አይውጣብሽ ተብላ ተረግማለች፡፡ በእውነቱ በቁማችን ሞተናል፡፡

በአፄ ኃ/ሥላሤ ዘመን ነው፡፡ አዲስ አበባ ይኖሩ የነበሩ አንድ የጎንደር ባላባት የአውሮፕላን ትኬት ለመቁረጥ ከአሽከራቸው ጋር ወደ አንዱ የአየር መንገዱ የትኬት ቢሮ ይሄዳሉ፡፡ እንደደረሱም “ከነአሽከሬ ወደ ጎንደር እምሄድ ነኝና ስንት ነው ክፍያው” ብለው ትኬት ቆራጩን ይጠይቁታል፡፡ ሠራተኛውም “ለአንድ ሰው 75 ብር፤ ለሁለታችሁ 150 ብር ነው ጌታየ” ይላቸዋል፡፡ ሰውዬው ያኔ እሳት ጎርሰው እሳት ለብሰው “ምን አልክ? እሱንም እንደሰው ቆጥረህ እኩል ልታስከፍለኝ ነው? አንት የሰው ልክ የማታውቅ ባለጌ የባለጌ ልጅ?…” በማለት በባላባታዊ የነገር ጅራፍ እስካጥንቱ ገብተው ይገሸልጡታል፡፡ ትኬት ቆራጩ ብልኅ ነበርና “አፌን አዳልጦት ነው ጌታየ! እባክዎ ይቅርታዎትን፡፡ እኔ ተሳስቼ እንጂ ክፍያው ለእርስዎ 100፣ ለአሽከርዎ ደግሞ 50 ብር ነው፤ አይለመደኝም ጌታየ” በማለት ተለሳልሶ ያስረዳቸዋል፡፡ እሳቸውም “አዎ፣ እንዲያ ነው ጨዋ ማለት፡፡ ጌታና አሽከር እኩል አይደለም፤ እኩልም አይከፍልም…” ብለው ቁጣቸውን ወደ አፎቱ ይመልሳሉ፡፡ ነገሩ ሥነ ልቦናዊ ነው፡፡ ሰውዬው እውነቱ ጠፍቷቸው ሳይሆን አሽከራቸው ከእርሳቸው እኩል እንዳልሆነ ይህችን ጠባብ ዕድል ሳይቀር በመጠቀም እንዲረዳቸው ለማድረግ ፈልገው ነው፡፡ 

የሽማግሌው ነገር በዚያ ብቻ ቢያበቃ ማለፊያ በሆነ፡፡ ጉዞው ሊጀመር ሲል ምናልባት ሲወዛወዙ ሆዳቸው ተረብሾ ያኮረፈ ምግብ ወደላይ ፍልቅ ቢል መቀበያ እንዲሆናቸው በሚል አስተናጋጆቹ ፌስታል ነገር ለተሣፋሪዎች ሁሉ ማደል ይጀምራሉ፡፡ ምክንያቱን አስረድተው ለዚያ ባላባት ሊሰጧቸው ቢሉ “ማን? እኔ? እኮ እኔን ሊያስመልሰኝ?” በማለት በስድብ ወርፈው አስተናጋጆቹን ያባርሯቸዋል፡፡ መኳንንት አያስታውክማ! ሆ! አስተናጋጆቹም ድፍረታቸው፡፡

አውሮፕላኑ ተነስቶ ጥቂት እንደተጓዘ የተፈራው አልቀረም ሽማግሌው ፊታቸው ይለዋወጣል፡፡ ከጥቂት ቅጽበት በኋላም አፋቸውን በመዳፋቸው ግጥም አድርገው በመያዝ ከተቀመጡበት ተነስተው ወደፓይለቱ በር ያመራሉ፡፡ ከዚያም “አቁም በለው! ጎንደር ተበላሸ አቁም በለው! እኔ ነግሬያለሁ…” እያሉ በመጮህ ሕዝቡን በሣቅ ገደሉት ይባላል፡፡ አንድ ሰው አስመለሰውና ጎንደር ሲዋረድ ይታያችሁ፡፡ ለሽንትና ለንፋስ በአንዳንድ ሥፍራዎች ቆም የሚያደርግ የክፍለ ሀገር አውቶቡስ ሳይመስላቸው ይቀራል? ለዚያ አባት “አልሰሜን ግባ በለው” ብላቸው ደስ ባለኝ፡፡

አዎ፣ አቢይ አህመድ ጥቁር ውሻ ይውለድ! መሬት አትቀበለው፡፡ ሁሉም የሰማይ በሮች ይዘጉበት፡፡ ኢትዮጵያን አዋርዷልና የእጁን አይጣ፡፡ የእግዚአብሔር በትር ትረፍበት! ፈጣሪ ፍርዱን በቅርቡ ይስጠው፡፡ ሌላ የምለው የለም፡፡

ብዙ ነገር እያሳጣን ነው፡፡ በግለሰብ ደረጃ ብዙዎችን አሳጣን፡፡ አሁን ደግሞ አንድ ክፍለ ሀገር ቀማን፡፡ ይህ ሰው እግዚአብሔር እስኪፈርድበት ድረስ ስንት ነገር እንደሚያሳጣን መገመት ይቸግራል፡፡ የርሱ መጨረሻ በተቃረበ ቁጥር የምናጣው መብዛቱ ግን እያሳሰበኝና እያስጨነቀኝም ነው፡፡ ወገኖቼ በአንድ አምላክ ጽኑና ጸልዩ! ጊዜው ቀርቧል፡፡

በሰሞነኛ የጎንደር የብልግና ሰልፍ የማይናደድ ጤናማ ኢትዮጵያዊ ይኖራል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ትልቁ ዳቦ ሊጥ ሲሆን የማይናደድ የለም፡፡ ያመኑት ፈረስ በደንደስ ሲጥል የማይበሳጭ አይኖርም፡፡ “አማራ እንኳንስ ተለያይቶ አንድ ሆኖም በሆነለት” ለሚሉ ወገኖች ይህ ዓይነቱ የጎጥና የሸጥ ክፍፍል ትልቅ መርዶ ነው፡፡ ለኦህዲድ ሸኔ ደግሞ ፌሽታ፡፡ 

ለፀጉር ስንጠቃ አንሩጥና እኔ በመሠረቱ በሕዝብ ኅልውና አምኜ አላውቅም፡፡ አንድ ዓይነትና የአእምሮ ብስለትን የሚጠይቅ ነገር ከሕዝብ አይጠበቅም፡፡ ሕዝብ ጎርፍ ነው፡፡ ጎርፍ ደግሞ ቆም ብሎ ማሰብ አይችልም፡፡ በፊቱ ያገኘውን እያገለባበጠ መውሰድ የጎርፍ ዓይነተኛ ባሕርይ ነው፡፡ ኃላፊነትን መሸከም ጠባዩ ስላልሆነ ሕዝብ የሚባለው ነገር ከጽንሰ ሃሳባዊ የማስመሰያ ትንታኔዎችና ገለጻዎች ባለፈ ሚዛን ሊደፋ የሚችል ብዙም የረባ ትርጉም የለውም፡፡ ከዚህ አኳያ “ሕዝብ ይፍረደኝ” የምትለዋ አስቂኝ አባባል ሁሌም እኔንም ታስፈግገኛለች፡፡ ማንን ለማስደሰት እንደምትባልም አላውቅም፡፡ ክፉም ሆነ ደግ የሚያስቡ ጥቂቶች ከፊት ሆነው እንደፈለጉ ሊያሾሩት ይችላሉ – ሕዝብን፡፡ ማንን እንምትደግፍ ሳታውቅና በተሳሳተ ወይ በተንጋደደ መረጃም ግልብጥ ብለህ ወጥተህ ወዳጅህን ልትቃወም ወይም ጠላትህን ልትደግፍ ትችላለህ፡፡ ሕዝብ የሚባል ነገር ስለሌለም ጸጸት የሚባል ነገር ሲያልፍ አይነካውም – ማን ይጠየቃል? ማንስ ነው ጠያቂው? ከዓለም መፈጠር ጀምሮ በተሳሳተ መረጃ ያበደ የሕዝብ መንጋ በሽዎችና በሚሊዮኖች ላይ እጅግ ብዙ ዘግናኝ አደጋዎችን አድርሷል – ዘቅዝቆ እስከመስቀልና ሰውነትን ቆራርጦ በእሳት እስከማቃጠል፡፡ ክርስቶስ የተሰቀለው በዚህ ዓይነት የስቅሎ ስቅሎ የመንጋ ፍርድ ነው፡፡ ያኔ እንዲያ የሆነ አሁን እንዲህ አይሆንም ብለን አንጠብቅም – በጎንደር ግን ሰቀጠጠኝ፤ ክፉኛም አዘንኩ – ከትግል ክብሪት መለኮሻ ሥፍራ የትግል ማኮላሻ በረዶ ይፈጠራል ብሎ ማን ሊገምት ይችላል? ለማንኛውም ይህን ሰልፍ ያስተባበሩና የመሩ፣ ይህን ደግና ጨዋ ሕዝብ ለዚህ ውርደት የዳረጉ ሰዎች ዘር አይውጣላቸው፡፡ በአካባቢው ያላችሁ ጤነኛ ወገኖች ታሪክን መዝግቡ፡፡ ጎንደርን ለዚህ የወረደ ተግባር ያበቁ ሰዎችን ስምና አድራሻ ያዙ፡፡ ለመበቀል አይደለም – ነጋችንንም እንዳያበላሹ ምናልባት ጥቂቶችም ብንሆን ለነገ መድረሳችን አይቀርምና ለጥንቃቄ ያህል ነው፡፡ እንጂ ከእግዚአብሔር ፍርድና ፍርዱም ከሚያላብሰን መለኮታዊ ፀጋ በስተቀር እኛ አንበቀል፡፡ እግዚአብሔር “በቀልን ለኔ ተዋት” ብሏልና ወደርሱ ብቻ እንጩህ፡፡

ዝናሽ ታያቸው ጎንደሬ መሆኗ፣ ብዙዎቹ የተላላኪው ብአዴን አጋሰሶች በጎንደሬነት መታማታቸው፣ ትብታባሙና ርኩስ መንፈስ የተቆራኘው አቢይ ለጠነሰሰው ሸር ስኬት ሲል ወደዚያ አካባቢ መመላለሱና አንዳንድ የአማራ ባለሀብቶችን ማባበሉ፣ ተረኞቹ ኦህዲዶች ጎንደርን ለማታለል ሲባል ለፋሲል ከነማ 25 ሚሊዮን ብር መመጽወታቸው፣ … ለዚህ በእውን ሊታሰብና ሊደረግ ቀርቶ በህልምም ሊታሰብ የማይችል ውርደት ዳርጎን ከሆነ አላውቅም፡፡ “የቀን እንጂ የሰው ጀግና የለውም” ይባላልና የነገ ሰው ብሎን ነገ ሁሉም ተፍረጥርጦ እናየዋለን፡፡

እጅግ የሚገርመው ደግሞ እኔ በጎንደር ውስጥ ሲውለበለብ የማውቀው ባንዲራ የጥንቱን ነበር፡፡ አሁን ያየሁት ግን ባለአምባሻውና የዲያቢሎስ ዓርማ ያለበት የኢሕአዲጉን ነው – የጎንደርን መለወጥ ለማመን ጊዜ ያስፈልገኝ ነበርና ክፉኛ የመደንገጤ ምክንያትም ይሄው ነው – ቀኝ እጄን የተቆረጥኩ ያህል ነው የተሰማኝ፡፡ ይህን ሕዝብ ከአማራ ወንድሞቹ ለመነጠል የተጎነጎነው ታላቅ ሤራ አሁን ነው ቁልጭ ብሎ የታየኝ፡፡ ይህንንም ስል ሁሉንም የጎንደር ነዋሪ ማጠቃለሌ እንዳልሆነ መግለጽ እወዳለሁ፤ ሁሉም ብልጽግናን ደጋፊ ሆኖ ከተገኘ ግን ከዚህም በላይ ከማለት አልመለስም – ለምሳሌ “ብልጽግናን መደገፍ አማራንና ኢትዮጵያን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት ቆርጦ እንደመነሣት በመሆኑ ብልጽግና ፓርቲን የደገፈ፣ ሰላማዊ ሰልፉን ያስተባበረ፣ በአባልነት ወደብልግና ፓርቲ የተደመረና ንጹሓንን ያስደመረ … ሁሉ፡- በመተከል፣ በጉራ ፈርዳ፣ በወለጋ፣ በሰሜን ሸዋ፣ በባሌ፣ በሶማሌ … የታረዱ አማሮች አጥንት እሾህ ሆኖ ይውጋው” ማለት አይከብደኝም፡፡ ለማንኛውም ሁሉም የሥራውን እንደሚያገኝ ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡ ሰው ነኝና ግን በማየው ነገር ለጊዜው መንጨርጨሬ አልቀረም፡፡ ከነፃነት በፊት ወደዚህ መድረክ ባልመጣ ደስ ይለኛልና የምታስቡልኝ ካላችሁ ጸልዩልኝ፡፡ የኢትዮጵያ ነፃነት ስለመቅረቡ ግን አደራችሁን ቅንጣት አትጠራጠሩ!! ጨለማ የሚበረታው ፈንቅሎት ሊወጣ የሚፈልግ ብርሃን ከኋላው እያስጨነቀው መሆኑን ካላመንን ተሳስተናል፡፡

Filed in: Amharic