>
8:40 pm - Tuesday March 21, 2023

የመስቀል አደባባይ ነገር ...!!! (ዘመድኩን በቀለ)

የመስቀል አደባባይ ነገር …!!!

ዘመድኩን በቀለ

… ደስ ይላል። መስቀል አደባባይ… መስቀል አደባባይ እንደሆነ… በዚያው በመስቀል አደባባይነቱ እድሳት ተደርጎለት…ስሙም በእብነበረድ ላይ ተቀርጾ በይፋም በክብር መመረቁን አይተናል። ተመልክተናልም። ይሄ እጅግ ሸጋ ነው። ፕሮጀክቱን በቃላቸው መሠረት የቦታም፣ የቅርጽም፣ የስምም ለውጥ ሳይደረግበት አስጀምረው ውብ አድርገው ላስፈጸሙት ሁሉ ክብር ይግባቸው። በተለይ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ የሚወቀሱባቸው እልፍ ጉዳዮች ቢኖሩም በዚህ ፕሮጀክት ጉዳይ ግን ሊመሰገኑም ይገባል። ኢንጅነር ታከለ ኡማንም ወሮ አዳናች አቤቤንም በዚህ ጉዳይ አለማመስገን ንፉግነት ነው።
… በምርቃት ሥነ ሥርዓቱም ላይ ቤተ ክርስቲያኒቱ መጋበዟም መልካም ቢሆንም… በሥፍራው የቤተ ክርስቲያኒቱ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ የሆኑት በብፁዕ አቡነ አረጋዊን ብቻ ማየት መመልከታችንን መነሻ በማድረግ ከምስጋናው ቀጥሎ የሚከተለውን ጥያቄ ለመጠየቅ እንወዳለን።
…ጥያቄ ?
፩ኛ፦ ቦታው ወይም ስፍራው ሌሎች ማኅበራዊ ክዋኔዎች የሚካሄዱበት ቢሆንም በዋናነት ግን በማይዳሰሱ ቅርሶች ዘርፍ በዩኔስኮ ጭምር በዓለም አቀፍ ደረጃ የተመዘገበ የቤተ ክርስቲያኒቱ የመስቀል በዓል ማክበሪያ የደመራው መደመሪያ አደባባይ መሆኑ ይታወቃል። ከግንባታው መጀመር አንሥቶ ዲዛይኑም ጭምር ተግባራዊ ሲደረግ መንግሥት ቤተክርስቲያኒቱ ጋር በመመካከር መሥራቱም ይታወቃል። እንዲያውም በግንባታው ሂደት መሃል ግንባታው የደረሰበትን የሥራ ሂደት በቅዱስ ፓትርያሪኩ የሚመራ አባቶች ያሉበት አንድ ቡድን ከከተማዋ ምክትል ከንቲባ ጋር በሥፍራው ተገኝተው መጎብኘታቸውን፣ ቅዱስነታቸውም ምስጋናና አስተያየት መስጠታቸውንም እናስታውሳለን። ዛሬ ታዲያ ግንባታው ተጠናቅቆ በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ቤተ ክርስቲያኒቱ በውጭ ጉዳይዋ በኩል ብትወከልም የተሰማትን ደስታም ይሁን ቅሬታ እንድትገልጽ በስፍራው ተገኝታ ንግግርም እንድታደርግ ያልተደረገው ለምንድነው?
… የከተማዋ ከንቲባ የሚመርቁት ፕሮጀክት ላይ የከተማዋ የሃገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ መገኘት ነበረባቸው። የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር በተገኙበት አደባባይ ደግሞ ቅዱስ ፓትርያሪኩ መገኘት ነበረባቸው። መገኘት ብቻ ሳይሆን ንግግርም ማድረግ ነበረባቸው። ይሄ ያልተደረገው ለምንድነው? ተገፍተን፣ ተንቀን፣ ወይስ ተጠርተው አንገኝም ብለው ነው?
… መስቀል አደባባይ አምሯል። ተውቧል። የደመራ እንጨት መትከያው ሥፍራም በልዩ ሁናቴ ተዘጋጅቷል። የምዕመናን መቀመጫ ወንበሮችም ግሩም ተደርገው ተውበው ተሠርተዋል። መስከረም 16 ምሽቱን ከጧፍ ብርሃን ጋር የመስቀልን የደመራ በዓል ስናከብር የሚፈጠረውን አስደማሚ የሆነ መንፈሳዊ ስሜት ከወዲሁ ሲታሰብ ልዩ ደስታ ይፈጥራል። ከምር ይሄኛው ደስስ ይላል።
፪ኛው ጥያቄ ደግሞ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ጉዳይ ነው። ከዚህ ቀደም ከዚያው ከመስቀል አደባባዩ አፍንጫ ስር ከቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ግርጌ በከተማው ነዋሪ ገንዘብ መናፈሻ ሥፍራ ተብሎ የተሠራውን ፕሮጀክት ለኢሬቻ በዓል ማክበሪያ ይሆን ዘንድ ተወስኖ ባለ ኢሬቻዎቹ ሳይጠይቁ ካርታ ተዘጋጅቶላቸው በልመና በሚመስል መልኩ እንደተሰጣቸው ይታወሳል። ዛሬስ የመስቀል አደባባያችን የባለቤትነት ካርታ ጉዳይ ከምን ደረሰ? የኢሬቻውን አዲስ ይዞታ ያህል ክብር ያልተሰጠውስ ለምንድነው? ቤተ ክርስቲያኒቱ በደብዳቤ ጭምር ጠይቃለች።
… መልስ እስክናገኝ ድረስ እኛም እንጠይቃለን …
Filed in: Amharic