አወድ መሀመድ
ፖለቲከኞች እና የማህበረሰብ መሪዎች በሁከት እንዳይሳተፉ እና ሌሎችን ከማነሳሳት እንዲቆጠቡም አሜሪካ አሳስባለች”
“ኢትዮጵያ ተግዳሮቶቿን እንድትፈታ እና ወደ ብሩህ የወደፊት ጎዳና እንድታቀና አሜሪካ ለመርዳት ዝግጁ ነኝ ብላለች”
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቀጣዩን የኢትዮጵያ ምርጫ በተመለከተ ያወጣውን መግለጫ የጀመረው፣ሰኔ 14 ቀን በርካታ ኢትዮጵያዊያን ለዜግነት እና ለፖለቲካዊ መብቶቻቸው አስፈላጊ በሆነው ምርጫ ድምፅ እንደሚሰጡ በመግለፅ ነው፡፡ ይህ ምርጫ እንደ ነጠላ ክስተት መታየት የለበትም ያለው ሚኒስቴሩ፣ ይልቁንም “ውይይትን ፣ መተባበርን እና መግባባትን የሚያካትት የዴሞክራሲያዊ ፖለቲካ ሂደት አካል ነው” ብሏል፡፡ ለዚህም ስኬት “የአገሪቱን ዴሞክራሲ እና ብሔራዊ አንድነት ለማጠናከር የሚወስደውን መንገድ ለመወሰን ከምርጫው በኋላ ሁሉንም የሚያካትት ፣ የፖለቲካ ውይይት ለማድረግ የኢትዮጵያ መንግስት እና ሁሉም ኢትዮጵያዊያን እንዲዘጋጁ እናሳስባለን” ብሏል ሚኒስቴሩ።
የሚኒስቴሩ መግለጫ በማከልም “በርካታ ኢትዮጵያዊያን በግጭቶች ሳቢያ በአመፅ እና በግጭት ምክንያት በተከሰተ የምግብ እጥረት እየተሰቃዩ እና እየሞቱ ባሉበት በዚህ ወቅት ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና ባልደረቦቹ ለዚህ ምርጫ ለመዘጋጀት ያደረጉትን ጥረት እንገነዘባለን” ሲል ገልጿል፡፡
ፖለቲከኞች እና የማህበረሰብ መሪዎች በሁከት እንዳይሳተፉ እና ሌሎችንም ከማነሳሳት እንዲቆጠቡም አሜሪካ በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቷ በኩል አሳስባለች፡፡ ሁሉም የፖለቲካ ተዋናዮች እና የማህበረሰብ አመራሮች ቅሬታዎችን በድርድር ፣በውይይት እና እውቅና ባላቸው ከአመጽ ውጭ የሆኑ የግጭት አፈታት ስልቶች ለመፍታት መዘጋጀት እንዳለባቸውም ነው አሜሪካ የጠየቀችው፡፡
አሜሪካ የኢትዮጵያ መሪዎች ነፃ ሚዲያ እና ንቁ ሲቪል ማህበረሰብን እንዲደግፉም ማሳሰቧን ቀጥላለች፡፡ መንግስት የዜጎችን ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ ፣ በሰላማዊ መንገድ የመሰብሰብ እና የመደራጀት መብትን እንዲያከብር እና “የበይነመረብን ከመዝጋት ወይም ኔትወርክን ከመገደብ እንዲቆጠብም እንጠይቃለን” ይላል መግለጫው።
መጪው ምርጫ የሚካሄድበት ከባቢያዊ ሁኔታ እጅግ እንደሚያሳስባት የገለፀችው ሀገሪቱ፣ “የተቃዋሚ ፖለቲከኞች መታሰር ፣ ነፃ ሚዲያዎችን ማዋከብ ፣ የአካባቢና የክልል መንግስታት የወገንተኝነት እንቅስቃሴዎች እና በመላው ኢትዮጵያ የሚስተዋሉ በርካታ የዘር እና የማህበረሰብ ግጭቶች ለነፃ እና ፍትሃዊ የምርጫ ሂደት እንቅፋቶች ናቸው ፤ እንዲሁም ኢትዮጵያውያን በምርጫው ላይ ያላቸውንም እምነት ጥያቄ ውስጥ ያስገባሉ ነው ያለችው። በፀጥታ ጉዳዮች እና በውስጣዊ መፈናቀሎች ምክንያት በርካታ መራጮችን ከዚህ ውድድር ማግለሉ በተለይ አሳሳቢ እንደሆነም አሜሪካ ገልጻለች፡፡
“በበርካታ የኢትዮጵያ ክፍሎች ውስጥ የክልል እና የጎሳ ክፍፍሎች መጠናከር የአገሪቱን ህዝብና የግዛት አንድነት አደጋ ላይ ይጥላል” መግለጫው እንደሚለው፡፡ ከምርጫው በኋላ ያለው ጊዜ ኢትዮጵያውያን እነዚህን ክፍፍሎች ለመጋፈጥ አንድ ላይ እንዲሰባሰቡ ወሳኝ ወቅት እንደሚሆንም ነው አሜሪካ የገለፀችው፡፡ ኢትዮጵያ እነዚህን ተግዳሮቶች እንድትፈታ እና ወደ ብሩህ የወደፊት ጎዳና እንድታቀና አሜሪካ ለመርዳት ዝግጁ ነኝ ስትል በመግለጫው አስታውቃለች፡፡ በመግለጫው ማጠቃለያም “ለአገሪቱ ሰላማዊ ፣ ዴሞክራሲያዊና አስተማማኝ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ከሚሰሩ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ጎን እንቆማለን” ብላለች፡፡
አሜሪካ ኢትዮጵያን በተመለከተ ሰኔ 4 ቀን 2013 ዓ.ም የሰጠችው መግለጫ ከሰሞኑ መግለጫዎች አንጻር መለሳለስ የታየበት ይመስላል። በዚህኛው የአሜሪካ መግለጫ፣ ባልተለመደ መልኩ፣ የትግራይ ክልል ጉዳይ በተናጠል አልተነሳም። የመረጃው ምንጭ