ጌታቸው ሽፈራው
የኢዜማው መሪ ብርሃኑ ነጋ ከአማራ ቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ ኢትዮጵያ ውስጥ የዘር ፍጅት አልተፈፀመም ብለው ተከራከረዋል። ጋዜጠኛው ጉዳዩን የሚያስተካክሉበት እድል ቢሰጣቸውም የኢዜማው መሪ ግን ከአቋማቸው ፍንክች አላሉም።
የአማራ ሕዝብ ከሌሎቹ ኢትዮጵያዊ ወገኖቹ በተለየ በሰነድ ተፈርጆ የተጠቃ ሕዝብ ነው። የአማራ ሕዝብ “ነፍጠኛ፣ ተስፋፊ፣ ወራሪ፣ መጤ፣ ሰፋሪ” ተብሎ የተጠቃ ሕዝብ ነው። የአማራ ሕዝብ ሌሎቹን ጨቁኗል ተብሎ የተጠቃ ሕዝብ ነው። ይህ የዘር ፍጅት በአዲስ መልክ 30 አመት ዘልቋል። ከአርባ ጉጉ እስከ ጉራፈርዳ፣ ከወልቃይት እስከ መተከል በአማራ ሕዝብ ላይ የዘር ፍጅት ያልተፈፀመበት ቦታ የለም።
ይህን አማራ ተኮር ጥቃት የተቃዋሚ ድርጅት መሪ ነን የሚሉት ብቻ ሳይሆኑ የቀድሞው የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ሳይቀር ተፈፅሟል ብለው አምነዋል። መንግስትም አምኗል። በአማራ ላይ የዘር ፍጅት መፈፀሙ በአሁኑም በቀድሞውም ፓርላማ ታምኗል። የቀድሞው ፓርላማ የአማራ ሕዝብ በቆጠራ ሆን ተብሎ እንደጠፋ ተገልፆበታል። በቅርቡ ደግሞ የፓርላማ አባላት እያለቀሱ በአማራ ሕዝብ ላይ የተፈፀመውን የዘር ፍጅት በይፋ ተናግረዋል። የአማራን ሕዝብ ምረጠኝ እያለ የሚቀሰቅሰው ኢዜማ መሪ ግን የዘር ፍጅት እንዳልተፈፀመ ደረታቸውን ነፍተው ተከራክረዋል።
ለኢዜማው መሪ መተከል፣ ኦሮሚያ፣ ጉራፈርዳ፣ ወልቃይት፣ ራያ፣ ደራና ሌሎችም ቦታዎች የተፈፀመው ግጭት ነው። ከጉራፈርዳ ያ ሁሉ ሕዝብ ተፈጅቶ፣ ቀሪው ሲፈናቀል ግጭት ነበር ማለት ነው። የኢዜማው መሪ ግጭት አድርገው የቆጠሩትን ግን አፈናቃዮቹም ግጭት አላሉትም። እነ ሽፈራው ሽጉጤ ተጋጩን አላሉም። “ነፍጠኛ ዛፍ ቆረጠብን” ብለው ነው የዘር ፍጅት ሰበብ የፈለጉለት፣ የተናገሩትም ይህንኑ ነው። ትህነግ ወልቃይትና ራያ ላይ ያን ሁሉ ፍጅት ሲፈፅም ግጭት ነው አላለም። አማራ ናቸው ነው ያለው። ኦነግ ነፍጠኛ ናቸው ነው ያለው። ገዳዮቹ ያላስተባበሉትን እነ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ሊያስተባብሉ መጡ። በእርግጥ ከአሁን ቀደምም ፕሮፌሰር ብርሃኑ አማራን “መጤ፣ ሰፋሪ” ብለው ተናግረዋል። አሁንም ፍጅት አልተፈፀመም ብለው ለገዳዮች ጥብቅና ለሕዝብ ክህደትን አሳይተዋል። የኢዜማው መሪ የአማራን ሕዝብ ሌላው ለዘር ፍጅት ለማመቻቸት በሚፈርጁበት ቃል ፈርጀውታል። በተደጋጋሚ። አሁን ደግሞ የወቅቱ ገዥዎች ሳይቀር ያመኑትን የዘር ፍጅት አልተፈፀመም ብለዋል። ጨፍጫፊዎቹ ያልካዱትን ለጨፍጫፊዎቹ ክደው ተከራክረዋል!
የአማራ ሕዝብ ለአመታት ያሳለፈውን በደል የሚክድበትን፣ ለገዳዮቹ ጥብቅና የሚቆምን ድርጅት ሊመርጥ አይችልም። ሊመርጥ አይገባውም።