>
5:21 pm - Thursday July 21, 9577

ከአገዛዙ ቁንጮ እንኳን ፍጹምነትን ‹ቸር› አምባገነንነትን የጠበቀ የለም! (ከይኄይስ እውነቱ)

ከአገዛዙ ቁንጮ እንኳን ፍጹምነትን ‹ቸር› አምባገነንነትን የጠበቀ የለም!

ከይኄይስ እውነቱ


የአገሬ ሰው ጽድቁ ቀርቶብኝ በቅጡ በኰነነኝ ይላል፡፡ በክርስትና/መንፈሳዊ አስተምሕሮ ካልሆነ በቀር ከሰው ፍጹምነትን የሚጠብቅ ማንም ሰው ጤነኛ አይመስለኝም፡፡ የእግዚአብሔር ሰዎች – ቅዱሳን – ሲበቁ ወደ ፍጹምነት ማዕርግ ይደርሳሉ፡፡ አምላካቸውን መስለው አምላካቸውን አኽለው ይገኛሉ፡፡ ባለቤቱ ራሱ በርእሰ መጻሕፍቱ ፍጹም እምነት ካላችሁ እኔ የምሠራውን ብቻ ሳይሆን ከዛም በላይ ትሠራላችሁ ብሎ በተናገረው ሕያው ቃሉ መሠረት፡፡ ባንፃሩም ሰውን እንደ ፈጣሪ የሚያመልኩ ሊያውም ቀጣፊ ፖለቲከኛን አምላኪዎች ካልሆኑ በቀር ባለ አእምሮ የሆነ ሁሉ ከዓለማዊ ሰው ፍጹምነትን አይጠብቅም፡፡ እነዚህ ሰው አምላኪዎች ደግሞ እንጨት ጠርበው ድንጋይ አለዝበው ከሚያምኑ አረማውያን ልዩነት የላቸውም፡፡ 

አንዳንዶች በሐሳዊ ፍቅረ ሀገር ስም እየነገዳችሁ ውስጣችሁ ግን አፅራረ ኢትዮጵያ ወ  ሕዝባ የሆናችሁ፣ በአካልም በመንፈስም ርቃችሁ በሕዝብ ቁስል ላይ እንጨት የምትሰነቅሩ አድር ባዮች ሰውን ባታፍሩም እምነት ካላችሁ ፈጣሪን፤ አልቦ አምላክ ካላችሁ ደግሞ ታናሹ አምላክ የሚባለውን ሕሊናችሁን ብታዳምጡ መልካም በሆነ ነበር፡፡ ሕሊና የሚባለው ትክክለኛውን ከስህተቱ የምንለይበት፣ እሳቤአችንን እና ድርጊታችንን የሚገዛው ረቂቅ የሞራል ኮምፓስ በሕማም/ደዌ ካልጠፋ በቀር ካዳመጥነው በማንአለብኝነትና በግዴለሽነት አገርንና ሕዝብን የሚጎዳ ቃላትን በዘፈቀደ አንወረውርም ነበር፡፡ ባለንበት ጊዜ ግን አድርባይነት የባሕርይ ገንዘብ እስኪመስል የጊዜአቸን መገለጫ ሆኖ ጥቂት በማይባሉ ሰዎች ላይ የሚስተዋል ክፉ ደዌ ሆኗል፡፡ እንደነዚህ ዓይነቱ ሰዎች ከሕሊናቸው ለመፋታት ብዙ የሚቸገሩ አይመስልም፡፡

አገዛዞች ሲፈራረቁባት የኖረችው ኢትዮጵያ በተለይም ባለፉት ግማሽ ምእት ዓመታት ትክክለኛውን የመንግሥት ባሕርይ የያዘ ሥርዓት አልነበራትም፤አሁንም የላትም፡፡ ስለሆነም ‹መንግሥትም ሆነ መሪ› የሚባሉት አጠራሮች በዘልማድ የሚነገሩ እንጂ በነዚህ ጊዜያት ኢትዮጵያ የመንግሥትን እና የመሪን ባሕርይ የያዘ ተቋም ወይም ግለሰብ ኖሯት አይደለም፡፡ መንግሥትና መሪ ባለበትም አገር ከመሪው ፍጹምነትን የሚጠብቅ አገር/ሕዝብ በዓለም ላይ የለም፤ አይኖርምም፡፡ ይነስም ይብዛም ከሸፍጥና ከሐሰት የጸዳ ፖለቲካ የለምና፡፡ በዚህ አስተያየትም ውስጥ ‹መንግሥትና መሪ› የሚሉትን ቃላት ለአገዛዙ ስንጠቀም በገለጽነው እሳቤ ነው፡፡

ለመሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ አረመኔው ዐቢይ ከሚገዛው አፓርታይዳዊ የጐሣ ሥርዓት ፍጹምነትን/እንከን የለሽነትን ነው የጠበቀው? መሠረታዊ የሆኑትን በአገር አጥፊ የጐሣ ‹ሕገ መንግሥት› የተደገፉትን መዋቅራዊና ሥርዓታዊ አንኳር አገራዊ ችግሮች ለጊዜው ወደ ጎን እናድርግና ሕዝብና አገርን በዕድገትና ልማት ጎዳና መምራት በአገዛዝ ሥርዓት (ቢያንስ ‹ቸር/ለጋስ› አምባገነን ካልሆነ) ቅንጦት ነው፤መንግሥተ ሕዝብ (ዴሞክራሲ) እንዲሰፍን መጠየቅ፣ሰብአዊ መብቶችን እና ነፃነትን ማክበር ደግሞ ለበለጠ ምክንያት እዬዬም ሲደላ በመሆኑ እንተወውና አብዛኛው ሕዝባችን ምን እያለ ነው? ዛሬ ሰላም ውሎ ሰላም የሚያድር የኢትዮጵያ ክፍለ ሀገር አለ? 

የአገዛዞች ግፍና በደል ገፈት ቀማሽ እንደሆነ፣ በአገዛዞች እንደተሳደደና ባገሩ ባይተዋር እንደተደረገ፣ አገዛዞች በፈጠሩት ምስቅልቅል ውስጥ እንዳለፈና አሁንም በውስጡ እየኖረ እንዳለ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ተሐዝቦቴን በጥቂቱ ለማነሣሣት እወዳለሁ፡፡

 • ዛሬ ሕዝባችን አገዛዙን እየጠየቀ ያለው አትግደለን/አታስገድለን፣ ሕግና ሥርዓት አስከብርልን፣ ዕትብታችን ከተቀበረበት÷ ከተወለድንበት÷ ካደግንበት እና ከምንኖርበት ማናቸውም የኢትዮጵያ ግዛት አታፈናቅለን፣ ቤት ንብረታችንን አታውድምብን/አታስወድምብን፤ በሕይወት የመኖር መብታችን/ዋስትናችን ይጠበቅልን በሚል እየጮኸ ይገኛል፤አገዛዙ በኅቡዕ እና በገሃድ ኢ-መደበኛ አሸባሪ ኃይሎችን (‹ኦሕዴድ ሸኔ›) እና መደበኛ ኃይሎችን (የጐሣ ፖሊስ እና መከላከያ ኃይል) አሰማርቶ በድርጊትና በዳተኝነት ሰላማዊና ያልታጠቀ ሕዝብ በነገዱና በእምነቱ ማንነት ምክንያት በማያባራ ሁናቴ የዘር ማጥፋት፣ በሰብአዊነት ላይ የተቃጡ እና የጦር ወንጀሎች እየተፈጸሙበት ይገኛል፡፡ ይሄ ፀሐይ የሞቀው ዓለም ያወቀው ኢትዮጵያ ምድር ላይ ያለ ጽድቅና የዕለት ተዕለት ዜና ነው፤ በአገራችን መንግሥት ካለ፣ ከአንድ መንግሥት የሚጠበቀውን ዝቅተኛውንና የተለመደ የወትሮ የአገርን ሰላምና የሕዝብን ደኅንነት የማስከበር ተግባሩን (conventional functions) ካልተወጣ መንግሥት የሚለው ስያሜ ሊሰጠውም አይገባም፡፡ ይህንን ለማድረግ ፍላጎትም ሆነ ብቃት ከሌለው መንግሥት ለምን ያስፈልጋል? ይህ የህልውና ጥያቄ ፍጹምነትን መጠበቅ ይሆን?
 •  ዛሬ አገዛዙ በሚከተለው ጐሣን መሠረት ያደረገ ሥርዓትና ፖሊሲ ምክንያት፣ ለዜጎች ባለው ደንታ ቢስነትና በጎ መካር በማጣት ወይም መልካም ምክሮችን ባለመቀበል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቻችን ከቤት ንብረታቸው መፈናቀል ብቻ ሳይሆን በከፍተኛ ቀጠና (ሀገር አቀፍ ረሀብ/ችጋር) ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ለአገር የሚተርፈው አርሶ አደር በተፈጥሮ ሳይሆን በሰው ሠራሽ አደጋ (መንግሥታዊ አሸባሪዎች) ምክንያት ሰብሉ ተቃጥሎበት ለረሃብ ለልመና ተዳርጓል፤ ሆን ብላችሁ እያፈናቀላችሁ በቀጠና አትፍጁኝ ብሎ መጠየቅ ከአገዛዙ ፍጹምነትን መጠበቅ ነው?
 • ዛሬ በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች ዜጎች የዘር ጥላቻንና መግደልን ብቻ ሙያ አድርጎ ‹በሰለጠነ› መንግሥታዊ የፖሊስ ኃይል እንደ እባብ ይቀጠቀጣሉ፤ ይገደላሉ፡፡ ኅቡዕ ገዳይ ቡድን በማሰማራትም የፖለቲካ ግድያዎች (‹ነፃ ርምጃዎች›) ተበራክተዋል፤ ዜጎች ለፍርድ ሳይቀርቡ እየታፈሱና እየተደበደቡ በወህኒ ቤቶች ታጉረው ይገኛሉ፡፡ በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት በግፍ የታሰሩ ሰዎች ጉዳይ በመደበኛ ፍርድ ቤት ሳይሆን ለፖለቲካ ዓላማ በተደራጁ ኮሚቴዎች አማካይነት ፍርድ የሚሰጥበት ሥርዓተ አልበኝነት ነግሧል፡፡ ታዲያ ዳኝነት የማግኘት መብታችን ይከበር፤ የሕግ የበላይነት ይስፈን ብሎ መጠየቅ ፍጹምነትን መጠበቅ ይሆን? 
 • ላገዛዙ ባደሩ ኃይሎች በነገድ ማንነታቸውና በእምነታቸው በፍጹም ጭካኔ ለተጨፈጨፉና እንደ ቆሻሻ በግሬደር ተዝቀው ባንድ ጉድጓድ ለተጣሉ ወገኖች እንደ አገር ‹መሪ› እና በሰብአዊነት ጭምር ቢያንስ እልቂቱ በተፈጸመበት ቦታ ተገኝቶ እንዲያጽናና፣ ሥርዓት ያለው ቀብር እንዲያገኙ፣ ለተጎጂ ቤተሰቦች አጋርነትን እንዲገልጽ፣ በተቻለ መጠን እንዲካሡ፣ ሕዝብንና የውጭ ዕርዳታንም አስተባብሮ የተፈናቀሉት መልሶ እንዲቋቋሙ፣ ሐዘኔታውን እንዲገልጽና የሐዘን ቀን እንዲታወጅ፣ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ እና በዘር ፍጅቱ ተጠያቂ የሆኑ ግለሰቦችና ቡድኖች ጉዳይ በገለልተኛ አካል ተጣርቶ ለፍርድ እንዲቀርቡ መጠየቅ ከአገዛዙ ዐቅም በላይ የሆነ ፍጹምነትን መጠበቅ ይሆን? 
 • ዛሬ በመንግሥት መ/ቤቶችና ድርጅቶች እንዲሁም ት/ቤቶች ውስጥ ዜጎች በማንነታቸው ከሥራና ኃላፊነት እየተነሡ በተረኞች እንዲተኩ የሚደረግበት አሠራር በይፋ እየተፈጸመ ነው፡፡ የሥራ ዋስትና በችሎታና በብቃት ሳይሆን በዘር ማንነት የሚሰጥ ችሮታ ሆኗል፡፡ መተዳደሪያዬ የሥራ ዋስትናዬ ይከበርልኝ ብሎ አገዛዙን መጠየቅ ፍጹምነትን መጠበቅ ነው? 
 • ዛሬ ከአንዱ የኢትዮጵያ ክፍለ ሀገር ተጕዞ ወደ ርእሰ ከተማችን አዲስ አበባ ከመግባት ወደ ጎረቤት አገር መሄድ የሚቀል ይመስላል፡፡ የአገዛዙ ካድሬዎች ባደባባይ ወጥተው ‹ፊንፊኔ› ምን ሊያደርግ ይመጣል? ‹ድፋው› እያሉ ለከት በሌለው ትእቢትና ጥላቻ ተሞልተው ሲነገሩ ይሰማል፡፡ በዚህም ምክንያት ቊጥራቸው ቀላል የማይባል ዜጎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በሰላም ወጥቶ የመግባትና ወደምንፈልግበት የአገራችን ክፍል የመንቀሳቀስ መብታችን ይከበርልን ብሎ መጠየቅ ከአገዛዙ ፍጹምነትን መጠበቅ ነው ብሎ የሚከራከር ያለ አይመስለኝም፡፡
 • በራሳችሁ የማስመሰያ ‹ሕገ መንግሥት› መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም ቢልም ባለፉት ሦስት ዓመታት የኢትዮጵያ ርትዕት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አገልጋዮች ካህናት፣ ምእመናን ላይ እልቂት፤ ቅርሶቿና ሕንፃ ቤተክርስቲያን ላይ ከፍተኛ ውድመት እየደረሰ ይገኛል፡፡ በቤተክህነት አስተዳደሯም ውስጥ አገዛዙ ካድሬዎቹንና የደኅንነት ሠራተኞቹን በማሰማራት ከፍተኛ ጣልቃ ገብነት በመፈጸም እጅግ አሳፋሪና ወራዳ በሆነ ተግባር ተጠምዶ ይገኛል፡፡ ከዚህም አልፎ በመዲናችን እና በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍላተ ሀገራት የሚገኙ የቤተክርስቲያኒቱን ሕጋዊ የአምልኮ ስፍራዎች በመቀማትና በዓላት እንዳይከበሩ እንቅፋት በመፍጠር ላይ ይገኛል፡፡ የቤተክርስቲያኒቱ የውስጥ ችግር እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የአገዛዙን ዓይን ያወጣ ጣልቃ ገብነት በመቃወም እጅህን ከቤተክርስቲያናችን ላይ አንሣ ማለቱ ፍጹምነትን መጠበቅ ነው የሚል ወገን ካለ የአእምሮውን ጤንነት ይመርምር፡፡ 
 • ለኢትዮጵያ ታሪክ እንግዳ በሆነ መልኩ የሱዳን ወራሪ ኃይል (ባገዛዙ ፈቃድ) ድንበራችንን ወደ 50 ኪሜ የሚጠጋ ጥሶ ገብቶ ወረራ ሲፈጽም፣ ዜጎችን ሲገድል፣ የኢትዮጵያ ገበሬዎችን እርሻ ሲያቃጥልና የባለሀብቶችን ንብረት ሲያወድም ዝም ብሎ በመመልከቱ ሉዐላዊ ግዛታችን በባዕድ ኃይል ተደፍሯል፤ አገዛዙ የአገር ዳር ድንበር ያስከብር÷ ዜጎቻችንንም ይታደግ ብሎ ተገቢ ጥያቄ ማቅረብ ፍጹምነትን መጠበቅ ነው?
 • አገራዊ ሀብት (የጉምሩክ፣ የኢትዮ-ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ወዘተ.) ተረኛ በሆኑ የአገዛዙ ባለሥልጣናት ሲዘረፍ፣ በመሬት ወረራ በሌሎችም የተፈጥሮ ሀብቶች ቅጥ ያጣ ንቅዘት ሲፈጸም፣ ባንፃሩም ዜጎች አገዛዝ ወለድ በሆነና በስግብግብ ነጋዴዎች ምክንያት የኑሮ ውድነቱ ጣራ ሲነካባቸው ይህ ትክክል አይደለም ብለው መጠየቃቸው በየትኛውም መመዘኛ ፍጹምነትን መጠበቅ ተደርጎ ሊታይ አይችልም፡፡ 
 • በውስጥ አገርንና ሕዝብ ባግባቡ ለመምራት ያልቻለ፣ በውጭ በዲፕሎማሲና በዓለም አቀፍ ግንኙነት ኢትዮጵያን ያዋረደ አገዛዝ ክሽፈቱን/ደካማነቱን የሉዐላዊነትን ካርድ በመምዘዝ ሊሸፍን ቢሯሯጥም ከካድሬዎቹ፣ አድባር ተከታዮቹ እና አእምሮአቸውን ለመጠቀም ካቆሙ የዋህ ነሆለሎች በስተቀር አብዛኛው ሕዝብ የአረመኔውን ዐቢይና ወንጀለኛ ድርጅቱን አሳብ ገብቶታል፡፡ የአገር ህልውና የሕዝብን ደኅንነት አደጋ ላይ ስትጥል፣ በሕዝብ ላይ የዘር ፍጅት ስታስፈጽምና በገዛ አገራቸው ባይተዋር በማድረግ በገፍ ስታፈናቅል፣ ድንበራችንን በሱዳን ስታስደፍር (በወያኔ/ኦሕዴድ የማስመሰያ ‹ሕገ መንግሥት› ባይሆንም የሉዐላዊነት ባለቤት ሕዝብ ነው)፣ ከኤርትራ አገዛዝ ጋር የሁለት ሉዐላዊ አገራት ሳይሆን ግለሰባዊና መርህ አልባ ግንኙነት በማድረግ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ዕውቀት ውጪ የኢትዮጵያን ብሔራው ጥቅም አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ትርጕም አልባ ‹ፖሊሲ› ስትከተል፣ የሻእቢያን ወራሪ ኃይል አገራችን በማስገባት ሕዝባችንን እንዲጨፈጭፍ ስትፈቅድ፣ እኅቶቻችንን እና እናቶቻችንን በዚህ አረመኔ ኃይል ስታስደፍር፣ መላ የአዲስ አበባን ሕዝብ የሴተኛ አዳሪ ልጅ ነው የሚል ስድ አደግ ባለጌ  ለአዲስ አበባ ከተማ የምርጫ እጩ አድርገህ ስታቀርብ ወዘተ. እንጂ አንተ እና ነፍሰ ገዳይና ዘራፊ ጓዶችህ ቪዛ ስትከለከሉ አይደለም የኢትዮጵያ ሉዐላዊነት የተደፈረው፡፡ በማለት የሚቀርብ ተቃውሞ በምን ሂሳብ ነው ከአገዛዙ ፍጹምነትን መጠበቅ የሚሆነው? 
 • ወያኔና ወራሹ የዐቢይ አገዛዝ ባህል ባደረጉት የቅጥፈት አስተሳሰብ የልማት አጀንዳ የምርጫ ጊዜ ብቻ ወሬና ቅስቀሳ (ሊያውም ለውሸት ምርጫ) ሆኖ ብቅ የሚልበት ትርኢት፤ የዋሀንን በታሸገ ውኃ እና በውሎ አበል በመደለል ከተማ ሲያውኩ መዋል ? ከቤት ንብረቱ ሲያፈናቅሉትና አንጀቱን ቋጥሮ በቆጠበው ገንዘብ ያሠራውን ቤት ለተረኞች ሲያድሉ ቆይተው በ‹ምርጫ› ሰሞን ቤትና ቦታ ልናድላችሁ ነው የሚል ሰበካ ሕዝብን የመናቅ ነውረኛነት ነው፤ ስለሆነም ይህንን ሸፍጥ አቁሙ ብሎ መጠየቅ ከአገዛዙ ፍጹምነትን መጠበቅ የሚሆነው እንደ አድርባዮች ሕሊናን መሸጥ ሲቻል ብቻ ነው፡፡  
 • ባጠቃላይ አገዛዙ አገርና ሕዝብን ባግባቡ ለማስተዳደር ተስኖት የአገር ህልውናና የሕዝብ ደኅንነት ከመቼውም ጊዜ በከፋ ሁናቴ አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ ምክንያት መፍትሄው አገዛዙ ሙሉ በሙሉ የተቆጣጠረውና ውጤቱ ከወዲሁ የታወቀውን የውሸት ምርጫ (ለዚያውም በጥቂት የአገሪቱ ክፍሎች ብቻ ሊደረግ የታሰበውን) ማድረግ ሳይሆን ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች ያሳተፈ አገራዊ ጉባኤ በመጥራት ብሔራዊ ውይይት፣ ብሔራዊ መግባባት እንዲሁም የሽግግር ፍትሕ ማድረግ ነው ከገባንበት ማጥ የሚያወጣን በማለት ባገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ አገር ወዳዶች የሚያነሱትን ሃሳብ (ሥልጣን በማጭበርበር በመያዝ ዘረኝነትንና ፈላጭ ቆራጭነትን ሕጋዊ ሽፋን ሰጥቶ ለማስቀጠል በማሰብ) ማጣጣል የማያዛልቅና ኋላ አገርንና ሕዝብን በእጅጉ የሚያስከፍል ይሆናል፡፡ አገዛዙ የዚህ አገራዊ መፍትሔ አካል እንዲሆን መጠየቅ እንዴት ተብሎ ፍጹምነትን የመጠበቅ ትርጕም እንደሚሰጠው ሊገባኝ አይችልም፡፡

እላይ የዘረዘርናቸው በኢትዮጵያ ምድር ላይ አፍጠው ገጠው የሚታዩ ጽድቆች ከዐቢይ አገዛዝ ቅንነትንና እና እውነተኛነትን ብቻ የሚጠይቁ፣ ለሕዝብና አገር ቅድሚያ የሚሰጥ፣ ኃላፊነት የሚሰማውና ተጠያቂነት እንዳለበት የሚያምን፣ አገራዊ አንድነትን እና አብሮነትን የሚፈልግ ‹መንግሥትና አመራር› ዐቅም በላይ ያልሆኑ፣ ፍጹም ከመሆን ጋር አንዳች ዝምድና የሌላቸው ከማናቸውም መንግሥት የሚጠበቁ ተግባራት ናቸው፡፡  

በአንድ አገር የመጨረሻ ሥልጣን ላይ በሕዝብ ፈቃድም ይሁን በጉልበቱ የተቀመጠ ግለሰብ/ቡድን የሚለካው በጎላው ተግባሩ ነው፡፡ ለሕዝብ ደንታ የሌለውና አገር በማፍረስ የተጠመደ ኃይል ለራሱ ዝና ሲል አንዳንድ በጎ የሚመስሉ ተግባራትን ሊያከናውን ይችላል፡፡ በዚህ ረገድ ብሔራዊ ቅደም ተከተል ሳይበጅላቸው መካር በማጣት ወይም በክፉ አማካሪዎች ድጋፍ ያለተጠያቂነት የሚሠሩ አንዳንድ ‹ብልጭልጭ› ተግባራት እንደ የአገር ሀብት ውድመት የሚታዩ እንጂ ከልማት የሚቈጠሩ አይሆኑም፡፡ እነዚህ በጎ የሚመስሉ ተግባራት ግን የግለሰቡን/የቡድኑን ማንነት አይለውጡም፡፡ ለአገዛዙም መልካምነት መለኪያ ሆነው ሊቀርቡ አይችሉም፡፡ ቀዳማዊው ኢሕአዴግ (ሕወሓት) በዘመኑ የሠራቸው መሠረተ ልማቶች፣ ግንባታዎች ወዘተ. አሉ፡፡ ይህ ዘረኛና አሸባሪ ቡድን ግን የኢትዮጵያን መንበር ይዞ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት ሌት ተቀን ሲሠራ፣ የሀገርን ሀብት ዛሬ በሥልጣን ላይ ከሚገኙት አሽከሮቹና ግብረ አበሮቹ ጋር ሙልጭ አድርጎ የዘረፈና ካገርም ያሸሸ ኃይል ሲሆን፣ በውድቀቱም ኢትዮጵያዊውን የትግራይ ሕዝብ ለሰቈቃ የዳረገ፣ ይህንኑ አገር የማፍረስ ዓላማ ከሱ ለከፋውና ወልዶ ላሳደገው፣ ዘረኛና አሸባሪ (ከመምህሩ ደቀመዝሙሩ እንዲሉ) ለሆነው ለወራሹ ካልዓይ ኢሕአዴግ (ኦሕዴድ) – በግብር ስሙ ‹ብልግና› ለሚባለው – አስተላልፎ ሰጥቶ አገራችን ግቢ ነፍስ ውጪ ነፍስ ውስጥ እንድትገኝ አድርጓል፡፡ አንድ አገዛዝ በመንግሥትነት ራሱን ሰይሞ የሚያከናውናቸው ተግባራት የሚያስመሰግንበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ አገዛዙ የተጠመደው እላይ በጠቀስናቸው የጥፋት ተግባራት በመሆኑ መደበኛ ሥራውንም አልተወጣም፡፡ 

በማጠቃለያነት ለዚህ አስተያየት መነሻ የሆነኝ ‹‹ፍፁም ሰዎች በሌሉበት ምድር መሪን ፍፁም ሁን ማለት ተገቢ አይደለም›› የሚል ጽሑፍ ነው፡፡ በመሠረቱ ማንም ሰው የመሰለውን አስተያየት መያዝ፣ ያንንም በንግግርና በጽሑፍ የመግለጽ መብቱ አገዛዞች ሲፈልጉ የሚቸሩት ሳይፈልጉ የሚነፍጉት ሳይሆን ተፈጥሮአዊ በመሆኑ አከብራለሁ፡፡ በነገራችን ላይ ዘረኛው የዐቢይ አገዛዝ ባለፉት ሦስት ዓመታት ለእሱ ድጋፍ ካልሆነ በቀር ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ከመንግሥት ፈቃድ የማያስፈልገውን ዴሞክራሲያዊ መብት በአውሬ ሠራዊቱ አማካይነት በማፈን ዘልቋል፡፡ የዚያኑ ያህል ደግሞ መብትና ነፃነት ልቅ እንዳልሆነ እገነዘባለሁ፡፡ የተፈቀደ ሁሉ አይጠቅምምና፡፡ ንግግራችንም ሆነ ጽሑፋችን ኃላፊነትና ተጠያቂነት እንደሚያስከትልም ማወቅ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ 

ለማንኛውም በተጠቀሰው ጽሑፍ የቀረበው አስተያየት የአረመኔውን ዐቢይ አገዛዝ ማንነት በፍጹም የማይገልጽ፣ አስተዋይነት የጎደለው ላም ባለዋለበት ኩበት ለቀማ ዓይነት ጽሑፍ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ሰው ከአንደበቱ የሚወጣውና በጽሑፍ የሚያሰፍረው ቃል ከልቡ ሞልቶ የፈሰሰውን ነው፡፡ የዐቢይ ተዋራጅ የሆነው ሌላው ግልገል አረመኔ ሽመልስ ዐወቅኹ ብሎ በጓዳ የተናገረው ‹ማደናገርና ማሳመን› የሚለው ቆሻሻ አስተሳሰብ አካል ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ በተጠቀሰው ጽሑፍ ላይ ያቀረብሁት ጥቅል ትችት እንጂ እያንዳንዱን ነጥብ እንምዘዝ ቢባል ብዙ ያነጋግራል፤ ለዚህ ደግሞ ተጨማሪ ጊዜ ማባከን አስፈላጊ ሆኖ አልታየኝም፡፡ 

የሐዋርያት አለቃ ቅ/ጴጥሮስ አምላኩን ክርስቶስን አላውቀውም ብሎ በካደ ጊዜ ሰቃልያነ ክርስቶስ አንተ የዚህ ሰው ወገን ነህ ሲሉ በንግግሩ ዐውቀውታል፡፡ ማንነቱን መደበቅ አልቻለም፡፡ አድር ባይ፣ ባንዳ አገር ሻጮችም ከንግግራቸው ወይም ከጽሑፋቸው ይዘት ይታወቃሉ፡፡ ራሳቸውን በአስመሳይ አገር ወዳድነት፣ በአገዛዞች ሥር አልኖርኩም በማለት ቢመጻደቁም (በአገዛዞች ሥር አድርባይና የጥቅማቸው ተካፋይ ካልሆነ በቀር ማንም በፈቃዱ መገዛት/መተዳደር አይፈልግም) በንግግር ወይም በጽሑፍ የተገለጸው ሃሳባቸው ማንነታቸውን ያሳብቅባቸዋል፡፡ ጸሐፊዋ እኛ ውስጡ ሆነን ያልተረዳነውን ለእሳቸው ብቻ ወለል ብሎ የተገለጠላቸውን ምሥጢር ቢያካፍሉን ቢያንስ ጊዜአችንን እንዳናባክን ያግዙን ነበር፡፡ በመዋቲ ሰው (ለዛውም በሥልጣን ፍትወት ምክንያት እጁ በንጹሐን ደም ከተጨማለቀ ዘረኛ) ከመታመን ሁሉን ቻይ በሆነ አምላክ መደገፍ ይሻላል፡፡ ይሄ ቢቀር ቢያንስ ለሕሊና ተገዝቶ የመርህ ሰው መሆን ያስከብራል፡፡ እንኳን ጨካኝና ዘረኛ አምባገነኖች በርካታ ደገኛ ነገሥታትና መሪዎች ይህን ዓለም ተሰናብተው ወደማይቀረው ተከማችተዋል፡፡ እናስተውል!!!

Filed in: Amharic