እስሌይማን አባይ
የግብፅ ምሁራን፣ ጋዜጠኞች፣ አክቲቪስቱ፣ ወዘተ ከሳምንታት በፊት ሲነዙት የነበረው “የሀይል አማራጭ መጠቀም”፣ “ኢትዮጵያ የግድቡን 30 ሜ. የመሀሉ ኮሪደር ግንባታ ክረምት ይቀድማታልና 13.5 ቢሊዮን ዘንድሮ መሙላት አትችልም”፣ “ምዕራባዊያን ጫና ያድርጉልን” የሚሉና የመሳሰሉት ነበሩ።
የጠ.ሚ አብይን “ከ 100 በላይ ግድቦች እንገነባለን” የምትል ንግግር ተከትሎ ነገሮች በካይሮና ጭፍሮቿ ምን መልክ እንደሚይዙ መከታተል በርግጥም አስፈላጊ ነበር።
ማርሳድ እንዳስነበበው ጠ.ሚ አብይ ከመቶ በላይ እንገድባለን ማለታቸውን ተከትሎ አልሲሲ የባህር ውሃ ማጣሪያ ፕሮጀክቶች በአስቸኳይ እንዲገነቡ ትዕዛዝ ሰጥተዋል። በአሜሪካና አውሮፓ በተለይም በእንግሊዝ የጣሉት ተስፋ ፍሬ ካለማምጣቱ በተጨማሪ ቻይናም አልተስማማችላትም። አሁን ወደ አረብ ሊግና አል ቡርሃን ጋር እየተያዩ ናቸው።
በምሁራንና ልሂቃኑ በኩል የዛቻ እና የአይችሉም ወሬያቸውን ገታ አርገውታል። የካይሮ ዩኒቨርሲቲ መሁራን እንዲሁም አክቲቪስቱ እያወራ ያለው ስለ ግብፅ የጨው ማጣራት ሆነበል። በዚህም አልሲሲ ያቀደቀቸው የ desalination ፕሮጀክቶች የውሃ እጥረቱን ይተካሉ አይተኩም እየተነተኑ ናቸው።
በሌላ በኩል የአልሲሲ መንግስት በማውገዝ በስደት ከሚኖርበት ስፔን መኖሪያው የአመፅ ጥሪ አቅርቦ ነውጥ የፈጠረው ግብፃዊ ለፀረ አልሲሲ አመፅ ቀን ቆርጧል። ሙሀመድ አሊ የግድቡን ቀውስ አስታኮ የአልሲሲን መንግስት ለመጣል በ july 10 የናይል አመፅ እንዲደረግ ሰፊ ዘመቻ ላይ ነው።
ግብፅና ሱዳን ዙረው የገቡበት የአረብ ሊግ አዳራሽ በራሱ ውሃ የጠማው ሌላኛ የበሽታቸው ምልክት ነው። ከኢትዮጵያ ጥቅም ያላቸው፣ ነገር ግን እስተወሰነ ርቀት አልሲሲን “እንስማህ እስቲ” እያሉ የሚገኙት ሳዑዲና ኳታር የናይል ሞኖፖሊ ከእጇ ሊወጣ ቀናት ብቻ ለቀራት ግብፅ የሚያደርጉት ድጋፍ ከነገዋ የውሃው ባለቤት ኢትዮጵያ ጋር የሚፈጥሩትን መቃቃር ለማስላት ብዙም አይከብዳቸውም። ለትራምፕ ያልተመለሰ አቋም ኢትዮጵያ ማሳየቷን ጤነኛ የሆነ ሁሉ አይዘነጋውም። ስለ ቻይና አስር ቦታ እየረገጡ የሚገኙት ፕሬዝደንት ባይደንም ስለ ጉዳዩ ድምፅ ከመስጠት ተአቅበው አየሩን በመቃኘት ላይ ናቸው። ታዲያ አረብ ሊግ የራሱን ውሃ ጥም ወይስ የግብፅን ውሸት ይከተላል። ከባድ ነው።
ቀይ ባህር መስመሮች ላይ ፀረ ኢትዮጵያ አድማ ቢያስቡስ? እኛም ስለ ጉዳዩ ማሰባችን አይጎዳንም። ይሁንና ጉዳዩ የኤርትራ፣ የሶማሊያ፣ ጂቡቲ ወዘተ… ጉዳይ ጭምር ነውና የቀንዱ ጥልፍልፍ ኳታርን እንደማገዱ ቀላል አይሆንም።
ከሁሉም በላይ ቻይና በጅቡቲ ያላት ወደብና ጦር ሰፈር ጉዳይ አለ። ቻይና ከኢትዮጵያ የተፈራረመችውን አስታውሱ። road and belt በጋራ የሚጠበቅበት መግባቢያ ነው። ይህ ስምምነት ሀዲድ ስለ መጠበቅ አይደለም ዋና አላማው። የቻይናን የአፍሪካ ዱካ ከባላንጣ አገራት የማስጠበቅ እንጂ። የኢትዮጵያን የባህር ንግድ መስተጓጎል ከስምምነቱ አንፃር ብቻ ነጥለን ብንመለከተው በቻይና ላይ የተደረገ ትልቅ መዳፈር ተደርጎ የሚወሰድ ይሆናል። ከዚህ ባለፈም ኢራን ቀዳዳውን ልጠቀም ብላ ከች ማለቷ አይቀርም። ስለ ባህር በሩ እንዶልታለን ካሉ ማለቴ ነው። (እዚጋ ከወር በፊት ሁቲዎች ስለ ግድቡ እናሸማግል ሲሉ እናስታውሳለን። ሁቲ በኢራን ማሊያ ነበር የተናገረው። አራት ነጥብ። ከሳምንት በፊትም የኢራኑ መሪ ከኢትዮጵያ ይበልጥ እንወዳጅ ብለው ነበር። መነሾው ይታወቃል። ሁሌም የሳኡዲን ተቃራኒ እያነፈነፉ ናቸዋ።
የቱርክ በቀይ ባህር ያላት ወታደራዊ መስፋፋት እዚጋ በትልቁ እንደሚመዘንም ግልፅ ነው።
ኢትዮጵያን ከጎረቤት የመነጠል እና ዲፕሎማሲያችንን እናቋርጥ ቢሉስ? የመጀመሪያው ጎረቤት የመነጠል ሐሳብ ቢነሳ ጂቡቲን ሶማሊያን ኬንያንና ኤርትራን እንዴት አድርገው። ምን የተሻለ ነገር አቅርበው ሊያሳምኑ። አሁንም ችግር ነው። ሁለተኛ ዲፕሎማሲያዊ አጥር ቢያስቡም የሚያጡት ያመዝናልና ይሄም የቸገረ ነገር ነው።
ነገሮች የዓባይ አቢዮት መገለጫ ናቸው። ኢትዮጵያዊው የዓባይ አቢዮት ከሰሜን እስከ ምስራቅ አፍሪካ ከምዕራብ እስከ ምስራቅ እንዲሁም እስከ ባህረ ሰላጤው የሚጋረፍ ነበልባል ሆኗል። ኢትዮጵያ ለወላፈኑ ፊት ባትሰጠውም ስንቱ አገር አስንት አገር ተኳረፈ? ከስንቱ ተዋደደ? ይህ አዙሪት ስንቴ ተደጋገመ? አዙሪቱ እነሱን አዙሮ ከነበሩበት እየደጋገመ ሲያደርሳቸው ኢትዮጵያ እንደፀናች መዝለቋ በርግጥም ጩኸታቸው የዓባይ አብዮት በሙሊቱ እስኪደመደም ድረስ ተጠባቂ የበሽታቸው ምልክት ስለሆነ ነው ለማለት ያስችላል።
የአፍሪካ ቀንድ በዓባይ አቢዮት ላይ የሃያላን ትንቅንቅ ተጨምሮበት ነገሮች ይበልጥ ተወሳስበዋል። ነገሮች ተለዋዋጭ ናቸው። በከፍተኛ ፍጥነት። በአቋም አለመፅናት በተለይም ለአረቦቹ ባህላቸው የነበረም ነው። እንኳን አረብ ሊግ ጆ ባይደን እንኳ በኢትዮጵያ አቋማቸው ስንቴ ወለም ዘለም እንዳሉ ልብ እንበል።
እናም በዚህ ውስብስብና ተለዋዋጭ ጂኦ-ፖለቲካ ውስጥ ጨዋታውን በማጤን፣ ሊከሰት የሚችለውን ገምተን የመፍትሄ አማራጮችን አስቀድመን እየቀየስን በፅናት መራመድ ይሆናል መንገዳችን። ያኔ ለአፍሪካም የሚተርፍ የፅናት ብርሃናችን ወገግ ይላል።
🇪🇹 ኢ ት ዮ ጵ ያ ታሸንፋለች