አባይን ከግብጽ ቅኝ ግዛት ማላቀቅ፤ የአገር ህልውና ብቻ ሳይሆን የሰብአዊ መብቶችም ጉዳይ ነው…!!!
ያሬድ ሀይለማርያም
ኢትዮጵያ እጅግ በድህነት ከሚማቅቁ የአለም አገራት መካከል አንዷ ናት። የከፋ ድህነት ደግሞ የመሰረታዊ መብቶች ጸር ነው። የከፋ ድህነት ባለበት ስፍራ ሁሉ የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ እና ባህላዊ መብቶችን የያዘውን አለም አቀፍ ድንጋጌ ውስጥ ያሉ መሠረታዊ መብቶችን ብቻ ሳይሆን የሲቪክ እና የፖለቲካ መብቶችና ነጻነቶችንም ማክበር እና ማስከበር ትልቅ ፈተና ይሆናል። ከዛ ባለፈ ድህነት በራሱ ብዙ ነጻነቶቻችንን እና የሰውነት ጸጋዎችን ይገፋል።
ኢትዮጵያ ረዘም ላሉ ዘመናት ክፉና አፋኝ በሆኑ ሥርዓቶች ውስጥ መቆየቷ ያላትን አንጡራ ሀብት እንዳትጠቀም አድርጓታል። ብዙ የጭለማ ዘመናትን አሳልፋለችም። ዛሬ ከኢትዮጵያ ውስጥ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ክፉ አስተዳደርን እና ድህነትን ለማጥፋት የሚፈልግ ሃይል ሁሉ አባይን ከግብጽ ቅኝት ግዛት ለማላቀቅ በሚደረገው እርብርብ ሊሳተፍ እና ከኢትዮጵያ ጎን ሊቆም ይገባል።
አባይን ከቅኝ ግዛት ነጻ ማውጣት መቶ ሚሊዮን የኢትዮጵያዊያን ከድህነት ነጻ ለማውጣት የመጀመሪያውና ትልቁ እርምጃ ይሆናል። ከድህነት የተላቀቀ ሕዝብ ሌሎቹ መብቶቹን እና ነጻነቱን ለማስከበር አቅም ያገኛል። ህዳሴ ግድብ ለድሀ ኢትዮጵያዊያን የመብላት፣ የመጠጣት፣ ህክምና የማግኘት፣ የመኖሪያ ቤት የማግኘት እና የሌሎች መሰረታዊ መብቶች መሟላት እንደሆነ ለመላው አለም አስረግጠን ማስረዳት የሁላችንም ግዴታ ይመስለኛል። የቤታችንን ስንክ ሳር እና የአገዛዞቹን አመል እየታገልን በአባይ ጉዳይ በአንድ ግንባር መሰለፍ የግድ የሚልበት ጊዜ ላይ የደረስን ይመስለኛል። የአረቡ አለም በተቃርኖ ከግብጽ ጋር በይፋ ግንባር ፈጥሮ ቆሟል። ሌላውን አፍሪቃዊ ከኛ ጎን ማሰለፍ መቻል የግድ ይላል።
ለእኔ ህዳሴ ግድብ የሰብአዊ መብት ጉዳይ ነው። ለእናንተስ?