ዝክረ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ (፪)
በአማን ነጸረ
#ምስጋና፡- ‹‹ሜይን ስትሪም›› ከሚባለው እስከ ማኅበራዊ ሚዲያ፣ በንባብ ከሚያውቋቸው ታዳጊ ወጣቶች እስከ ክብርት ፕሬዝዳንታችን ወ/ሮ ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ለፕ/ር ጌታቸው ድካምና አስተዋጽኦ የተሰጠውን ዕውቅና ማድነቅ ይገባል፡፡ ፕሮፌሰርን የሚቀርቧቸውና የሚያውቋቸው በርካቶችና ታላላቆች ናቸው፡፡ በዚያ ሰልፍ ውስጥ እኔ በአመጣጥም በቁመናም የመጨረሻው ነኝ፡፡ ስቀርባቸው እንደ ቤተ ክርስቲያን ልጅ፣ እንደዚህ ዘመን ወጣት፣ እንደ ትውልዴ (የ90ዎቹ ባች መሆኔ አይረሳብኝና) ወኪል ሆኜ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ከእርሳቸው አግኝቼ ባጋራሁት ተሞክሮ ላይ የፌስቡክ ጓደኞቼ ለፕ/ር ጌታቸው ሲሰጡ ባየሁት ክብር የተነሣ በትውልዴ አባት አክባሪነት መኩራቴን አልደብቅም!
—
#ደቂቀ_እስጢፋኖስ፡- ከፕ/ር ጌታቸው ጋራ ከተነጋገርንባቸው ጉዳዮች መካከል ትውልዴ (በተለይ ኦርቶዶክሳዊው ትውልድ) ላይ ብዥታ ፈጥረዋል የምላቸው የደቂቀ እስጢፋኖስና ሰሞኑን ደግሞ በነገረ ክርስቶስ ጥናታቸው ካሰባሰቧቸው መዛግብት መካከል ሆን ተብሎ ትችታቸው እየተዘለለ ለአጓጉል የስሑት መንገድ መናጆነትና ቀሊላን አንባብያንን ማወናበጃነት የሚቀርበው የነገረ ቅብዓት ሐተታቸው ይገኝበታል፡፡ የቅብዓቱን ጉዳይ ከጥቅል የነገረ ክርስቶስ ጥናቶቻቸው፣ የሀገርና የነገረ ቤተ ክርስቲያን አሻራቸው ጋራ በመደምደሚያነት ለመዳሰስ አሳድረን ከደቂቀ እስጢፋኖስ ጋራ እየተያያዙ በተነሡት ነጥቦች ላይ ፕ/ር ጌታቸው ድኅረ ኅትመት የሰጡዋቸውን አስተያየቶች ከነጓዛቸው እንይ፡፡
—
#አውሮፓዊው_የኢትዮጵያ_ነገረ_ማርያም_እይታ፡- ምዕራባውያን ሚሽነሪዎች (የፕሮቴስታንትም የካቶሊክም) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በእመቤታችን ዙሪያ ያላትን አቋም የአምልኮ አድርገው ይወስዱታል፡፡ ይኸነን አመለካከት ከካቶሊካዊው ቄስ ሉቦ ማስታወሻ፣ ከፕሮቴስታንታውያኑ ሳሙኤል ጎባትና ክራምፕፍ የጉዞ ማስታወሻች መረዳት ይቻላል፡፡ ፕ/ር ጌታቸው ከዶናልድ ክሩሜ ጋራ በመሆን ባሳተሙት የአቡነ ሰላማ ሣልሳይን ታሪክና በ1846 ዓ.ም. የተካሄደውን የአምባ ጫራ (ጎንደር) ጉባኤ በሚዘክር ጥናት ‹‹ወላዲተ አምላክ ሞተት ለቤዛ ብዙኃን›› የሚሉ የእመቤታችንን ፍቅር አለቦታው የሚጠቅሱ ወገኖች ተገሥጸዋል፤ ‹‹ላቲ ይደሉ ክብር ወስብሐት ወለወልዳ አምልኮ ወስግደት – ለእርሷ ክብርና ምስጋና ለልጇም አምልኮና ስግደት ይገባል›› ከማለት ይልቅ ‹‹ዘምስለ ወልዳ አምልኮ ወስግደት – ከልጇ ጋራ አምልኮና ስግደት ይገባታል›› የሚሉ ወገኖች ቦሩ ላይ እንደ ተነቀፉ ጸሐፌ ትእዛ ገብረ ሥላሴ ወልደ አረጋይ በታሪክ ዘዳግማዊ ምኒልክ ነግረውናል፡፡ አመለካከቶቹ በካቶሊካዊው ዶ/ር አባ አየለም ተጽፎባቸዋል፡፡ ከእነዚህ አጋጣሚዎች የሚነሣው የኋላ ኋላ የሚሽነሪዎቹና የነገረ ኢትዮጵያዊ አጥኚዎቹ (Ethiopianists) ድምር መደምደሚያ ‹‹ኢትዮጵያውያን ማርያምን ያመልኳታል!›› ማለትን ጋበዘ፡፡
#አውሮፓዊውን_የኢትዮጵያ_ነገረ_ማርያም_እይታ_ የማረም_ተልእኮና_ያልታሰበው_ፈተና፡- ፕሮፌሰር ሰፊ የጥናት ጊዜያቸውን ያሳለፉት በምዕራባውያን መካከል ነው፡፡ ምዕራባውያን የነገረ ኢትዮጵያ ተመራማሪዎች በምዝበራም በማይክሮ ፊልም ቅጂም ያገኟቸውን መዛግብት በምዕራባዊ መነጽር እየመረመሩ ምዕራባዊ መደምደሚያ ላይ ይደርሳሉ፡፡ የፕሮፌሰር ተልእኮ ይኸን እይታ ማረቅ ነበረ፡፡ በዚህ ረገድ ለሀገርና ለቤተ ክርስቲያን የሠሩትን በቀጣዩ ክፍል ፍንጭ ይሰጡናል፡፡ ወደ ጉዳያችን ስንመለስ፡- ኢትዮጵያውያን ለእመቤታችን የሚሰጡትን ክብር በአምልኮ በመረዳት ‹‹የማርያም አምልኮ!› (እነርሱ Cult of Mary/Marian cult ይሉታል) ለማረም ፕሮፌሰር ጌታቸው ተደጋጋሚ አፀፋ ይሰጣሉ፡፡ የዚህ አፀፋ አዝማቻቸው ‹‹እኛ ኢትዮጵያውያን ፥ ማርያምን እናከብራታለን እንጂ አናመልካትም!›› የሚል ነበረ፡፡ ይኸን አቋም በሁሉም መጻሕፍቶቻቸው ቢጠቅሱም በደቂቀ እስጢፋኖስ ላይ ታሪኩም ስለተመቸ አጉልተውታል፡፡ (በእኔ እምነት በአገር ውስጥ የነበረችው ቤተ ክርስቲያን ያለባትን የተሐድሶዎች የ‹‹ህፀፅ ነቃሽነት›› ፈተና ባለመረዳትና የምሥራቃውያንንና የአኃት አብያተ ክርስቲያናትን ተሞክሮ ባለማካተት ጭምር) ከመስመር ወጣ ባለ መልኩ ለቁንፀላ በር ከፍተዋል፡፡ አውሮፓዊውን የኢትዮጵያዊ ነገረ ማርያም እይታ የተከላከሉት ወደኋላ (በኋላቸው ያለውን ከሚሽነሪዎች የሚገጥም እምነት ያለው ሃይማኖተ ልውጥ ኢትዮጵያዊ ዘንግተው) አፈግፍገው ነበረ ፡፡ በዚህ የተነሣ በኦርቶዶክሳውያን ዘንድ ከተራ አንባቢ እስከ መንበረ ፓትርያርክ (መልአከ ታቦር እንደ ነገሩን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስን ጨምሮ) በደቂቀ እስጢፋኖስ መግቢያና ኅዳግ ፕ/ር ጌታቸው ባኖሯቸው አንዳንድ ቃላት መሪነት መጽሐፉ በውጹኣን ቤተ ክርስቲያንን ለማጥቃት ሲባል በመቈንጸሉ ቅሬታ ተፈጥሮ ነበረ፡፡ የበኩሌን ቅሬታ በማኅበራዊ ሚዲያው ስተሻሽ ቆይቼ በመጨረሻ በመጽሐፍ ገልጫለሁ፡፡ ዘግይቶ ደግሞ የቤተ ክህነቱን አቋም ለመወከል አቅም ያላቸው መልአከ ታቦር ተሾመ ዘሪሁን በምሁራዊ ቋንቋና ዘይቤ በደቂቀ እስጢፋኖስ ዙሪያ የሚስሰማቸውን በብይን መልክ አኑረዋል፡፡ የሁለታችንንም መጽሓፍት በቅድመ ኅትመት የገመገመው ብርሃኑ አድማስ ደግሞ ደቂቀ እስጢፋኖስ ምን ያህል እንደ ተቈነፀለ ለፕ/ር ጌታቸው በአካል አግኝቶ አብራርቷል፡፡ ፕ/ር ጌታቸው ዝም አላሉም! ምላሻቸውን ሰጥተውናል፡፡
—
#ፕ/ር_ጌታቸው_ለቅሬታችን_የሰጡት_ምላሽ፡- ፕ/ር ጌታቸው፡- ለእመቤታችን የሚደረገውን ስግደት ለሥሉስ ቅዱስ ከሚደረግ የአምልኮ ስግደት ለመለየት ሲባል ከምንጠቀመው ‹‹የጸጋ ስግደት›› የሚል ቃል ይልቅ ‹‹እማኄ›› ብንለው እንደሚሻል ይጠቁማሉ፡፡ (ለትሑት እይታዬ ይቅርታ እየለመንኩ) አነጋገራቸው ‹ቃልን ከነመገለጫው በስስት ከሚያይ የሊቀ ልሳናት ምሁራዊ (scholastic) አመለካከት የመነጨ› ወይም የአብነት ሊቃውንት እንደሚሉት ‹የጉባኤ ቀለም›ን ወደ መድረክ የማምጣት ሙከራ መስሎ ይታየኛል፡፡ በእርግጥ መልአከ ታቦርም ስግደትን፡- ‘ሰጊድ፣ አስተብርኮና አድንኖ’ በማለት ካብራሩልን በኋላ ‹ሰጊድ ለፈጣሪ›፣ ‹አስተብርኮና አድንኖ ለቅዱሳን› እንደሆነ ፍትሐ ነገሥቱን ጠቅሰው በዲ/ዳንኤል አርትዖቱ በተሠራውና እነ ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ በተረጐሙት የአባ ጊዮርጊስ ፍካሬ ሃይማኖት በኩል ነግረውናል፡፡ የፕ/ር ጌታቸውን ሰጊድን ለአምልኮ ብቻ በመስጠት የጸጋ ስግደትን እማኄ በሚል ቃል የመለየት ሙከራ በዚህ ድጋፍ ፈላጊ መነጽርም ልናየው እንችላለን፡፡ ማዛለቁን ግን እንጃ! የእኛን ጨምሮ የምሥራቅ ሊቃውንት ከቃል ይልቅ ለዐውድ ይጨነቃሉ፡፡ ቅዱሳን አበው እነ ቅዱስ አትናቴዎስ፣ ቅዱስ ቄርሎስ፣ በጥቅሉ በእስክንድርያ በኩል ያሉ መተርጕማን ቃልን ሳይሆን ዐውድን ይከተላሉ፤ ከቃል መጣበቅን አያበረታቱም፡፡ በመሆኑም ‹‹ንሰግድ ለማርያም›› ካሉ በኋላ ምክንያተ ሰጊዳቸውን ‹‹በእንተ ዘወለደቶ ለመድኃኒነ … እስመ ተወልደ እምኔሃ እግዚአብሔር ፈጣሪሃ …›› እያሉ ስለሚዘረዝሩ፣ ፈጣሪ ያላት ፍጡር መሆኗን ሳይዘነጉ ‹‹ድንግል ፈጣሪዋን ወለደችው›› እያሉ ስለሚሰግዱላት ፊደል-ተኮር ተዋሥኦው በዚህ መጠን በአደባባይ ባይውል መልካም ነበረ፡፡ አልሆነም! የጉባኤው ቀለም በዐውዳዊ ትርጓሜና በአኃት አብያተ ክርስቲያናት ትውፊት ማንጸሪያነት ሳይሞረድ በአደባባይ ዋለ! ቢውልም ፕ/ር ጌታቸውን ከእናት ቤተ ክርስቲያን ነጥሎ ለማየት እስከማብቃት ያደርስ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም፡- —
በማህበራዊ ሚድያ መድረክ በሰጡን ቃል ‹‹ #አምኀ_ለእመቤቴ_ስሰጥ_ተገትሬ_አይደለም፤ ለአባቴና ለመምሀሬ ከማጎነብሰው ይበልጥ አጎምብሼ ነው … ሰይጣን አንድ መንገደኛ አግኝቶ ‹ሁሉንም አደርግልሃለሁ፤ ብቻ ማርያምን ካድ› ሲለው ‹ምን ይዞ ጉዞ› ያለው ለእኔም መልስ እንደሰጠልኝ ይሰማኛል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ብቻ ሳይሆን የምወድና የማከብረው አባቴ አደራ ነው፤›› ብለውን ነበረ፡፡ —
የአባታቸው አደራ ምን እንደሆነ በአንዳፍታ ላውጋችሁ እንደ ተነገረን የዕለት ጸሎት ማድረስ ባይችሉ ‹‹እምኵሉ ይኄይስ በሥላሴከ ተአምኖ፡ #ወበወላዲትከ_ተማኅፅኖ … ከሁሉም (ይልቅ) በሦስትነትህ ማመን፡ #በእናትህ_መማፀን_ይሻላል…›› እያለ የሚሄድ የመልክአ ኢየሱስ መሳረጊያ (መርገፍ) ጸሎት ነው፡፡ ጸሎቱን ፕ/ር እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ ከአቡነ ዘበሰማያት ጋራ ሲያደርሱት እንደ ነበረ አረጋግጠውልናል፡፡ —
የፕ/ር ጌታቸው የምንጊዜም ምርጥ ጸሐፊ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መሆኑንና አባ ጊዮርጊስ ለእመቤታችን ያለው ፍቅር ደግሞ ነጋሪ እንደማያስፈልገው ይታወቃል፡፡ በ2010 ዓ.ም. የታተመው ‹‹ስለ ግዕዝ ሥነ ጽሑፍ የተሰበሰቡ አንዳንድ ማስታወሻዎች›› የሚል መጽሐፍ ከግማሽ በላይ ስለእመቤታችን ክብር የሚዘክሩ ድርሳናትና ተአምራት የተተረጐሙበት ነው፡፡ ፕ/ር ጌታቸው የአድዋ ድል ግብዝና ለቅዱስ ጊዮርጊስ ብቻ ሳይሆን ለቅድስት ኪዳነ ምሕረትም ሊሰጥ ይገባል ሲሉ ማስረጃ ያቀረቡትም በዚህ ዕትም ነበረ፡፡ —
ስለ ታቦትና ስለመስቀል ክብር የተጻፉ የግእዝ መዛግብትን አጥንተው ከነአርትዖቱ በግእዝና በእንግሊዝኛ ያቀረቡት ጥናት ከዐርባቸው በፊት በሚታተመው (Ethiopian Studies in Honour of Amha Asfaw) መጽሐፍ ተካትቶ ይቀርባል፡፡ ውዳሴ መስቀል በዲ/ን ዳንኤል ክብረት ለመተርጐሙ ትልቁ መነሻ ፕ/ር ጌታቸው በግእዝና በእንግሊዝኛ ያሳተሙት ውዳሴ መስቀል ነውና በደቂቀ እስጢፋኖስ ያማናቸውን በእነዚህ ኅትመቶች በማመሳከር የፕ/ር አካዳሚያዊ ቁመና ከግል እምነታቸው የመለየትን ኃላፊነት ራሳችን ላይ እንጥላለን፡፡ —
እ.ኤ.አ. ኖቬምበር 25/2019 በደቂቀ እስጢፋኖስ ዙሪያ በኢሜይል ስንጻጻፍ ‹‹ #የአምላክ_እናት_ያልተከበረች_ማን_ይከበራል!›› ብለውኛል፡፡ ሕያው ምስክራቸው ነኝ! —
በአንዳፍታ ላውጋችሁ በሚካተተውና በደቂቀ እስጢፋኖስ ዙሪያ ካዩአቸውና ከሰሟቸው ልዩ ልዩ ልዩ አስተያየቶች በመነሣት ‹‹ #የደቂቀ_እስጢፋኖስ_ኦርቶዶክሳዊት_ቤተ_ ክርስቲያን›› በሚል ርእስ ባዘጋጁት ተጨማሪ መግቢያ ማሳረጊያ እንዲህ ይላሉ፡- ‹‹ማንም ደቂቀ እስጢፋኖስን ከአደነቀ ‹ከመረቁ አውጡልኝ፥ ከሥጋው ጦመኛ ነኝ› የሚለው እንዳይሆንበት የሚያደንቃቸው ሙሉ ፈለጋቸውን እየተከተለ ከሆነ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የምታቅፈው ልጇ ነው፡፡ … የደቂቀ እስጢፋኖስን ታሪክ ስጽፍ እንደተናገርኩት እመቤታችንን እናከብራታለን እንጂ አናመልካትም፡፡ ደቂቀ እስጢፋኖስ፣ ደቂቀ ኤዎስጣቴዎስ፣ ደቂቀ ተክለ ሃይማኖት ‹ሰአሊ ለነ ቅድስት› የሚሏት በዐጸደ በፍስና በዐጸደ ሥጋ ያሉ ቅዱሳንና ቅዱሳት እንደሚጸልዩልን፣ ይቅርታም እንደሚያስገኙልን ቤተ ክርስቲያናቸው ስለምታስተምር፣ ‹ከፍቁር ልጅሽ ምሕረት ጠይቂልን› ማለታቸው ነው፡፡ እኅቶሙ ለመላእክት፣ ወለቶሙ ለነቢያት፣ እሞሙ ለሐዋርያት የምትባለውን #የአምላክን_እናት_የሚያህል_ምሕረት_አስገኝ_ ቅዱስ _የለም፡፡ ሰአሊ ለነ ቅድስት፡፡ ሎቱ ስብሐት ለዓለመ ዓለም፤ አሜን ወአሜን፡፡›› —
ፕ/ር ጌታቸው ከማረፋቸው 28 ቀናት አስቀድሞ እንኳ በደቂቀ እስጢፋኖስ መጽሐፋቸውና እርሱን ተከትሎ በተሐድሶ/ፕሮቴስታንት ወገኖች በተጻፉ ጽሑፎች በቀላሉ እናጠምዳቸዋለን ብለው ያሰቡ ሰዎች ‹‹ኢየሱስን ተቀበል›› እያሉ እንደሚረብሹዋቸው ‹‹…ጴንጤ ዘመዶቼ በሃይማኖቴ ዳሕጽ ላይ ሊጥሉኝ ይፈታተኑኛል፡፡ ‹ #የኔ_ኢየሱስ_እያለኝ_የናንተን_ኢየሱስ_ አልፈልግም› እስከ ማለት ደፍሬያለሁ፡፡›› ሲሉ በላኩልኝ ጽሑፍ አጫውተውኛል፡፡
—
ይኸን እያዩ ጌታቸውን ከውጹኣን መደመር ለሕሊና ይከብዳል፡፡ ግፍም፣ ትምክሕትም፣ ኵነኔም እንዳይሆን እፈራለሁ፡፡ ለወጣት ኦርቶዶክሳውያን ያለኝ ተደጋጋሚ አስተያየት የፕ/ር ጌታቸውን እምነት ከጥናት ሥራዎቻቸው ለይታችሁ እዩላቸው የሚል ነው፡፡
—
ጸሎታ ለማርያም ወስእለታ ለነፍሰ ሣህለ ማርያም ያድኅና እመዐተ ወልዳ (ክርስትና ስማቸው በአመቤታችን ስም፣ የአንደኛዋ ልጃቸውን ስም እንዲሁ ‘ማርያም ስና’ ማለታቸውም የእመቤታችን ስም ከቤተሰባቸው ያለውን ቁርኝት ይጠቁመናል፡፡)
—
ደግመን፡- ‹‹ጸሎታ ለማርያም ወስእለታ ለነፍስ ሣህለ ማርያም ያድኅና እመዐተ ወልዳ›› እንላለን፡፡
—
ፕ/ር ጌታቸው ለሀገርና ለቤተ ክርስቲያን አበረከትኩት የሚሉትን ዋና ጭብጥና የነገረ ክርስቶስ ጥናቶቻቸውን ምጥን ዳሰሳ በቀጣዩና በመጨረሻው ክፍል ለማቀረብ እሞክራለሁ፡፡ የምወዳቸውን ሊቅ ደጋግሜ ሠልሼ ‹‹ጸሎታ ለማርያም ወስእለታ ለነፍሰ ሣህለ ማርያም ያድኅና እመዐተ ወልዳ›› ስል እርሳቸውም በዐጸደ ነፍስ እንደሚጸልዩልኝ በማመን ነው፡፡
ይቀጥላል