>

የሰኔ 15ቱ የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ግድያ ብይን ተሰጠ...!!! (ዶቼዌሌ)

የሰኔ 15ቱ የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ግድያ ብይን ተሰጠ…!!!
ዶቼዌሌ

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም  ከነ ዶ/ር አምባቸው መኮንን ግድያ ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው ክስ ተመስርቶባቸው ሲከራከሩ በቆዩ 55 ተከሳሾች ላይ ብይን ሰጠ.።
ፍርድ ቤቱ ዛሬ ከቀትር በፊት በዋለው ችሎት ብይን ከሰጣቸው ታራሚዎች መካከል  በሦስት ተከሳሾች ላይ የጥፋተኝነት ብይን ሲሰጥ፣ 20 ዎቹ  በነፃ  እንዲሰናበቱ ወስኗል። ሌሎች ቀሪ ተከሳሾች ደግሞ እንዲከላከሉ ፍርድ ቤቱ ለሐምሌ 5 ቀን 2013 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
ፍርድ ቤቱ በሌሉበት የጥፋተኝነት ብይን የሰጠው  1ኛ ተከሳሽ ሻምበል መማር ጌትነት፣ 15ኛ ተከሳሽ በላይሰው ሰፊነውና 44ኛ ተከሳሽ ልቅናው ይሁኔ ናቸው።
ተከሳሾቹ ጥፋተኛ የተባሉት በዋና ወንጀል አድራጊነት፣ በተከሰሱበት የወንጀል ድርጊት አቃቤ ህግ ባቀረባቸው የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች ድርጊቱን ስለመፈፀማቸው ፍርድ ቤቱ ማረጋገጥ በመቻሉ ነው፡፡
በሌላ በኩል ወንጀሉን ስለመፈፀማቸው የቀረበባቸው የሰውና የሰነድ ማስረጃ ጥፋተኛ ሊያስብላቸው ባለመቻሉ በሌሉበት የፍርድ ሂደታቸው ሲታይ የቆዩት አቶ ዘመነ ካሴን ጨምሮ 20 ታራሚዎች ፍርድ ቤቱ በነፃ እንዲሰናበቱ ለባህር ዳር ማረሚያ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል።ሰኔ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም  የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት ዶ/ር አምባቸው መኮንን፣ የአማራ ክልል ጠቅላይ አቃቤ ህግ  አቶ ምግባሩ ከበደና የርዕሰ መስተዳድሩ የህዝብ ተሳትፎና አደረጃጀት አማካሪ  አቶ እዘዝ ዋሴ በክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ ቤት በስብሰባ ላይ እንዳሉ መገደላቸው ይታዋሳል።
Filed in: Amharic