>

መፈንቅል ወመግረሬ ፀር...!!! ዝክረ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ (፫) - በአማን ነጸረ

መፈንቅል ወመግረሬ ፀር…!!!

ዝክረ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ (፫)

በአማን ነጸረ


ፕ/ር ጌታቸው በጥናቶቻቸው ለረጅም ጊዜና በብዛት የጻፉት በእንግሊዝኛ ነው፡፡ በአማርኛ ደጋግሜ ለመጻፍ የበቃሁት በአቶ አምሐ አስፋው እርዳታና ግፊት ነው ይላሉ፡፡ የሚደሰቱበት ትልቁ ተግባርም ምዕራባውያን ስለ ኢትዮጵያና ስለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሲያጠኑ የሚጠቀሙት መነጽር ምዕራባዊ እንዳይሆን በጎ ተጽእኖ መፍጠራቸውን ነው፡፡ የእርሳቸውን ትሑት አማርኛ ‹‹መፈንቅለ ምዕራብ ወመግረሬ ፀር›› እንለዋለን፡፡ ስቴፈን ካፕላን የፕ/ር ጌታቸውን በምዕራባውያን አጥኚዎች መካከል መከሠት  (ምጽአተ ጌታቸውን) ‹‹አርዕድ አድለቅልቅ – groundbreaking›› ይሉታል፡፡ ምጽአታቸውን መፈንቅል ወይም በቤታችን ቋንቋ መግረሬ ፀር ብንል ሲያንሳባቸው ነው፡፡ በትሑት አንደበት ካጫወቱን  ማሳያዎችን እንቈነጥራለን፡፡
ጌታው ጌታቸው ሲናዝዝቸው፡- መጻፍቶቻቸው ቀስ በስ ወጣቱ እየለመዳቸው እያነበባቸው እንደሆነ ስነግራቸው እንደቀላል እንዲህ አሉኝ፡- ‹‹በአማርኛ የምጽፋቸው ተፈላጊነት ማግኘታቸው ደስ ብሎኛል፡፡ ግን እኔ ባልጽፋቸውም ሌሎች ይጽፏቸው ነበር፡፡ #ለእኔ_ትልቅ_ደስታ_የሰጠኝ_በውጪው_ዓለም_ተመራማሪዎች_ላይ_አዎንታዊ_ተጽዕኖ_መፍጠሬ_ነው፡፡ የሚጽፉትን ከማሳተማቸው በፊት ሲያሳዩኝ ጊዜ ባይኖረኝም አላይም አልልም፡፡ #ሳነብ_ሀገርና_ቅድስት_ቤተ_ክርስቲያናችንን_የሚጎዳ_ነገር_ካገኘሁበት_በማስረጃ_ማስለወጥ_እችላለሁ፡፡›› ጌች እንዲህ የምዕራቡን አጥኚ የሚናዝዙ፣ በምዕራቡ ዓለም የነገረ ኢትዮጵያ ጥናት የነፍስ አባት ነበሩ ስንል አንገታችንን ሰገግ፡ ደረታችንን ነፋ አድርገን ነው! ስምከ ሕያው ዘኢይመውት!
መናዘዝ በበተግባር፡- አንድ ጊዜ እንጀራ ከምበላባት ሥራ ጋራ በተያያዘ ወደ ላሊበላ ስሔድ ታዋቂዋን ፈረንሳዊት የመካከለኛው ዘመን ተጠያቂት እንስት ወ/ሮ ዴራት (Maura-Merie Derat) አገኘኋት፡፡ የተቀመጥንበት መንገድ የግድ ስላገናኘን የተጓዥ ወግ ስናወጋ ማንነቷን አወቅሁ፡፡ ጥቂት ቆይቶ የጋራ አጀንዳ አገኘን፡፡ ይገርማል! ፕ/ር ጌታቸውን በሥራዎቻቸውም በአካልም ታውቃቸዋለች፡፡ ደስታ ሞትኩ፡፡ ክቡርነታቸውን እንድተገልጥልኝ ተንደፋደፍኩ፡፡ ፈረንሳይኝ በሚጫነው ቅላፄ “His works are scientific” አለችኝ፡፡ እነርሱ በአጥኚ ዐይን ሳይቲፊክ ሲሉ በጥናትና በአመክንዮ የተደገፈ ማለታቸው ነው፡፡ ይህን ወግ አንድም አላስችል ብሎኝ፡ አንድም ደስታዬን ለፕ/ር ጌታቸው ሳልጋራ ብቀር ሆዴን ስለሚቆርጠኝ ነገርኳቸው፡፡ መለሱልኝ፡፡  ‹‹ስለ ዴራት የጻፍከውም አጋጣሚ ነው፡፡ ከጓደኞቿ ጋራ ሆነው አንድ መጽሐፍ እያዘጋጁ ነው፡፡ መቅድሙን ጻፍልን ስላሉ ጽፌ የላኩላቸው በዚህ ወር (ኅዳር 2012 ዓ.ም. አካባቢ) ነው፡፡ በዚያው አጋጣሚ ከመጽሐፋቸው ውስጥ ሊለወጥ የሚገባውን ጠቁሜአቸው እየለወጡ መሆኑን ነግረውኛል፡፡ #አንዱ_ማስጠንቀቂያዬ_ስለኢትዮጵያ_ቤተ_ክርስቲያን_ሲጽፉ_በካቶሊኮች_ዐይን_እያዩ_እንዳይሆን_ነው፡፡›› ብለው መለሱልኝ፡፡ ጌች አውሮፓዊው ሥዕለ ሕሊና ላይ መፈንቅል አድርገዋል ስንል ገቢሩን ዐይተን ሰምተን ነው!
በአውሮፓውያን የኢትዮጵያ ነገረ ክርስቶስ ጥናት ላይ የተካሄደው መፈንቅል፡- እንዲህ ሆነ! ጸጎች በ1870 ዓ.ም. ቦሩ ላይ ተሳደዱ፡፡ ግማሹ በግዞት፣ ግማሹ በቅጣት፣ ግማሹ በስደት ተቀጣ፡፡ በስደት የሄዱት ወደ ሚሽነሪዎች ተጠግተው አንድ ከባድ በቀል ፈጸሙ፡፡  የጸጎች አስተምህሮ ትክክለኛውና ‹‹ተዋሕዶ›› ሊባል የሚገባው የኢትዮጵያ ነገረ ክርስቶስ መሆኑን ጻፉ፤ ተናገሩ፡፡ ታመኑ፡፡ በእነ ኢግናዚዮ (ኢኛሲዎ) ጕይዲ ተረካቸው ታመነ፡፡ ተጻፈበት፡፡ የምዕራቡ ዓለም ስለ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ያለው እይታ እንዲህ ተቀረፀ፡፡ ቀረጻው እዚያው አልቀረም፡፡ እነ ዶ/ር አባ አየለ ተክለ ሃይማኖትም ኢትዮጵያ ላይ አንፀባረቁት፡፡ ምስጋና ለእነ መልአከ ብርሃን አድማሱ ይሁንና እዚህ (በሀገር ውስጥ) በስዱዳን ጸጎች የተቃኘው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ በጸጋ አስተምህሮ የመመልከት ስሑት እይታ ተቀጨ፡፡
በአውሮፓ ግን እስከ ምጽአተ ጌታቸው ድረስ ይህ ሲሆን አልታየም፡፡ ጌች ወደ ምዕራቡ ንፈቀ ክበብ ገቡ፡፡ ተገረሙ፡፡ መፈንቅሉን ጀመሩት፡፡ Material on the Theology of Unctionists, The Faith of Unctionists, Ethiopian Heresies and Theological Controversies, Two Amharic Versions of One Essay in Defense of the Tawahido Faith, … በመሳሰሉ ሥራዎች የኢትዮጵያን ነገረ ክርስቶስ መሠረታውያን በውስጣዊ እይታ አነጠሩ፤ የምዕራቡን ዓለም በክልኤ ባሕርይ ተወዳጅተው በስሕተት የቀረፁትን ጸጎች “Crypto-Catholic” (መፍቀርያነ ካቶሊክ) ሲሉ ሚስማር መቱባቸው፡፡ ምቱ ለጊዜው በእነ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌና በመምህራኖቻቸው እነ አለቃ ክፍለ ጊዮርጊስና አለቃ ተክለ ጽን ላይ በማረፉ በሀገር ልጅነት ስሜት መሰቀቅ ቢኖርም ዒማላው በሐዲስ ጸጎች ታዝሎ ሊመጣ ያለውን ካቶሊካዊ ተረክ ሳይነሳ ባለበት መምታት ነበረ፡፡ ጌች ዒላማውን አልሳትም! ጉዳዩን በኢንሳይክሎፐዲያ ኢትዮፒካ በሰፈሩ አጫጭር የነገረ ክርስቶስ ጽሑፎችም አትሞታል! በዚህ ምክንያት ያልጐመጐሙ እንደ እንደ አባ ተስፋእዝጊ ዑቁቢት ያሉ ትውልደ ኢትዮጵያ/ኤርትራ ካቶሊካውያን አጥኚዎች ቢኖሩም አላገገሙም፡፡ የጌታቸውን አሰር የተከተለው የቀሲስ ዶ/ር መብራቱ ኪሮስ Mia-physite Christology ተጨምሮባቸዋል፡፡ ዋነኛው መግረሬ ፀር ግን እርሱ ነው – ጌታቸው ኃይሌ!
የቆጋው ኢቀኖናዊ ‹‹ሲመት›› በፕ/ር ጌታቸው ዐይን፡- አስቀድመን ፕ/ር ጌታቸው ስለ ሐዋርያዊ ቅብብሎሽና ቤተ ክርስቲያንን ሐዋርያዊት ከሚያሰኟት መሠረታውያን አንዱ ብለው በደቂቀ እስጢፋኖስ ተጨማሪ አዲስ መግቢያ ውስጥ ከጻፉልን እንቀንጭብ፡- ‹‹ ሐዋርያዊት ከሚያሰኟት አንዱ መሠረታዊ ምክንያት መሪዋ (ዋናው ጳጳስ) ክርስቶስ ለሐዋርያት የሰጠው ሥልጣን ሲያያዝ መጥቶ ለእሱ ስለደረሰው ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ይኸንን ባህል ለመጠበቅ ብዙ ፈተና አልፋለች፡፡ መንፈሳው ሥልጣን ስለሚወረስ፥ ጳጳስ ሲሞት #በሐዋርየዊት_ቤተ_ክርስቲያን_ሥርዓት_የጵጵስና_ሥልጣን_ባለው_የበላይ_ጳጳስ_እንጂ_የጵጵስና_ሥልጣን_የሌላቸው_ካህናት_ተሰብስበው_ሌላ_ጳጳስ_መሾም_አይችሉም፡፡ ስለዚህ ጳጳሳችን በሞተ ቁጥር በብዙ ጥረት #ያልተቋረጠ_ሥልጣን ካለው ከግብጹ ፓትርያርክ እናስሾም ነበረ፡፡ … የአምላክ ፈቃድ ሆኖ አሁን ቤተ ክርስቲያናችን ራሷን ችላ የራሷን ፓትርያርክ ክርስቶስ በሰጠው ሥልጣን ትሾማለች፡፡ … ግራና ቀኝ የማይለው የቤተ ክርስቲያናችን ቀጥታ (ርቱዕ) ጉዞዋ ፓትርያርኩ መምህራችን ምርኮች ምዕመናኑን ለክርስቶስ እስከሚያስረክብባት እስከ ዳግም ምጽአቱ ድረስ ይቀጥላል፡፡››
ፕ/ር ይህን መርሕ የሚጥሰውን የቆጋ ዘመዶቼን (ስለ ቅብዓቶች ስንነጋር እኔ ‹‹ዘመዶቼ›› ስለምል እርሳቸውም ‹‹ዘመዶችህ›› እያሉ ይመልሱልኛል) ድርጊት ስንግራቸው የመለሱልኝ መልስ ‹‹ #የቅብዓቶች_ነገር_እብደት_ነው፡፡ … እኔም (ሰ)ሞኑን ጤና ስላጣሁ ተቸግሬ እንጂ ነው እንጂ ልጽፍባቸው እፍልጋለሁ›› ብለው ነበረ፡፡ ዶክትሪናዊ ንባቦቻውን በጽንዐ ተዋሕዶ ዝግጅት ወቅት አጋርተውኛል፡፡ አረብኛና ግእዙን አቀናጅተው ያጠኑትና ካቶሊካውያን አጥኚዎች ለጸጋ እንደተወሰነ አድርገው ሲቆጥሩት የኖሩትን፣ ነገር ግን በተግባር ጸጎችና ቅብዓቶች የተወገዙበትን የ1755/6 የካይላ ሜዳ ጉባኤ ጥናት ብለምናቸውም ሳይታተም ረቂቅ መስጠት ያልበሰለ ወጥ እንደማቅረብ መሆኑን ነግረው ሽታው እያወደኝ እንደቆይ ከነገሩኝ በኋላ መደምደሚያው ግን ጸጎችና ቅብዓቶች የተወገዙበት መሆኑን አረጋግጠውልኛል፡፡ በጽንዐ ተዋሕዶ ገጽ 249፣ ኅዳግ ቁጥር 638 ቃላቸውን አኑሬያለሁ፡፡
ሰሞኑን ከጥናታቸው ውስጥ በስመ አቡነ ማርቆስ የተዘጋጀውን ጽሑፍ እንደወረደ ካኖሩ በኋላ ጽሑፉ በመፍቀሬ ቅብዓቱ አባ ወልደ ትንሣኤ አማካይነት በጳጳሱ ስም የተዘጋጀ፣ ዝግጅቱ በቅብዓቱ ዐፄ ቴዎፍሎስ ዘመን ሆኖ ሳለ በተዋሕዶው ዐፄ ተክለ ሃይማኖት እንደተዘጋጀ ተደርጎ መረቀቁን፣ ጳጳሱ አቡነ ማርቆስ መፍቀሬ ተዋሕዶ እንጂ የቅብዓት አስተምህሮ አራማጅ እንዳልነበሩ በእንግሊዝኛ ያኖሩት ትችት እየተዘለለ ክቡርነታቸውን ባልዋሉበት ለማዋል ይሞከራል፡፡ ስሕተት ነው! ምዕላዳቱን በኮፕት ከተመዘገበ የዜና ጳጳሳት መዝገብና ከዜና መዋዕሎች ጋራ እያናበቡ ማየት መልካም ነው፤ ከቁንፅልነትም ይታደጋል፤ በተለይም ሰውን ባልዋለበት ከማዋል ያድናል፡፡
ፕ/ር ጌታቸው ስለቤተክርስቲያን ወቅታዊ ሁኔታ፡- ‹‹ #የቤተ_ክርስቲያናችን_ደኅንነት_ሁል_ጊዜም_ያሳስበኛል፡፡ የሚቡዋጨቁዋት እንደበዙ ለሁላችን ግልጽ ነው፡፡››
የሚገርመኝ፡- ፕ/ር ጌታቸው ስለቤተ ክርስቲያን ሲናገር ራቅ አድርገው በገለልተኛ አንደበት ‹‹ቤተ ክርስቲያን›› ከማለት ይልቅ በባለቤትነት አነጋገር ‹‹ #ቤተ_ክርስቲያናችን›› ማለት ይወዳሉ፡፡
እንዳንሳሳት፡- ፕ/ር ጌታቸው የሐዲስ ኪዳን ትርጓሜን የተማሩት ከሊቀ ጳጳስና ከፓትርያርክ ነው፡፡ በኢዮጵያ የሐዲስ ኪዳን መምህራቸው ቀድሞ ሊቀ ሊቃውንት ይባሉ የነበሩትና በጳውሎስ መልእክታት ትርጓሜ የገነኑት ብፁዕ #አቡነ_ጴጥሮስ ሲሆኑ በግብፅ ደግሞ የሐዲስ ኪዳን ትርጓሜ መምህራቸው ብፁዕ ወቅዱስ #አቡነ_ሺኖዳ ነበሩ፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን በኦሪየንታል አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤያትና በሌሎችም ዓለም አቀፋዊ ስብሰባዎች እየወከሉ በተደጋጋሚ ቀርበዋል፡፡ Ethiopian Liturgical Christology የሚል ጥናትም በጉባኤ አቅርበዋል፡፡ ስለ ሃይማኖት ሲጽፉ የተራ ምዕመን ጽሕፈት መስሎን እንዳንሳሳት! ለማለት ነው፡፡ ስሕተት ወደሌለበት ዓለም የሄዱትን አባት ነፍስ ይማርልን፡፡
በዝየ ተፈጸመ ዝክረ ስሙ ለአብ ጌታቸው ኃይሌ ዘወእቱ ገንጳሌ ሕሊናሆሙ ወግብሮሙ ለጠቢባነ አፍርንጅ እለ የሐውሩ ግድመ ግድመ በምዕራብ ወምሥራቅ፡ ወልታ ጽድቅ ወመድፈነ ፀር ለኵልነ ደቂቀ ቤቱ፡፡ እግዚኦ አእርፍ ነፍሰ ገብርከ ሣሕለ ማርያም፡፡ አሜን፡፡
Filed in: Amharic