>

ባሌን ጎዳሁ ብላ ……...የህወሃታውያኑ ነገር...!!! (ብንያም ሀይሉ)

ባሌን ጎዳሁ ብላ ………የህወሃታውያኑ ነገር…!!!

ብንያም ሀይሉ

*… ዛሬ በርካታ የትግራይ ወጣቶች ስለ ደርግ መውደቅ ያላቸው ስእል በህወሃት ፕሮፓጋንዳ የተነዛውን ጀግናው የህወሃት ሰራዊት እየተኮሰ የደርግ ሰራዊት ደግሞ ውሃ እየረጨ የተዋጉበት አይነትን ምስል ነው፡፡ ያ ጦርነት እጅግ አስከፊ፣ እጅግ ውስብስብ፣ የሚሊዮኖችን ህይወት የቀጠፈ፣ ሚሊዮኖችን ያፈናቀለ፣ ሀገርን በመገንባት ታላቅ ሀገር ለማድረግ ይወጣ የነበረን ኢኮኖሚ ዶግ አመድ አድርጎ እስከዛሬ ድረስ በድህነት ውስጥ እንድንዳክር ያደረገን ነበር፡፡
ብዙ የትግራይ ወጣቶች ያልተረዱት ነገር ያ ጦርነት ህወሃት ብቻውን የተዋጋው አልነበረም፡፡ ደርግን ለመጣል ትልቅ አስተዋጽኦ ካደረገው የኤርትራ ውጊያ በተጨማሪም የደርግ የእርስ በርስ ስልጣን ሽኩቻ፣ የአለም አቀፍ ፖለቲካው በተለይም የምእራባውን ደርግን ለመጣል የሰሩት ስራ እና የሶሻሊስቱ ካምፕ መፈራረስ ዋነኞቹ ናቸው፡፡ የህውሃት ድልም ከአለም አቀፉ እውነታ በተጨማሪም የሻእቢያ ሰራዊት እና የአማራ ገበሬ ትልቅ አስተዋጽኦ ላይ የተመሰረተ ነበር፡፡ ጦርነቱ 17 አመት የፈጀውም እጅግ ከባድ እና ውስብስብ ስለነበረ ነው፡፡
እድሜአቸው በ20ዎቹ እና በ30ዎቹ የሚገኙ በርካታ ወጣቶችም ህወሃትን የማይበገር፣ የማይሸነፍ፣ መለኮታዊ መሰል ሃይል ያለው፣ እንኳን አፍሪካ ውስጥ ያለ ሃይል ራሳቸው አሜሪካኖቹ ሊያሸንፉት የማይችሉ ሱፐር ናቹራል ሃይል አድርገው እንዲያስቡ ተቀርጸዋል፣ እውነቱ ግን ያ አይደለም፡፡ የእውነት ዛሬ አንድ ግጭት ቢቀሰቀስ የህወሃት አቅም አንድን የኤርትራ ሰራዊት ክፍለጦርን ለመቋቋም መቻሉን እጠራጠራለሁ፡፡
ከ1983 ለውጥ በኋላ ኢትዮጲያ ውስጥ የተከሰተው ሰላም እና የነጻ ኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ እንዲሁም በአለም አቀፍ ደረጃ የተፈጠረው የጸረ ሽብር እንቅስቃሴ በሃገራችን ከፍተኛ እድገት እንዲመዘገብ እና ለውጦች እንዲመጡ አድርጓል፡፡ በርግጥ ለ27 አመታት በህወሃት አጋፋሪነት ሲመራ የነበረው መንግስት በእነዛ 27 አመታት ከአለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች እና ከፋይናነስ ተቋማት ያገኘው ብድር እና እርዳታ፣ እንዲሁም በተነቃቃው የሀገር ውስጥ ኢኮኖሚ ምክንያት ከሃገር ውስጥ በታክስ እና መሰል መንገዶች የመነጨውን ገንዘብ ታሳቢ በማድረግ የመጣው እድገት ከተገኘው ገንዘብ አንጻር እጅግ በጣም አነስተኛ ነው የሚሉ ኢኮኖሚስቶች አሉ፡፡ ያ ዳታ የሚፈልግ እና ባለሞያ መሆንን የሚጠይቅ ስለሆነ አስተያየት ለመስጠት እቸገራለሁ፡፡
በእነዚህ አመታት ኢትየጲያ ውስጥ ከፍተኛ ልማት የታየባቸው ሁለት አካባቢዎች ትግራይ እና አዲስ አበባ ናቸው፡፡ እንኳንም ለሙ፡፡ በተለየ ሁኔታ በእነዚህ አካባቢ የመጡት ልማቶች ለትግራይ ህዝብ በአንጻራዊ መልኩ ከፍተኛ ጥቅምን የሰጡ ናቸው፡፡ የአዲስ አበባው ልማት ለምሳሌ በከፍተኛ ሁኔታ የተያዘው የህወሃት ደጋፊ ወይም በነሱ ዙሪያ ባሉ የትግራይ ባለሃብቶች ነው፡፡ ይህንን ሃቅ ከብዙ ነገር ጋር በማያያዝ ሊያስተባብሉ የሚሞክሩ ሰዎች ይኖሩ ይሆናል ሃቁን ግን መለወጥ አይቻለም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በትግራይ ክልል እጅግ ሰፊ የሆነ የመሰረተ ልማት እና የኢንዱስትሪ እ,ድገት ተፈጥሯል፡፡ መልካም ነው እንኳንም አደገች፡፡
በህወሃት መር አስተዳደር ዘመን የመንግስት አስተዳደር ፣ የመከላከያ ሰራዊት ፣ እና የደህንነት እና ጸጥታ መዋቅሩ  በከፍተኛ ያልተመጣጠነ ሁኔታ በትግራይ ተወላጆች ተይዞ ነበር፡፡ በተመጣጣኝ የብሔር ውክልና አምናለሁ የሚለው አስተዳደር ይህንን ፍትሐዊ ያልሆነ የመንግስት ሃላፊነት ቦታን እና ሃላፊነትን በአንድ አካባቢ ሰዎች መሙላት ለ27 አመታት ተያይዞት ነበር፡፡ በተለያዩ መንገዶች የሚገኙ ጥቅሞች ለምሳሌ የኪራይ ቤቶች ቤት፣ የመሬት ምሪት፣ የኢንቨስትመንት ድጋፍ፣ የባንክ ብድር፣ ወዘተ…. ባልተመጣጠነ እና እጅግ ሰፊ በሆነ መልኩ በሰፈር እና በአከባቢ ላይ የተመሰረተ እና በአጠቃላይ በሃገራችን ላይ ኢፍትሃዊ አስተዳደር እና ኢኮኖሚ ፈጥሮ ነበር፡፡ የማይካድ……ሃቅ!!!
በንግድ ስራ ላይ ለተሰማሩ ሰዎች የነበረ ፈተናም ይህ ነው፡፡ የመንግስት ጨረታዎች፣ በርካታ ያለጨረታ የሚተላለፉ ትልልቅ ኮንትራቶች፣ ልዮ የንግድ እድሎች ወዘተ…. ብሔር ተኮር በሆነ መልኩ ሲከናወኑ ነበር፡፡ ለምሳሌ የሜቴክ “አጋርነት” በሚል በብዙ ሚሊዮን ብር የሚቆጠር ስራዎች ለተመረጡ ሰዎች ብቻ የሚሰጥበት አካሄድ ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡
ያ ……ሁሉ አለፈ፡፡ ይሁን ይሁን ሁሉም ኢትዮጲያዊ ነው፣ ያለፈው አልፏል እና ወደሚቀጥለው ምእራፍ እንሸጋገር ተብሎ የመጣው ለውጥ ግን ለህወሃታውያን በቀላሉ የሚዋጥ ነገር አልሆነም፡፡ እስካሁን በሀገራችን ለተፈጠሩት ችግሮች ሁሉ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እጃቸው አለበት፡፡
ዛሬ ህወሃታውያን ነገሮች ወደኋላ ካልተመለሱ በስተቀር…… በሚል በመንግስት ላይ ከፍተኛ ጫና ማድረግ ብቻ ሳይሆን ትግራይን ነጻ ሃገር እናደርጋለን የሚል ዛቻ ውስጥ ገብተዋል፡፡ ወደኋላ መመለስ የማይታሰብ ነገር ስለሆነ የትግራይ ጉዳይ ምን ይዞ ይመጣል፡፡
ትግራይ በእምቢተኝነት ብትቀጥል….
መንግስት እርምጃ መውሰዱ አይቀርም፡፡ ዛሬ ሊሆን ይችላል …የዛሬ አመት ሊሆን ይችላል፡፡ በጀት ከመከልከል ጦር እስከመላክ ድረስ የሚደርስ መሆኑ ደግሞ አይቀርም፡፡ በዚህ ሂደት ደግሞ የሚጎዳው ህዝቡ ነው፡፡
ትግራይ ነጻ ሀገር ብትሆንስ………..
መታወቅ ያለበት ትልቅ ጉዳይ የትግራይ ነጻነት እንደ ኤርትራው ዘመን በምርቃት የምትለያይበት አይደለም፡፡ በጦርነት የማስቆም ፍላጎት ከመንግስት በኩል ይኖራል የሚል ግምት የለኝም፡፡ ነገር ግን ሁለት ጉዳዮች ……..ለትግራይ ህዝብ ዳግም አዲስ የመከራ ዘመን ጅማሬ ይሆናል፡፡
የመጀመሪያው ልክ ነጻነት የሚል ነገር እንደተሰማ ከአማራ ክልል ጋር በተለይም በራያ እና በወልቃይት እና ሌሎችም አካባቢዎች ያለው የድንበር ይገባኛል ጥያቄ ወዲያውኑ በግጭት ለመፍታት ሩጫ ይጀመራል፡፡ ወዲያውኑ ከሚፈጠሩ ግልጽ እውነቶች አንዱ ይህ ነው፡፡ ጦርነት ብዙ ታንክ፣ የጦር አውሮፕላን፣ ትልቅ ሰራዊት…ወዘተ ሰላለ ብቻ የሚያሸንፉበት ነገር አይደለም፡፡ በቂ ቁርጠኝነት ያለው ሰፊ የሰው ሃይል ብቻ ለሰፊ ጥፋት በቂ ነው፡፡ በሁለቱ በኩል ግጭት ቢፈጠር አሸናፊ የሌለው የዘመናት ጥፋት ይፈጠራል፡፡
ሌላው ከኤርትራ በኩል ወዲያውኑ የድንበር ጥያቄን ተከትሎ የሚጀመረው ግጭት ነው፡፡ ይህም እጅግ አስከፊ እልቂት ብቻ ሳይሆን 27 አመት የተገነባው መሰረተ ልማትን ሙሉ በሙሉ ሊያወድም የሚችል ግጭት ይሆናል፡፡
ብዙ ሰው የረሳው ሌላው ትልቅ ጉዳይ ግን…..ትግራይ ነጻ ሀገር ከሆነች በቀሪው የኢትዮጲያ ክፍል የሚኖረው የትግራይ ተወላጅ ምን ይሆናል? የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ በጸብ መለያየት የሚያመጣው ብዙ ጦስ አለ፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጲያ መንግስት ውጡልኝ ሊል ይችላል፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወንድሞቻችን ልክ በኢትዮ ኤርትራ ዘመን እንዳየነው አስከፊ ሁኔታ ሊደገም ይችላል፡፡ ያ ደግሞ በትግራይ ሊፈጥር የሚችለው የኢኮኖሚ እና የሰብአዊ ቀውስ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ብዙ ሃብት ያፈሩ፣ የሀገር ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ ያላቸው ሰዎች ንብረታቸውን እና ሃብታቸውን የሚያጡበት፣ ለኢትዮጲያም የተወሰነ የኢኮኖሚ ተጽእኖ የሚፈጥርበት ጉዳይ ይሆናል፡፡ ያ ብቻም ሳይሆን በርካታ ወጣቶች እድሜያቸውን በሙሉ በኖሩበት እና ሁሉንም ያልተሸራረፈ መብት በሚያገኙበት ሀገር ላይ ወይ የመኖር መብታቸው ወይም ደግሞ የመስራት መብታቸው ላይ ገደብ እና ሌሎች ነገሮችም ሊፈጥር ይችላል፡፡
ሃገር ምስረታ ብሎ በማህበራዊ ሜዲያ ላይ መፎከር እና የብሽሽቅ ፖለቲካ ውስጥ መግባት ሲያዩት ቀላል እና በሞባይል ወይም በኮምፒውተር ኪቦርድ ላይ ኢጎን መወጫ እና ሌሎችን ማብሸቂያ መስሎ ቢታይም፣ ጉዳዩ መሬት ላይ ሲወርድ 85% ገበሬ የሆነው የትግራይ ህዝብ ላይ ይዞ የሚመጣው ጣጣ ግን እጅግ ብዙ ነው፡፡ ዛሬ ላይ ቆመን በኤርትራ ነጻነት ወቅት የነበረውን ፉከራ፣ ድንፋታ፣ …..ብዙ ብዙ ነገሮች ስናስብ ምን ይሰማናል?
የሆነ ሆኖ ህወሃታውያን የዛሪዪቱ ኢትዮጲያን በመነጋገር እና በመከባበር፣ ለሁሉም እኩል የሆነች አድርጎ ለመፍጠር የሚደረግ ማንኛውንም ጥረት እንቅፋት በመሆን የሚያተርፉት ነገር የለም፡፡ ነገር ግን ለእኛም ሆነ ለትግራይ ገበሬ የዘላለም ቁስል ትተው አብዛኞቹ በውጪ ሀገር የሞቀ ኑሯቸውን መግፋት ይጀምራሉ፡፡ ማን ተጎዳ?

በነገራችን ላይ :– ይህ የምትመለከቱት ፎቶ በ1977 ዓ.ም. ከትግራይ አካባቢ ተፈናቅለው በሱዳን ከተጠለሉት ስደተኞች ህይወታቸውን ያጡት ኢትዮጲያውያን መቃብር ነው፡፡

Filed in: Amharic