>

እነ ጄነራል ሰዓረ መኮንንን በመግደል ጥፋተኛ የተባለው ተከሳሽ በዕድሜ ልክ እስራት እንዲቀጣ ተወሰነ...!!! (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

እነ ጄነራል ሰዓረ መኮንንን በመግደል ጥፋተኛ የተባለው ተከሳሽ በዕድሜ ልክ እስራት እንዲቀጣ ተወሰነ…!!!
ኢትዮጵያ ኢንሳይደር

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ የኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ አዛዥ የነበሩትን ጀነራል ሰዓረ መኮንንን እና ሜጀር ጄነራል ገዛዒ አበራን በመግደል ጥፋተኛ የተባለው ተከሳሽ በዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ወሰነ። ፍርድ ቤቱ ዛሬ ሰኞ ሰኔ 21 በተከሳሽ አስር አለቃ መሳፍንት ጥጋቡ  ውሳኔውን ያስተላለፈው፤ በፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የቀረበውን የሞት ቅጣት ውድቅ በማድረግ ነው።
ዐቃቤ ህግ ሰኔ 11 በዋለው ችሎት የከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት 3ኛ የፀረ ሽብር እና ህገ መንግስታዊ ጉዳዮች ችሎት ከቅጣት አወሳሰን መመሪያው ወጥቶ በተከሳሽ ላይ የሞት ቅጣት እንዲወስንበት ጥያቄ አቅርቦ ነበር። ሆኖም ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ ላይ በእድሜ ልክ እንዲቀጣ የወሰነው “ድርጊቱ ተሳክቶ ቢሆን በአገሪቱ ውስጥ የሚከሰተውን ከግምት ውስጥ በማስገባት እና ተከሳሹ የገደላቸው የአገሪቱን ሉዓላዊነት ጠባቂ የሆነውን የመከላከያ ጠቅላይ አዛዥ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት” መሆኑን በዛሬው ችሎት ላይ ገልጿል።
በዛሬው ችሎት ከጋዜጠኞች በተጨማሪ ለተከሳሹ አጋርነታቸውን ለማሳያት የማህበራዊ ሚዲያ አንቂዎች እና የተከሳሹ የቅርብ ሰዎች በፍርድ ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ እና በችሎቱ ውስጥ ተገኝተው ነበር። ()
Filed in: Amharic