የህውሃት እርኩሰት እና የአብይ ክሽፈት፤ የአንድ ወገን ተኩስ አቁም – ሰላም፣ ፍትህ እና ተጠያቂነት…!!!
ያሬድ ሀይለማርያም
የአብይ አስተዳደር አፈሙዝ ወደ መሬት ማለቱ እሰየው ነው የሚያስብለው። ከደም መፋሰስ እና የግጭት አዙሪት ሊያወጣን ከቻለ ከማንም ጋር ለሰላም ሲባል መደራደር፣ መነጋገር፣ ለውይይት ፈቃደኛ መሆን እሰየው ነው የሚያስብለው። ለእኔ ከመነሻውም ይህ ጦርነት የህውሃትን እርኩስነት እና የአብይ አስተዳደርን ክሽፈት ማሳያ ሆኖ ስላየሁት ያሳስበኝ የነበረው በአንደኛው እርኩሰት እና በሌላኛው ክሽፈት የሚያልቀው ወገኔ ጉዳይ ብቻ ነበር። ምክንያቱም በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ዜጎቻችንን የሰዋንባቸው ያለፉት ጦርነቶች ሁሉ የፖለቲከኞቻችን ክሽፈቶች ማሳያዎች ናቸው። ከመቶ ሺ በላይ ገብረን ኤርትራን አስገነጠልን። ከሰባ ሺ በላይ ህይወት ገብረን ባድመን በፍርድ ተረታን፣ ዛሬም እንዲሁ በሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ገበርን። ይሄኛው ግን በሰላም የኢትዮጵያን አንድነት አስጠብቆ ለመኖር ይሁን ትግራይን ለመሸኘት ግን ገና ውሉ አለየም።
+ ሰላም፤
ለማንኛውም ይህ በህውሃት እርኩሰት እና በአብይ ክሽፈት የተጀመረው ጦርነት ከአንድ ወገን በተወሰደ እርምጃ ወደ ተኩስ አቁም መድረሱ ይበል የሚያሰኝ ነው። ላለፉት ስምንት ወራት ሰላሙን ተነጥቆ በስቃይ ውስጥ የቆየው የትግራይ ሕዝብ ቢያንስ ከተኩስ ድምጽ እረፍት ያገኛል። ስቃዩም ይቀንስለታል። ለኢትዮጵያም በጦርነቱ ሰበብ ፊቱን ያዞረባት አለም ትንሽም ቢሆን ሊለሳለስ ይችላል።
+ ፍትህ
በዚህ ጦርነት ኢትዮጵያ እንደ አገር እና ትግራይም እንደ ክልል በሰው ህይወት እና በንብረት ላይ ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል። ከግራ ቀኝ የሞተው ሰው ቁጥር ገና በውል ባይታወቅም በሺዎች እንደተቀጠፉ አንዳንድ ሪፖርቶች ያመላክታሉ። በንብረት የደረሰው ውድመት ስፍር ቁጥር የለውም። ሚሊዮኖች ተፈናቅለዋል። እጅግ ከፍተኛ የሆነ ሰብአዊ ቀውስም ደርሷል። ዜጎች ለርሃብም ተዳርገዋል። የጦር ወንጀል፣ በሰብአዊነት ላይ ያነጣጠሩ ወንጀሎች እና ሌሎች ከፍተኛ ወንጀሎችም ተፈጽመዋል። ኢትዮጵያ እንደ አገር ከስራለች። በዚህ ጦርነት የተጎዱ ወገኖች ግን ፍትህን አጥበው ይፈልጓታል። ፍትህ ለተደፈሩ ሴቶች፣ ፍትህ ለማይካድራ፣ ፍትህ በሰሜን ዕዝ ውስጥ ለተጨፈጨፉ፣ ፍትህ በአክሱም በጅምላ ለተገደሉ፣ ፍትህ ለትግራይ ሕዝብ፣ ፍትህ ለወላይት እና እራያ ሕዝብ። ከተኩስ አቁም ጥያቄው መመለስ በኋላ የፍትህ ጉዳይ የሚደረጉ ድርድሮች አካል ይሆናል ብለን እንመን?
+ ተጠያቂነት
ኢትዮጵያን ለዚህ ሁሉ መከራ የዳረጓት በግራ እና በቀኝ ቆመው የሥልጡን ፖለቲካ መስራት ያቃታቸው እና የስልጣን ጥም ናላቸውን ያዞረው የትላንት ኢህአዴጎች፤ የዛሬዎቹ ህውሃት እና ብልጽግና ናቸው። ሕውሃት በቆረበበት የእኩይ ባህሪው እስከ ጥግ ገፍቶበት፤ ብልጽግና ህውዋት ባዘጋጀለት ወጥመድ ውስጥ ዘሎ ዘው ብሉ አገሪቱን እንዲህ ወዳል የከፋ ጦርነት ውስጥ ዶለው ሺዎችን ጨረሱ። ይባስ ብለው የጎረቤት አገርም ጋብዘው ፍዳችንን አበዙት። ኢሳያስም ክፍተቱን ተጠቅሞ የቆየ ቂሙን አወራረደ። እነዚህ ሁለት ኃይሎች የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ በተለይም የትግራይ ክልል ለደረሰበት ኪሳራ ሁሉ ተጠያቂዎች ናቸው። የተጠያቂነት ደረጃቸው ይለያይ ይሆናል እንጂ።
+ ሕዝብን ማክበር እና ግልጽነት
ሌላው የፖለቲከኞቻችን ክሽፈት ለሕዝብ ያላቸው ንቀት ነው። እርስ በርስ ሲጣሉም ሆነ ሲፋቀሩ በሕዝብ ኪሳራ መሆኑ አልበቃ ብሎ ሕዝብ በአገሩ ጉዳይ የባዳነት ስሜት እንዲሰማው የሚያደርጉት ነገር ግርም ይለኛል። ጦርነት ማካሔድ የሕዝብ ድጋፍን ይጠይቅ ስለነበር ሲጀመር በአዋጅ እና በጋዜጣው መግለጫ ጋጋታ ነው። ይህን የመሰለ የሰላም ብስራት፤ ተኩስ ማቆምን ግን ትላንት በብጣቂ ማስታወሻ ከጠ/ሚኒስትሩ ቢሮ ከተሰጠ የእወቁልን መረጃ ባለፈ ግን ግልጽነት የጎደለው እና ሕዝቡንም ለብዙ የተሳሳቱ ትንታኔዎች ያጋለጠ ነው። ሕዝብ በአገሩ ጉዳይ መቼ ነው በአገዛዞቹ በኩል በወቅቱ፣ እውነተኛ እና ትክክለኛ መረጃ እንዲያገኝ የሚደረገው? ለምንድን ነው የተወሰደውን እርምጃ በተመለከተ ወሬዎ እየተዛባ ከመናፈሱ በፊት መንግስት ዝርዝር መግለጫ በአግባቡ የማይሰጠው? የተወሰደውስ እርምጃ የተኩስ አቁም ነው? ወይስ ትግራይን ለህውሃት አስረኮ መመለስን ይጨምራል? ወይስ ሌሎች እንድምታዎች አሉት? ሕዝብን ማማከር፣ ለሕዝብ ቶሎ የአገሩን ጉዳይ እንዲያውቅ ማድረግ፣ በእያንዳንዱ ወሳኝ አገራዊ ጉዳይ ላይ ቶሎ መግለጫ ሰጥቶ ሕዝብን ማረጋጋት የመንግስት ሥራ ነው። ብልጽግና አንዱ ጎልቶ የሚታይበት ክሽፈት ቢኖር ከሕዝብ ጋር ያለው የመረጃ ልውውጥ መስመር ነው። ሕዝብ በአገሩ ጉዳይ ሁሉንም ነገር የማወቅ መብት አለው።
የተኩስ አቁሙን እርምጃ ዘላቂ እንዲያደርግልን እና ሰላም እንዲሰፍን ተግተን እንጸልይ።
ሰላም ለአገራችን!