ትናንትም ጥያቄ! ዛሬም ጥያቄ! ነገም ጥያቄ! ጥያቄ ብቻ ነው ማቅረብ የምንችለው!
አሰፋ ሀይሉ
ስንት ህዝብ ከፈጀና ካስፈጀ በኋላ፣ ከሕዝብ የተሰወረ ስምምነተ ከጎረቤት ሀገር ጋር ፈጽሞና ያለ ህዝብ ዕውቅናና ውሳኔ ስምምነቱን አፍርሶ ወይም ቃሉን አጥፎ፣ መከላከያውን አምኖ የዘመተውን የአማራን ህዝብ ሚሊሻና ሠራዊት ለጥቃትና ጦርነት አጋልጦ፣ ራሱ አቋቁሜዋለሁ ያለውን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደርና በሥሩ ተባብረውት ይሠሩ የነበሩ ሀይሎችንና ሰዎች በመካድ ሜዳ ላይ ጥሎ በመሸሽ የሚገኘው መልካም ስምና ዝና፣ የሚገኘው ሀገራዊ ትርፍ፣ ወይም የሚመጣው መልካም ቱሩፋት ምንድነው?
ለመሆኑ የዓለማቀፍ ኃይሎች ለሰብዓዊ እርዳታና ለተኩስ አቁም ስምምነት እንዲሁም ለሁሉን አቀፍ ሠላማዊ ንግግርና ሀገራዊ ስምምነት በሚገፋፉበት በዚህ ሰዓት – ስንት ሺህ የሀገሪቱን ሠራዊት አስፈጅቶ፣ ስንቱን ሺህ ለምርኮ አስረክቦና ለአካል ጉዳት ዳርጎ፣ ያለምንም ሂደትና የተጠና አካሄድ – ያለምንም ስምምነትና ንግግር.. ድንገት እንዳበደ ሰው በመንግሥት ሥር ያለን የሀገር ክፍልና ድንበር ከነህዝቡና ከነመሠረተ ልማቶቹ፣ ከነሀብቱና ንብረቱ ‹‹አሸባሪ›› ብሎ ለፈረጀው ቡድን እርግፍ አድርጎ ጥሎ ብርርርር.. ብሎ መጥፋት – ቆይ… ይሄ ሁሉ ነገር… የጤና ነው ግን? ከአንድ የሀገር መሪስ የሚጠበቅስ ነው ወይ?
‹‹ነፋስ ላይ የተበተነ ዱቄት አድርጌያቸዋለሁ!›› እያለ ሲፎክር የከረመ ሰው፣ አሁን በምን አፉ ነው ዓይኑን በጨው አጥቦ የዓለም ሁሉ ዓይኖች እያዩት ከተበተነበት ንፋስ እንደ አዙሪት አቧራ ወደላይ ተነስቶ ማረከኝ፣ ገደለኝ፣ አሸነፈኝ፣ አባረረኝ የማለት ሞራሉንና ድፍረቱን የሚያገኘው?
ለመሆኑ ይሄ ሰውዬ የሰከነና የታወቀ የተፈረመ ስምምነት ከሚደረግባቸው ተገቢና ህጋዊ ተግባራት የሚሸሸውና የተራ ዱርዬና ንክ ሰው ባህርይን የሚመርጥበት ምክንያቱ ምን ይሆን? አሁን ‹‹ድል-ቁርሱ›› እያለ የካባቸውን ቱልቱላ ማዕረግተኞች ምንድነው የሚያደርጋቸው? የኢትዮጵያን ህዝብ የዋሸበትና በቁሙ ያሞኘበትስ አግባብ? ማነው የሚጠይቀው ይሄን የኢትዮጵያውያንን ደም በከንቱና ያለምንም ግብ በማፍሰስና በማስፈሰሰ የተለከፈ ሰውዬ?
ለመሆኑ አስመራ ሲመላለስና ከኢሣያስ አፈወርቂ ጋር ሳዋ ለሳዋ ሲያሽቃብጥ – ከኤርትራስ ጋር አወዛጋቢ ድንበሮችን በተመለከተ በህቡዕ ያደረገው ህጋዊ ስምምነት አለ? ወይስ የጨረቃ ‹‹አሁን-ና፣ አሁን-ሂድ›› የሚል ዕቃ-ዕቃ ጨዋታ ነበር ሲካሄድ የቆየው? ማነው ለደረሰውና ወደፊትም ለሚደርሰው ሀገራዊ ውድመት፣ ሰብዓዊ ኪሣራና ወንጀሎች ሁሉ ተጠያቂ የሚሆነው? ቀድሞስ ምን አስቦ ነው ይሄ ሰውዬ ቁጭ አድርገን በጠረጴዛ ዙሪያ እናደራድራችሁ ሲባል አሻፈረኝ ብሎ የከረመው?
አሁንም ወደፊትም በዚህ ቢጩ ሰውዬ እየተመራን ለመቀጠል ነው ወይ የኢትዮጵያውያን ሀሳባችን? መቼ ነው አንድ ሰው ለሠራው ጥፋት ሁሉ ኃላፊነቱን ወስዶ ከሥልጣኑ የሚወርደውና፣ ላደረሰው ሀገራዊ ሰቆቃ የሚጠየቀው?
‹‹ስንኖር ኢትዮጵያዊ፣ ስንሞት ኢትዮጵያ›› ያለውን ሕዝብ ደም ካፋሰሰና ሀገርና ዜጋን ካወደመ በኋላ፣ ‹‹ጀግናው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት›› እያለ በል-በለው ብሎ ወገንን ከወገን ሲያዋጋና ሲያጫርስ ቆይቶ፣ ሲማረኩ ‹‹የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት አይደሉም›› እያለ ለመስዋዕት ዕርድ አሳልፎ የሰጠውን ወጣት ዜግነት የሚክድ መሪ – መሪ ነው ወይ ለመሆኑ? መሪ ይባላል ወይ በበላይነት እያዘዘ፣ እየመራና ‹‹ከሲቹዌሽን ሩም›› ያደባባይ አዛዥነት ምክንያት ለሆነው ስኬትም ሆነ ውድቀት ሀላፊነቱን የማይወስድ ሙልጭልጭ ለወስዋሳ ሰው?
ምን ሆነን ነው እንዲህ የወረድነውና የማንም ዘልሎ ያልጠገበ ቱሪናፋ ወጠጤ መጫወቻ ያደረግነው ራሳችንን? መቼ ነው የሰከነና ሩቅ ያለመ፣ በሚሊዮኖች ዜጎች ህይወትና ደም ሳይቀለድ፣ በሰከነ አዕምሮ ነገሮቻችንን የምናከናውነው? ሰው ጠፋ ወይ ባገሩ? ምን እስክንሆን ነው?
ዛሬ እኮ ዓለምና የዓለም ሚዲያ ሁሉ ያየውና ያጋለጠው ጉድ ስለሆነ በዓይናችን ፊት በካሜራ ስለቀረበልን እኮ ነው ከመራሩ እውነት ጋር ፊት ለፊት ለመጋፈጥ የተገደድነው! ስንት ጊዜ ነው በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጦሩ ውጣ እየተባለ ከተሞችና የሀገሪቱ ዜጎች ለሰብዓዊ ሰቆቃ የሚዳረጉት? ማነው ይሄንን ሀገራዊ የደምና የሰቆቃ አሳዛኝ ቀልድ ማስቆም የሚችለው? በቃን፣ በቃህ፣ ከዚህ በላይ መውሸልሸልና መወሻከት በቃህ የምንለው መቼ ነው?
ለመሆኑስ ከወያኔም ሆነ ከማንም ጋር በጨዋ ደንብ ቁጭ ብሎ ሰክኖ መምከርና ወደ መግባባት ማምራት ነው የሚሻለው?.. ወይስ ሀገርንና ህዝብን አውድሞና አዋርዶ ሀገርምድሩን ላሞራ ጥሎ መፈርጠጥ ነው? ይሄን ዓይነቱ መደዴነትና ያደባባይ ውንብድና ለእኛ ኢትዮጵያውያን ይገባናል ወይ? ይመጥነናል ይሄ? ስም የሌላቸውና የአንድን በሽተኛ ሰው ቅዠት ለማሳካት ሲባል በሺህዎች በለጋ ዕድሜያቸው እየወጡ ለጅምላ እልቂትና በጥይት መታጨድ የተዳረጉትን ወገኖቻችንን ማን ነው ስማቸውን የሚያነሳላቸው? ያጎደሏቸውን ቤተሰቦቻቸውን ዞር ብሎ የሚያያቸው ማነው?
እንዲህ ያለ የህጻናት ዕቃ-ዕቃ፣ እንዲህ ያለ ዲሞ-ፈጭስ ጨዋታ በሀገር ላይ መጫወት እንዴት ተቻለ? እንዴት ራሳችንን ለእንዲህ ያለው ከህጻንም የባሰ ህጻን ምሪትና መዋረድ አሳልፈን ሰጠን? ምንድነው እያደረግን ያለነው? ምርጫችን ምንድነው?
አሁንም በቅርቡ ከዓለም ሁለት ሃያላን አገራት መካከል አንዱ አደርጋችኋለሁ ተከተሉኝ የሚለውን ልክፍተኛ እየተከተልን ለመንጎድ በእውን መርጠናል ማለት ነው? እውን እኛ ኢትዮጵያውያን ምርጫችንና ማንነታችን ይኸው ነው? ከዚህስ በኋላ እንዴት ወዳለ ሞት ይነዳናል? እንዴት ወደመሰለ ሀገራዊ ሰቆቃና እልቂት እንነዳለን? መቼ ነው በቃን የምንለው? መቼ ነው?
አሁንስ ሁሉም ነገራችን እጅግ ስለበዛ ከፈጣሪ የምጠይቀውም ልቦና የለም! ሁሉም ልመና አልቆብናል! ፈጣሪ የሚገባንን፣ የእጃችንን፣ የሆንነውን መጠን ይስጠን! (ማለት ብቻ ነው የሚቻለው)፡፡ ምናልባት ምርጫችን ይህ ይሆናል፡፡ ምናልባት ልንሆንና ልንደርስበት የምንችለው ትልቁ ከፍታ ይኸውና ይኸው ነው፡፡ ከሆነም ያለንን፣ የሰጠንን፣ የመረጥነውን ይባርክልን!
አንቺ መሪዎችሽ ህጻናት የሆኑ ሀገር ወዮልሽ፡፡ ኤሎሄ! ኤሎሄ! አምላክ ሆይ ስለምን ተውኸን? ብትወድስ ይህ በህጻን መሪዎች የገባንበት ጽዋ ከእኛ ይለፍ! ይለፍልን! ያሳልፈን! ያሳልፍልን ፈጣሪ አምላክ ይህን እርግማን ከላያችን ላይ! ወደን ከተደፋን፣ ብንረገጥ እንዳይከፋን – ጫንቃችንን ያደንድንልን ማለት ነው! ሌላ ምን ይባላል? እርሱ አንድዬ ይሁንሽ አንቺ ምስኪን ሀገር።