>

ስምምነትና.....ድል...!!! ዘመድኩን በቀለ

ስምምነትና…..ድል…!!!

ዘመድኩን በቀለ

 

*…. መለስ ዜናዊ ኤርትራን ገፋፍቶ አደፋፍሮ አስገነጠለ። ኤርትራ ስትገነጠል ትግራይ በኢትዮጵያ ሃብት እንድትለማ አስቦ ነው የሚሉ አሉ። ኤርትራም ተገነጠለች። ከእናት ሃገሯም ተለየች። ነገር ግን ደቀቀች። ወደመች። አሁንም እነ ዐቢይ አሕመድ ገፋፍተው ገፋፍተው ትግራይን የአንቀጽ 39 ን መንገድ አሳይተው ዘፍ ሊያድርጓት የሚፈልጉ ይመስላል። ነገሮች ሁሉ ደስስ አይሉም። ትግራይም የኤርትራ ዕጣ እንዲደርሳት፣ እየገፏትም ይመስላል። ሂዱልን አይነት ነገርም ነው የሚመስለው…!
 
… መቼም የፍልስጤሙ ሃማስንና የኃያሏን ሃገር  የእስራኤልን ነገር ሳስብ ይገርመኛል። የሆነ ጊዜ አጅሬ ሃማስ ወፈፍ ያደርገውና ወደ እስራኤል ከተሞች በመቶ የሚቆጠሩ ኢላማቸውን የማይመቱ ርኬቶችን ያስወነጭፋል። ያስወነጭፍናም ከእስራኤል ወገን የሆነች ከተማ ወይ መንደር ውስጥ አንድ ኩሽና ያፈርሳል፣ ሁለት ሦስት እስራኤላውያንም ይገድላል። አበቃ።
… በተራዋ እስራኤል ደግሞ የአጸፋ ምላሽ ለመስጠት በሚል ሰበብ ሙሉ የፍልስጤም ከተሞች ላይ እሳት ታዘንብቧቸውና ታወድማቸዋለች። የፍልስጤማውያን ህንጻዎች ወደ ዐመድ… ወደ አፈር ፍርስራሽነትም ትለውጣቸዋለች። 200 የፍልስጤም ህጻናት ይገደላሉ። ከሺ በላይ ጎልማሶች፣ ወጣቶችና ሴቶችም ይገደላሉ። ብዙዎችም ይማረካሉ።
… ብዙም ሳይቆይ ከዚያ እነ አሜሪካ ግብጽን አሸማግያቸው ብለው ይልኳታል። ወዲያው የተኩስ አቁም ስምምነትም ይፈራረማሉ። የሚገርመው ነገር በዚህ ጨዋታ እስራኤል ዝም ጮጋ ስትል ፍልስጤማውያን ግን በወደሙባቸው ከተሞች፣ በፍርስራሽ ቤቶቻቸው ስር፣ በሞቱ፣ በተገደሉ ልጆቻቸው መቃብር ላይ ቆመው ” የዓለም ዋንጫን የበሉ ያህል ያለቅጥ፣ ያለልክ ይጨፍራሉ። ” ለሚያያቸው ለሚመለከታቸውም እስራኤል ተሸናፊ፣ ፍልስጤማውያን አሸናፊ ነው የሚመስሉት። ለማንኛውም በእስራኤልና በሃማስ ፀብ ፍዳውን የሚያየው የፍልስጤም ህዝብ ነው። የሚራበው፣ የሚጠማው፣ የሚሞተውም ህዝቡ ነው።
… በኢትዮጵያ የሴራ ቦለጢቃው እንዳለ ሆኖ አሁን በህወሓትና በብልጽግና መካከል ተፈረመ የተባለውን “የተኩስ አቁም ስምምነት” ማጣጣሉም ተገቢ አይመስለኝም። ፍጥነቱ ቢያስደንቅም ማለቴ ነው። SMS የመሰለ ስምምነት ቢመስልም ይሄ ለትግራይ እናቶች እንደምን ያለ እረፍትና መታደል እንደሆነ በቦታው የሚገኙ የመከራው ገፈት ቀማሾች ብቻ ናቸው የሚያውቁት። የሚረዱትም። ይሄ እንደ ሃማስ ተደቁሶ ሲያበቃ አሁን በስንት ትግልና ደጅ ጥናት የተገኘን ስምምነት እንደ ” የድል” አድራጊ ቆጥሮ የሚፎክረውን ሰምተን ነገሮች ሊምታቱብን አይገባም። ወዳጄ እንጠይቅ? አሁን ከተኩስ አቁም ስምነቱ በኋላ… በመቀሌም ሆነ በትግራይ እየሆነ ስላለው ነገር የሚያውቅ አለን? ነገስ ስለሚፈጠረው ነገር የሚያውቅ አለን? የትናንቱ ጭፈራ ዛሬ ተደግሟልን? ማነው እየተጎዳ ያለው? የመቀሌ ህዝብ ህወሓት ተመልሳ ስትመጣ የባንክ አግልግሎቱ ጀመረለት? መብራት፣ ውኃ፣ ስልክ፣ ኢንተርኔት ተለቀቀለት? ንግዱ እየተነገደ ነው? ሸቀጦች እንደልብ አሉ? የጤናችሁስ ሁኔታ እንዴት ነው? ቤተሰቦቻችሁን ደውላችሁ ታገኟቸዋላችሁ? የኑሮ ውድነቱስ ቀነሰ? ሰላሙስ ሰፈነ? ሞትና የሞት ዜናዎችስ ቀሩላችሁ? የናፈቃችኋቸው የህወሓት አመራሮች መቀሌ ገቡላችሁ? እናም ማይ ብራደር የስምምነቱን ውል በጭፈራ እንደ ድል አድራጊዎች ጭፈራ ባታስመስሉት፣ ደግሞም ስምምነቱን ለመበሻሸቂያ ባትጠቀሙበት ይመከራል።
…ጎበዝ አሁን በመገናኛ ብዙኀንም… በአካልም በዐማራ ላይ የምትፎክሩ የትግራይ ልጆችም ትንሽ ቀዝቀዝ በሉ። በኤርትራም ላይ የምትፎክሩ ሰዎች ተረጋጉ። የመከላከያን የወታደር ልብስ እንደ ሬሳ እየጎተትክ መደንፋቱን አቁሙ። አጠፋሃለሁ እያልከው አጥፋኝ ብሎ ጭብጦ ይዞ የሚጠብቅህ የለም እና ተያይዞ ለማለቅ አትጣደፉ። እነ አማሪካን፣ አውሮጳና እነ እንግሊዝን አሳምኖ… የኢትዮጵያ መንግሥትን ሸብረክ ያደረገው የእነ ዶር ቴዎድሮስ አድሃኖምንና የትግራይ ዳያስፖራን እልህ አስጨራሽ እንቅልፍ አልባ የዲፕሎማሲ ትግልም ይሄን ስምምነት እንዳመጣም ማወቁ መልካም ነው። እናም ተረጋጉ። የዐቢይ ሴራ እንዳለ ሆኖ ማለት ነው።
… ተወደደም ተጠላም የምትወቃቀጠው እዚያው እርስ በራስህ መሆኑን ዕወቅ። የብልጽግና አገልጋዮች የነበሩ ከሃዲዎች ናቸው ብለህ የምትገድለው የራስህኑ ትግሬ ወንድምህን መሆኑንም አትርሳ። ለምን ከእኛ ጋር በረሃ አልወረዳችሁም? ብለህ የምትገፈው፣ የምትገርፈው፣ የምታስረውም የራስህኑ ወንድም እና እህቶች መሆኑንም አትዘንጋ። ከአፍህ ለሚወጣ ቃል ጥንቃቄ አድርግ። ምክር ነው።
… በሴራ እጅህ በገባው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ላይ መቀለዱንም አቁም። ” ይሄ ዐማራ ስም ነው? አይደል? እያልክ በምርኮኛ እየቀለድክ ቪድዮ መልቀቁ አይበጅህም። እዚህ ውስጥ ዐማራ የሆነ ወታደር አለ? እያልክ ምርኮኛ እየቀረጽክ መልቀቁን አቁም። አይበጅህምና አቁም። የሃገር መከላከያ ሠራዊትን ገዢዎች በየዘመናቱ ቁማር ቢጫወቱበትም ተልዕኮው ሃገር መከላከል ነውና አትዘብትበት።
… ህወሓት አንዴ ቡሩንዲ፣ አንዴ ላይቤሪያ፣ አንደዜ ሶማሊያና ዳርፉር ስትልከው የነበረው ይህንኑ ጦር እንደነበርም አትዘንጋ። ባድመ ላይ እንደቅጠል የረገፈው የኢትዮጵያ ጦር መሆኑንም አትዘንጋ። እናም እንደ ዕድል ሆኖ ዛሬ በኢትዮጵያ ጦር ላይ ቀን ጨልሞበት በዐቢይ አሕመድ፣ በብርሃኑ ጁላ፣ በጌታቸው ጉዲና፣ በባጫ ደበሌ እጅ ወድቆ በሴራ እንዲሾቅ መደረጉን ዓይተህ የሃገር መከላከያ ሠራዊቱ ላይ አታላግጥ። ወገን ቤተሰብ አለውና አታላግጥበት። እነ እገሌን ወደ ሃገራቸው እመልሳለሁ። እነ እገሌን ግን…  የሚለውን ነገር አቁም። ትርፍ የለውም። ኪሳራ ነው።
… መለስ ዜናዊ ኤርትራን ገፋፍቶ አደፋፍሮ አስገነጠለ። ኤርትራ ስትገነጠል ትግራይ በኢትዮጵያ ሃብት እንድትለማ አስቦ ነው የሚሉ አሉ። ኤርትራም ተገነጠለች። ከእናት ሃገሯም ተለየች። ነገር ግን ደቀቀች። ወደመች። አሁንም እነ ዐቢይ አሕመድ ገፋፍተው ገፋፍተው ትግራይን የአንቀጽ 39 ን መንገድ አሳይተው ዘፍ ሊያድርጓት የሚፈልጉ ይመስላል። ነገሮች ሁሉ ደስስ አይሉም። ትግራይም የኤርትራ ዕጣ እንዲደርሳት፣ እየገፏትም ይመስላል። ሂዱልን አይነት ነገርም ነው የሚመስለው።
… ኢትዮጵያ ግን “ንጉሥሽ ሕፃን የሆነ፥ መኳንንቶችሽም ማልደው የሚበሉ፥ አንቺ አገር ሆይ፥ ወዮልሽ!” መክ 10፥16
… ይህ የእኔ የግሌ እይታ ነው። ከተሳሳትኩ እታረማለሁ። ሰላም አምሹልኝ  !!
Filed in: Amharic