>

ኢትዮጵያዊነት ምንድን ነው? (በአንዱ ዓለም ተፈራ)

ኢትዮጵያዊነት ምንድን ነው?

 

ፃ አስተያየት፤ በአንዱ ዓለም ተፈራ


የትናንት ታሪካችን ልንለውጠው ወይንም ልናርመው አንችልም። ማድረግ የምንችለው፤ ከትናንት ተምረን፣ ዛሬ በምንችለው የተሻለ ሠርተን፣ ለነገዎቹ ያማረ ማሰተላለፍ ነው።

 

ኢትዮጵያዊያን ለአገራችን ያለን ፍቅርና ተቆርቋሪነት፤ መለኪያ የለውም። ኢትዮጵያዊያን በያለንበት፤ አረንጓዴ፣ ብጫና ቀዩን ሰንደቅ ዓላማችን፤ በጃችን ጨብጠን፣ በላያችን ላይ አጥልቀን፣ ከሁሉም በላይ በልባችን አቅፈን ይዘን፤ ቀኑንና ሌቱን በያለንበት ኑሯችን እንገፋለን። ይህ ኢትዮጵያዊነት ነው እኛን ካገራችን ጋር ማስተሳሰሩን የሚያንፀባርቀው። ኢትዮጵያዊነት፤ በራሱ ቢያቆሙትም ሆነ ጀርባና ሆዱን አገላብጠው ቢያዩት፤ አንድና አንድ ትርጉም ብቻ ነው ያለው። አንድን ነገር፤ የነገሩ ባለቤቶችም ሆኑ ከባለቤቶቹ ውጪ ያሉ አዳማጮች፤ በትርጉሙ ካልተስማሙ፤ ስለ ነገሩ ያላቸው ግንዛቤ የተለያየ በመሆኑ፤ በመካከላቸው መግባባት ሊኖር አይችልም። ባጠቃላይ፤ አንድ ጉዳይ የተለያየ ትርጉም ካለው፤ ያ ጉዳይ አንድ ብቻ አይደለም። እዚህ ላይ ነው፤ ኢትዮጵያዊነት ምንድን ነው? የሚለው ጉዳይ የሚነሳው? ለኢትዮጵያዊያን ኢትዮጵያዊነት ግልጥ ነው። ይህ ግልጥ የሆነ ጉዳይ፤ ባለፈው ግማሽ ክፍለ ዘመን ብዙ ፈተናዎች ገጥመዉታል። ይህ በበኩሉ፤ ለተለያዩ ሰዎች፤ ለኢትዮጵያዊነት የተለያየ ትርጉም እንዲሠጡት መንገድ ከፍቶላቸዋል። ለመሆኑ፤ ኢትዮጵያዊነት ከፖለቲካ አመለካከት ጋር ይያያዛል ወይ? ታሪክ፣ ቦታ፣ ጊዜ፣ የመሪዎች ጥንካሬ ወይንም ድክመት፤ የውጪ ኃይላት ትንኮሳና ወረራ፣ የተለያዩ ሃይማኖትና ቅርንጫፎቻቸው ወደ አገራችን ሰርጸው መግባት፤ በኢትዮጵያዊነት ላይ ምን ተፅዕኖ አደረጉ? ይህ ጽሑፍ ለኢትዮጵያዊነት ጥያቄ መልስ ሥጡኝ ይላል።

ኢትዮጵያዊያን በአንድ ሕዝብነታችን ተሳስረን፣ አንድነታችን አጠንክረን፣ አንድ አገር ኖሮን ወደፊት ልንጓዝ የምንችለው፤ ኢትዮጵያዊነት ምን ማለት እንደሆነ፤ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ፣ ከሰሜን እስከ ደቡብ ያለነው ሁሉ፤ አንድ የሆነ እምነትና መግባባት ሲኖረን ነው። ይህ ባልሆነበት ሁኔታ፤ ሰላምና መረጋጋት፤ ልማትና ዕድገት፤ የሕልም እንጀራ ናቸው። ይህ፤ መሠረታዊ ሀቅ ነው። አንድ ትርጉም መኖሩ ብቻ ሳይሆን፤ ለዚያ ትርጉም ሁላችን ሕይወታችን ለመሥጠት የምንቆምበት እውነታ ሊኖር ይገባል። ብዙዎች አገሬ ብለው ያልተቀበሉት አገር፤ አገር ነው ወይ? በአንድ አገር፤ ሁልጊዜ ሰላም፣ ሁልጊዜ ደስታ፤ ሁልጊዜ አኩልነት፣ ሁሉም ትክክል የሆነበት ነው ወይ? እኒህን ሁሉ መመርመሩና ማጥናቱ ጠቀሜታ አለው። ታሪካችን ማወቅ፤ ሕልውናችንን ማወቅ ነው። ይህ፤ ግለሰቦች ስለ አገራቸው ያላቸውን ፅናት ያጎላዋል እንጂ አያደበዝዘውም። ቁምነገሩ፤ በማንኛውም ሰዓት፤ ሕዝቡ፤ በዚህ አንድ ኢትዮጵያዊነቱ ማመኑና፤ ለዚህ እምነቱ ሕይወቱን ለመስዋዕትነት ለማቅረብ መቆሙ ነው። ይህ በሆነበት ሀቅ፤ የውጪ ወራሪም ሆነ የአገር ውስጥ አጉራ ዘለል፤ በሕዝቡና በአገራችን ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት ሊያስከትል አይችልም።

እንኳንስ የረጅም ዘመን ታሪክ ያላት አገራችን ይቅርና፤ ከኛ አገር በኋላ የተመሠረቱ አገሮችም ብዙ ፈተናዎች ገጥሟቸዋል። አገራችን ኢትዮጵያ፤ ከረጅም ታሪኳ ባሻገር፤ ከሌሎች አገሮች ልዩ የሚያደርጉ ብዙ ዕሴቶች አሏት። በዓለም ዙሪያ የምትገኝበት መልክዓምድራዊ አቀማመጥ፣ ለሃይማኖት፣ ለታሪክና ለንግድ ቦታ አዋሳኝነቷ፣ በሰሜኑ የዓለም ዋልታ ተቀምጣ የደቡቡን የዓለም ዋልታ የአየር ጠባይ ወቅቶች መያዟ፣ ለሁለቱ ሃይማኖቶች መቀበል ቀደምትነቷ፣ በሥልጣኔም ቢሆን ቀደምትነት ካላቸው አገሮች መሰለፏ፣ የእኒህ ሃይማኖቶች ተከታዮች፤ በሰላም አብረው የመኖር ረጅም ታሪክ፣ ብዙ የተለያዩ ቋንቋዎች በአገሪቱ መኖራቸው፣ ባጠቃላይም የኒህና ሌሎች ያልተዘረዘሩ ተደማምረው፤ አገራችን ልዩ ያደርጓታል። አገራችን ከሠለጠኑት አገሮች ባትሰለፍም፣ በሀብት ረገድ ከሀብታሞቹ ጎን ባትቀመጥም፤ የራሷ የሆነ ኢትዮጵያዊ ዕሴት አላት። አዎ! ብዙ አጣብቂኝ ሁኔታዎችን አልፋ፤ ለኛ ለዛሬዎቹ ባለተረኞች ደርሳናለች። የመሪዎች ጥንካሬና ድክመት፣ የውጪ አገራት መሰሪ ተፅዕኖና ወረራ፣ ተደጋጋሚ ድርቀትና ረሃብ አገራችንን ብዙ ፈትነዋታል። ይህ ሁሉ በኢትዮጵያዊነታችን ላይ ምንም ዓይነት ተፅዕኖ ሊኖረው አይገባም። ግለሰቦች በረሃብም ሆነ በፖለቲካ ግንዛቤያቸው ምክንያት፤ አገር ለቀው ሊሰደዱ ወይንም ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ሊዛወሩ ይችላሉ። አሁንም፤ ይህ በኢትዮጵያዊነታቸው ላይ ለውጥ አያስከትልም፤ ኢትዮጵያዊነት በአንድ ግለሰብ ፍላጎት፣ በአንድ የታሪክ ወቅት፣ ወይንም በአንድ የታሪክ ቦታ የሚተረጎም አይደለምና! እንኳንስ በአንድ ግለሰብ ይቅርና፤ በአንድ የታሪክ ወቅት በሥልጣን ላይ በተቀመጠ ገዢ አካል አይተረጎምም! በብርሃንም ሆነ በጨለማ የታሪክ ወቅት፤ የኢትዮጵያዊነት ትርጉም በአንድ ግለሰብ የኑሮ ሁኔታ ላይ አይመሠረትም። ኢትዮጵያዊነት ከትውልድ ትውልድ የሚተለለፍ የአገር ባለቤትነት ነው። “ለኔ ይሄ ወይንም ያ ካልሆነልኝ፤ ኢትዮጵያዊነት ለኔ ትርጉም የለውም!” ባይ ግለሰብ፤ ኢትዮጵያዊ አይደለም። ኢትዮጵያዊነት፤ ሌሎች እንዲህ ወይንም እንዲያ ስለሆኑ፤ እኔም እንዲህ ወይንም እንዲያ ልሁን የሚያሰኝ ግንዛቤ አይደለም። ኢትዮጵያዊነት፤ ቋሚ ማንነት ነው። አሳይታም ይወለድ ጋምቤላ፤ ከሺ ዓመታት በፊትም ይኑር ዛሬ፤ ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊ ነው። የተወለደበት አንድ የኢትዮጵያ ልዩ ቦታ ወይንም ወቅት የኢትዮጵያዊነት ትርጉሙን አይቀይረውም። ያለው አንድና አንድ ኢትዮጵያዊነት ነው።

ኢትዮጵያዊነት ከኢትዮጵያ መገኘትን ይጠይቃል። በትውልድም ሆነ በፈቃደኝነት የኢትዮጵያ ባለቤትነትን ይወርሳል። ኢትዮጵያዊነት ለኢትዮጵያ ያለንን ፍቅር ያቅፋል። ይህ ፍቅር በበኩሉ፤ “የኔ ነውና አጥብቄ እቆምለታለሁ!” የሚለውን ያስይዛል። የራስን ጠንቅቆ ማወቅ መሠረታዊ መነሻ ነው። መሪዎችን ተጠይቂ ማድረግ፤ አገርን ከመውደድ የሚመነጭ፤ የውዴታ ግዴታ ነው። አንድን መሪ መውደድም ሆነ መጥላት፤ ስለ አገራችን ያለንን ተቆርቋሪነት እንጂ፤ ተፃራሪውን አያሳይም። አገራችን በአምባገነን ሥር ስለሆነች፣ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ስለመጣ፣ ወይንም በውጪ ወራሪዎች ስለተያዘች፤ ኢትዮጵያዊነታችን አይቀየርም። በርግጥ አገራዊ ግዴታችን እና ተልዕኳችን ይለወጣል። በወራሪዎች ጊዜ፤ ተወላጁ በሙሉ፤ የግል ኑሮንው ትቶ፤ ትጥቅ አንግቶ አገርን ነፃ ለማውጣት መሰለፍን፣ በአምባገነኖች ጊዜ፤ በተገኘው መንገድ ሁሉ እነሱን ከሥልጣን ለማውረድ መታገልን፣ በዴሞከራሲያዊ ስርዓት ጊዜ ደግሞ፤ መንግሥትን ደግፎ መኖር ይሆናል ተልዕኮው። በፋሺስቱ የጣሊያን ወረራ ጊዜ፤ ኢትዮጵያዊያን ከያሉበት ጨርቄን ማቄን ሳይሉ፤ በባዶ እግራቸው ወራት የፈጀ መንገድ ተጉዘው ሕይወታቸውን ሠጥተዋል። ኢትዮጵያዊነት ከታሪክ ጋር የተሳሰረ ነው። አገራችን ከውጪ ወራሪዎች ጋር ካደረገችው ትግል ጋር ይያያዛል። በዚህ ትግል ካስገኘችው ድልና ከደረሰባት ጥቃት ጋር ይያያዛል። ከሕዝቡ እምነትና ባሕል ጋር ይያያዛል። ከወላጆቻችንና ከቀደምቶቻችን ኑሮ ጋር ይያያዛል። ለኢትዮጵያዊያን፤ ኢትዮጵያዊነት፤ የትም ሆን የትም፤ የግል ማንነታችን ዋነኛ አምዱ ነው። ኢትዮጵያዊነት፤ እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝና፤ ኢትዮጵያዊነትን ለማበልጠግ፤ ምን ማድረግ እችላለሁ የሚል ጥያቄ ወደራሳችን እንድናዞር ያደርገናል።

ታሪካችን አንድ ወጥና ሁላችንም እኩል ሊያስደስተን የሚችል አይደለም። ከጥንት ጀምሮ፤ በኛ አገር ብቻ ሳይሆን በየትኛውም አገር፤ ታሪካዊ ትርክቶች፤ የአቸናፊዎችን ትረካ እነሱ በሚፈልጉት መንገድ አጉልተው፤ የነሱን ጀግንነትና የተፃራሪዎቻቸውን ድክመት አግዝፈው፤ የነሱን ድክመትና የተፃራሪዎቻቸውን ጀግንነት አቀጭጨው፤ ያሰፈሩት ነው። እናም የተደረጉ ጦርነቶችም ሆኑ ውጤታቸው፤ በጸሐፊዎች ፍላጎት ይመራል። አንድ ነገር ግን መታወቅ አለበት። ከፋም በጀም፣ በግል ተጠቀምንም ተጎዳንም፣ ትናንትን ልንለውጠው ወይንም ልናስተካክለው አንችልም። እኛ ማድረግ የምንችለው፤ ከትናንት ተምረን፣ ዛሬ በምንችለው የተሻለ ሠረተን፣ ለነገዎቹ ያማረ አድርገን ማሰተላለፍ ነው። የኢትዮጵያ መሪዎች፤ በሕዝቡና በአገሪቱ ላይ ከፍተኛ ሚና ነበራቸው። በአንፃሩ ደግሞ ሕዝቡ መሪዎችን በመደገፍም ሆነ ድጋፉን በመንሳት የተጫወተው ሚና ከባድ ነበር። ከደካማ መሪዎችና ከመጥፎ ሁኔታዎች በኋላ፤ አገራችን በጣም ጠንካራ የሆኑ መሪዎችን አግኝታ፣ ጥሩ ክስተቶች ተተክተው፣ አገር ሰላም ሆኗል። ከአፄ ሱስንዮስ የተተራመሰ የመጨረሻ ዘመናቸው በኋላ፤ አፄ ፋሲል ተተክተው ሰላም ባገር ሰፍኗል። ከጨለማው የዘመነ መሳፍነት በኋላ፤ አፄ ቴዎድሮስ መጥተው፤ አገራችን አንድ ዘመናዊ መንግሥት ኖሯት እንድትጠነክር አድርገዋል። ከፋሽስቱ የጣሊያን ወረራ በኋላ፤ አገራችን፤ በሃያኛው ክፍለ ዘመን፤ ከነበረችበት የአስራ ስምንተኛው ክፍለ ዘመን፤ የአንድ ክፍለ ዘመን ዕመርታ አድርጋ፤ አንድ ክፍለ ዘመን ወደ መቅረቷ እንዳለ ሆኖ፤ ወደ አስራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን ተሸጋግራለች። 

ኢትዮጵያዊነትን ግለሰቦች በሚፈልጉት መንገድ በመምራት፤ የአገራችንን ታሪክ ባጠቃላይ ከመመልከት ይልቅ፤ ለራሳቸው የፖለቲካ ግብና ዓላማ ሲሉ፣ የሚፈልጉትን አንዳንዱን መርጠው በመልቀምና አጉልተው በማሳየት የሚያቀርቡት ትርክት፤ ትክክለኛ የአገራችን ታሪክ አይደለም። ጥሩውም ሆነ ጥሩ ያልሆነው፣ የተጻፈውና ያልተጻፈው ተደምሮ፣ በወቅቱና በቦታው ተመርኩዞ ነው የአገራችን ታሪክ። ታሪክን መምረጥና ማቅረብ አይቻልም። ያ ከሆነ፤ ከላይ እንዳቀረብኩት መግባባቱ ይጠፋል። መግባባት የሌለበት አገራዊነት፤ በአንድነት ወደፊት አይስኬድም። ኢትዮጵያዊነትን ማወቅ፤ ራስን ማሳደግ ነው። በራስ ላይ መተማመንን ማጠንከር ነው። ኢትዮጵያዊነት ከያንዳንዳችን ከራሳችን ይጀምራል። እስኪ እባካችሁ ኢትዮጵያዊነትን እናንተ ተርጉሙልኝ።

ኢትዮጵያ የኢትዮጵያዊያን ነች።

Filed in: Amharic