ከአብይ ጎን አልቆምኩም ወደፊትም አልቆምም…!!!
ጎዳና ያእቆብ
በዛሬዋ እለት ብቻ ሶስት ወዳጆቼ « ኢትዮጵያን ስለሚያወሳልን፡ ከአብይ ጎን እንቆማለን» ሲሉ ሰምቼ ይህ ድግምት ነው እንጂ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል ስል እራሴን ስጠይቅ ውያለሁ። የሚያቀርቡልኝ መከራከሪያ፡ ላለፉት 27 አመታት እናታችንን ኢትዮጵያን « ይቺ ሀገር» እያሉ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት ተዳፍኖ የኖረውን አብይ አህመድ አመዱን አራግፎ፡ እፍ ብሎ መልሶ ሀገራዊ ፍቅርን አቀጣጥሎልናል የሚል ነው። እውነት ነው አብይ አህመድ ኢትዮጵያን አውስቷል፡ አወድሶአል። ያን በማደረጉ አብይ አህመድ ለንሰኅው ቀኖና (penance) ሊሆን ይችላል እንጂ ለሙገሳና «ከእብይ ውጪ ወደውጪ» የሚያስብል ተአምር አይደለም። እንደ ዘኬዎስ ሁሉ አብይ አህመድ በዚህ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን ሲያሸማቅቁ፡ ሲያከስሙ እና ሲያጥላሉ ከነበሩት ጋር የሚስማማ ብቻ ሳይሆን ተባባሪም ነበር፡ ነውም። ሲታሰሩ ሲፈቱ የነበሩት እነ እስክንድር ዛሬም በሰንሰለት እና በእስር ላይ ሆነው በገዛ አንደበቱ « የኢትዮጵያን ህዝብ በድለናል፣ይቅርታ አድርጉልን፣ አሸባሪ ነበርን ያለውን› እና መረጃ ሲያቃብል እና ለስንት ኢትዮጵያዊያን እስር ጉስቁልናና ስደት ምክኒያት የነበረውን አብይ አህመድን ይቅር ብለንሀል ማለት እንኳን ስለሚገባው ሳይሆን ከኢትዮጵያዊያን ትልቅነት እና ጨዋነት የመነጨ ስለሆነ፡ የሱው ኢህአዲግ (ቀዳማዊ) ያሸማቀቀውን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የሱው ኢህአዲግ (ካልዕ – የአሁኑ ብልግና) አረመው እና ንጉስ ሺ አመት ንገስ የሚያሰኝ አይደለም።
ተባብሮ በኢትዮጵያና በህዝቦቿ ላይ አብይ አህመድ ለሰራው በደል ከዚህ በኋላ የ300 አመት እድሜ ቢኖረው እና ብዙ መልካም ነገር ቢያደርግ እንኳን ተባብሮ ለሰራው ጥፋት እና ላተረፈበት ስርዓት ካሳ እንጂ ሂሳብ አወራርዶ ለምስጋና እና ለሙገሳ የሚበቃ ስራ ሊሰራ አይችልም። አብይ አህመድ ኢትዮጵያን ላደቀቀው፡ ኢትዮጵያዊነትስ ያሸማቀቀው ስርዓት አካል ነው። « ለማያቅህ ታጠን፡ ለማያውቅሽ ታጠኝ» ከሚባባሉ ድኩማን አንዱ ነበር ብቻ አሁንም ነው። እክስንድር ነጋን ቄሮን ተናገረብን ነካብን፡ በታከለ ኡማ ምስለኔነት በተቀላጠፈ ሁኔታ ሲከናወን የነበርውን አዲስ አበባን ፊንፊኔ ለማድረግ ያላሰለሰ ጥረትን ለእትዮጵያዊያን በማስረጃ አስደግፎ ሲያሳይባቸው ስለነበር አጋጣሚውን በመጠቀም በጨለማ ቤት ውስጥ ያሰረ ነው። ምግብ ከልክሎ፡ የቆሎ ያለህ ያሰኘ ነው። የሚጠሉትን እና ያጎሳቆሉትን ያህል ይህን ህወሀት እንኳን በእስክንድር ላይ አልፈጸመም። አብይ አህመድ ማለት ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ እንዲሉ፡ ከፈጣሪዎቹ በአነጋገር እንጂ በግብር ከፈጣሪዎቹ የማይለይ በመለስ ዜናዊ መንፈስ የሚጓዝ አረመኔ ስለሆነ ከጎኑ አንቆምም ልቆምም አይቻለኝም።
ውሃ ላይ እንዳለ ኩበት ለምትዋዥቁም ይህንን እራሳቹን ጠይቁ፦ አብይ አህመድ የሚያማልል ቃላት ባለፈ አብይ አህመድ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ያሳደገበት መዋቅር፡ የህግ እና የህገ መንግስት ማሻሻያ ያደረገው ነገር አለ ወይ? ተረኛነት ወይስ ኢትዮጵያዊነት ላለፉት ሶስት አለታት እየጎለበተ ያነበረው? ለውብ ቃላት ድርደራ በስሟ ሊጠሯት እንኳን የሚጸየፉዋት ቀዳማዊ ኢህዲጎች ብሔራዊ መዝሙር ብለው የሰጡ ሲጀምር « የዜግነት ክብር፡ በኢትዮጵያችን ሰፍኖ» ብሎ ይጀምርና፣ « ኢትዮጵያችን ኩሪ እናም ባንቺ እንኩራ» ሲል ይጨርሳል። እውነታው ግን መዋቅሩ ብሄርን እንጂ ዜጋን የማያውቅ ሲሆን፣ ኩሪ ያላትን ኢትዮጵያችን – ያቺ ሀገር ሲሉ ሰንብተዋል። አብይ አህመድንም መንበሩን አደላድሉትና የኩሽ ምድር ብሎላችሁ ያርፋል። በስልጣኑ ላይ እንደ ህብስት ጥሩነት « እንቡጥ ነኝ፣ ለጋ ነኝ» ቢልህ እና አቅም እስኪያጠራቅም ቢያቀማጥልህ እውነት መስሎህ እንደ በሬው ሳሩን አይተህ ገደሉን ሳታይ ተከተልው እና መጨረሻህ ምን እንደሚሆን እምቢኝ ካልክ እየው! ለነገሩ አሁን አሁንማ አዳነች አቤቤ እንዴት ታማብኝ ያለቻቸውው ቄሮች ሳርም ሳያሳዩ (እንደ አብይ ሳያማልሉ)፡ ገደልም ሳይወስዱ ዜጎችን ያለርህራሄ የሚያርዱበት ግዜ ከአብይ ጋር የያዝከው የጫጉላ ሽርሽር ሳያልቅ መምጣት ብቻ ሳይሆን፡ በሙሽራው እየተሸፋፈነና አጥፊው እንዴት ሆኖ አጥፊ ይባላል ብሎ አምኗጉዋሮ ሲፈጥር ስላየህ – ተጨማሪ ዲስኩር ሳያስፈልጋችሁ በልባችሁ መፍራት መጀመራችሁን ባትነግሩኝም አውቀዋለሁ።
የግርጌ ማስታወሻ:-
ከአመት በፊት ያንጸባረቅኩት አቋም ነው
*… ዛሬም ከሀገሬ እንጂ ከአንድ ግለሰብ ጋር አልቆምኩም