>

ምርጫው እና መጪው ጊዜ....!!! (በፍቃዱ ሀይሉ)

ምርጫው እና መጪው ጊዜ….!!!

በፍቃዱ ሀይሉ

ምርጫ2013 ብዙዎቻችን እንደምናውቀው፣ ምርጫ ቦርድም እንዳመነው ፍትሐዊ ባይሆንም ሰላማዊና ተዓማኒነት ያለው ሆኖ አልፏል። ቀጣዩን የቤት ሥራ ማወቅ ነው ቁም ነገሩ!
በበኩሌ ምርጫ ቦርድ በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ  ለመፍጠር የሞከረውን ተቋማዊ ነጻነት እንደ ድልና ዕድል እየቆጠርኩ የምርጫውን ውጤት ግን ከልምድ መቅሰሚያነት የበለጠ ፋይዳ የሌለው አድርጌ ነው የምመለከተው። የምርጫ ዓላማ የብዙኃንን ይሁንታ ያገኘ መንግሥት መመሥረት ነው። ይህ አልሆነም፤ ምክንያቱም ብዙኃን ይሁንታቸውን ለመስጠት የሚያስችላቸው ነጻ፣ ዴሞክራሲያዊና በመረጃ ላይ የተመረኮዘ ፉክክር አላደረጉም። ገዢው ፓርቲ ሥልጣኑንና የሕግ ክፍተቶችን ተጠቅሞ ፍፁም የበላይነቱን አረጋግጦበታል። ይህ እንግዲህ በፖለቲካ ቀውስ ምክንያት በሒደቱ ያላለፉትን ዜጎችና ድርጅቶችን ጉዳይ ከግምት ውስጥ ሳናስገባ መሆኑ ነው። በዚህ ዓይነት ባለፈው ብቻ ሳይሆን በመጪዎቹ ምርጫዎችም ተስፋ የሚጥል ትውልድ ማፍራት አይቻልም። በጦርነትም፣ በአመፅም ዴሞክራሲ አይወለድም። ዴሞክራሲ ይገደኛል የሚሉ ሰዎች በሙሉ ከዛሬው ተጨንቀው ማሰብ የሚኖርባቸው ለዚህ ነው።
መጪው ጊዜ የ #አሳታፊ_ሪፎርም ጊዜ መሆን አለበት። ከዚያ በፊት ግን #ዕርቀ_ፖለቲካ ያስፈልጋል።
ዕርቀ ፖለቲካ ስል በፖለቲካ ልኂቃን ዘንድ ሰላም ማውረድን የሚመለከት ጉዳይ ነው። በዚህ ርዕስ ላይ ከሰሞኑ በሰፊው እመለስበታለሁ።
አሳታፊ ሪፎርም ስል ደግሞ የዴሞክራሲ ሕግጋት እና ተቋማት እንዴት ሪፎርም ይደረጉ የሚለውን ማለቴ ነው። የፖለቲካ ልኂቃን እና የድርጅት መሪዎች በጋራ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሪፎርም ማንዴት ተሰጥቷቸው የዴሞክራሲ ተቋማትን መሪዎች፣ የሕግጋት ለውጦችን የሚመክሩበት፣ የተቋማትን መልሶ ማዋቀር ላይ የሚወያዩበት እና በቅርብ የሚመረምሩበት ዕድል ተሰጥቷቸው መልሶ ማዋቀር ሥራ ካልተሠራ በስተቀር፣ ምርጫዎች ዘለዓለም ዓለም ሥልጣን በያዘው አካል አሸናፊነት የሚጠናቀቁ እቃቃዎች ሆነው ይቀራሉ።
መቀየር ካለባቸው ሕግጋት መካከል የምርጫ ስርዓቱ አንደኛውና ዋነኛው ነው። ከታች ያስቀመጥኳቸው ስክሪንሾቶች ከምርጫ 2002 ውጤት እወጃ በኋላ ነሐሴ 2010 ከጻፍኩት ጽሑፍ የወሰድኩት ነው። አንድ ዓይነት ችግር። የምርጫ ስርዓቱ፣ ድምፆች እንዲባክኑ ይዳርጋል። ተቃዋሚዎችን የመረጡ ሚሊዮኖች ድምፅ ከንቱ ሆኖ የሚቀርበት ስርዓት በተለይ ለኛ አይጠቅመንም።
Filed in: Amharic