>

ኮለኔል መንግስቱ ለሱዳኑ መሪ ኑሜሬ እንዲህ አሉ...! (ሳይሞን ሩፋኤል)

ኮለኔል መንግስቱ ለሱዳኑ መሪ ኑሜሬ እንዲህ አሉ…!

ሳይሞን ሩፋኤል

 “መንግስታት ይመጣሉ ይሄዳሉ፤ እኛም እናልፋለን። የሱዳንና የኢትዮጵያ ህዝብ ግን ከእኛም በኋላ ይኖራሉ። ስለዚህ ወደደንም ጠላንም ለዘለአለም አብረን ስለምንኖር፤ ህዝቡን ማቀራረብ እንጂ ማራራቅ የለብንም። ወዳጅነቱን መገንባትና ማጠናከር እንጂ ጠላትነትንና ጥላቻን መዝራት የለብንም። አንድ ሰው ሚስቱን ሊመርጥና ሊያገባ ይችላል፤ ካልተስማሙም ሊፈታ ይችላል። ጎረቤቱን ግን ሊመርጥ አይችልም። ተስማሙም አልተስማሙም የግድ በጉርብትናቸው ይኖራሉ። የእኛም ሁኔታ ይኸው ነው። ዋናው ቁም ነገር አብረን እንድንኖር እስከተገደድን ድረስ ለምን አንወዳጅም? ለምን አንጠቃቀምም? ለምን አንተባበርም? ለምን አብረን አናድግም? ለምን እንጎዳዳለን? ለምን እንጠፋፋለን?”
“ለህዝባችን ጥቅም ነው??? አይደለም! ለጠላቶቻችን ጥቅም ነው እንጂ የኢትዮጵያም ሆነ የሱዳን ህዝብ ከዚህ ጥፋት ምንም የሚጠቀመው ነገር የለም። የሌሎች አረብ ሀገሮች ተፅእኖ እንዳለባችሁ ደጋግማችሁ ነግራችሁናል፤ እኛም እናውቀዋለን። በእኔ እምነት አሳሳቢ የሚሆነው የግብፅ ተፅእኖ ነው። ሌላ ክብደት የሚሰጣት አገር ሳኡዲ አረቢያ ናት። ግን እሷ ከርቀትም ከሌላውም አንፃር አስጊነቷ እስከዚህ አያሳስብም። ግብፅ ግን ከሱዳን ጋር ኩታ ገጠም የየብስ ጠረፍ ያላት ከመሆኗም በላይ በቅኝ ግዛትነት ይዛት ስለነበረ የህዝቡን ጠባይ፣ የመሬቱን ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥና ሌላውንም ስትራቴጂክ ሁኔታ ሁሉ አበጥራ ታውቀዋለች። ‘የአረብ ተፅእኖ ስላለብን የኤርትራ ተገንጣዮች በሚመለከት እርምጃ ለመውሰድ እእነቸገራለን’ ስትሉን ለእኔ የሚታየኝ የግብፅ ተፅእኖ ብቻ ነው።”
“አሁን ዋናው ጥያቄ መሆን ያለበት የግብፅን ተፅእኖ እንዴት እንቋቋመው? የሚለው ነው። እኛኮ ትልቅ መሳሪያ አለን – የዓባይ ውሀ!  ኢትዮጵያ እና ሱዳን የራስጌ አገር ሁነው ድርሻቸውን አያገኙም! እናም መብታችንን ለመጠቀም ልናስፈራራ እንችላለን። መጠቀምም እንችላለን። ዓለምአቀፍ ህግም ይደግፈናል”
“እነሱ ማንንም እኛንም ሆነ እናንተን ሳያማክሩ ነው የአስዋንን ግድብ ገንብተው ውሃውን ለብቻ የያዙት። ኢትዮጵያ በወቅቱ ይህ ተግባር ህገወጥ እንደሆነና በፈለገች ጊዜ በመብቷ ፣ በድርሻዋ ከመጠቀም እንደማያግዳት ለግብፅም ለመላው ዓለምም አሳውቃለች። ሱዳንም ብትሆን በተፅዕኖ የተጣለላትን ትርፍራፊ እንጂ ተገቢና ህጋዊ ድርሻዋን እንደማታገኝ ከእኔ የበለጠ እርስዎ አጥርተው ያውቁታል። እናም ከጉርብትናው፣ ከደም ዝምድናው ከሌላው ከሌላው በተጨማሪ ይኼ ኢትዮጵያንና ሱዳንን አንድ ሊያደርጋቸው ይገባል ባይ ነኝ። ይኼን አቋም ከያዝን ችግሮቻችንን ለማስወገድ የማንንም ተፅዕኖ ሳንፈራ የፈለግነውን እርምጃ መውሰድ እንችላለን። ከዚያ አልፈው መሳሪያ መማዘዝ ቢፈልጉ የኢትዮጵያ ሰራዊት ለመዋጋት ዝግጁ ነው፤ ዐቅሙም አለው።”
ምንጭ: ያልታሰበው የህይወቴ ፈታኝ ጉዞ  እና የኢትዮጵያ አብዮት ተሳትፎዬ (በሌ/ኮለኔል ብርሃኑ ባይህ፤ ገፅ 595-596)
Filed in: Amharic