>

ግፍ አይፈሬው አቢይ አህመድ በአማራው ላይ ጢባጢቤውን ቀጥሏል! (ዳግማዊ ጉዱ ካሣ)

ግፍ አይፈሬው አቢይ አህመድ በአማራው ላይ ጢባጢቤውን ቀጥሏል!

ዳግማዊ ጉዱ ካሣ


ዝም ማለት ስላላስቻለኝ እንጂ በዚህ የባቢሎን ዘመን ተናግሬ እደመጣለሁ፣ ጽፌም እነበባለሁ ብዬ አይደለም፡፡ ይሁንና ቢያንስ በሕይወት መኖሬን ለግለ ታሪኬ ለማስመዝገብ ስል አሁን ከሰማሁት ድንገተኛ ግን የሚጠበቅ አሳዛኝ መረጃ በመነሳት ጥቂት ልናገር ፈለግሁ፡፡ የራሔሎ ልጅ አቢይ ራያንም እያስመታው ነው…

በነገራችን ላይ የመጨረሻውን ተሸናፊ አላውቅም፡፡ የመጨረሻውን አሸናፊ ግን በሚገባ አውቃለሁ፡፡ ይህን አሸናፊ የማውቀው ከዛሬ 30 ዓመት ገደማ በፊት ጀምሮ ነው፡፡ አትደናገጡ፡፡ እንደሰው አለመሸበር አስቸጋሪ ቢሆንም በምትሰሙት ሰቅጣጭ ዜና ሁሉ አትሸበሩ፡፡ ሁሉም ሊሆን የግድ ነው፡፡ ልጅ ያለምጥ፣ ነፃነትም ያለመስዋዕትነት አይገኙም፡፡ ገና ብዙ የሚዘገንኑ ሀገራዊና ማኅበረሰብኣዊ ክስተቶችን እናያለን፡፡ ቃየሎች በአቤሎች ላይ ጭካኔያቸው ወደር አጥቷል – ዘመናቸው ነው፡፡ ዘመኑን በአግባቡ የማይጠቀም በኋላ ይቆጨዋል፡፡እነሱም የባሕርይ አባታቸው ሊቀ ሣጥናኤል በሰጣቸው ጊዜ ባለመጠቀማቸው ከሹመትና ዕድገት እንዳያግዳቸው ሰግተው ነው እንዲህ የሚቅነዘነዙት፡፡ ሰይጣን ግዘፍ ነስቶ አቢይንና የወያኔን ርዝራዥ ጌታቸው ረዳንም ተመስሎ በአካል መጥቶብናል፡፡ ለተወሰነ ጊዜ ቻል ማድረግ ነው፡፡ ንግርት አይቀርም፡፡

አቢይ አህመድ አማራውን ለማስጨፍጨፍ ከባልደረባው ከሽመልስ አብዲሣና መሰል የኦሮሙማ ፍልስፍና አራማጆች ጋር እያደረገ ያለውን ሤራ በጥሞና እየተመለከትን ነው፡፡ ያቺ የሽመልስ ምሥጢራዊ የኦሮምኛ ንግግር ሥራዋን እየሠራች ነው፡፡ “አባይን ተሻግረን በማሳመንም በማደናገርም ብዙ እየሠራን ነውና ዝም ብላችሁ ውጤቱን ብቻ ጠብቁ” ብሎ የተናገረው ንግግር መሬት ላይ ጠብ አላለም፡፡ እውን እየሆነ ነው፡፡ ጅሎች ደግሞ እየተባሉ ነው፤ ግዴለም ይባሉ፡፡ ለምን ቢሉ ሰው በፈለገው መንገድ እንደፈለገው ሲጓዝ ደስታ ይሰጠዋልና ይብላኝ ለምሥኪኖች እንጂ ጥጋበኞችስ እንደፈለጋቸው ይሞሻለቁ፡፡ ግን ግን ከወዲያም ከወዲህም ያሉ የዋሃን ያሳዝናሉ፡፡ ይህ የሰይጣን ልዑክ ኢትዮጵያንና አማራን ድራሻቸውን ለማጥፋት የጀመረውን ቁማር አፋፍሞ ቀጥሏል፡፡ የራሱን መቀበሪያ ጉድጓድም እያራቀው ነው፡፡ በቆፈረው ጉድጓድ ራሱ ይገባበታል፡፡ 

ዛሬ ከኮረም አቅጣጫ የምንሰማው ትንግርታዊ የማይታመን ክስተት ብዙዎቻችንን መዳፋችንን አፋችን ላይ ጭነን እንድንደመም አድርጓል፡፡ ይህ አቢይ መከላከያን ከመቀሌ ማስውጣቱ የፈጠረብንን አግራሞት ሳንጨርስ ዛሬ ደግሞ የአማራ ልዩ ኃይልና መከላከያ ኮረም ግራካሱ አካባቢ ወያኔን ድባቅ እየመቱ ባሉበት ሁኔታ ወደኋላ እንዲያፈገፍጉ ትዕዛዝ በመስጠት እስከቆቦ ድረስ ያለውን ቦታ ለወያኔ አስረክቧል፡፡ ወያኔዎች ራያን ከአቢይ በነፃ መረከባቸው በራሱ ባልከፋ – እንዲህ ማድረጉ ብዙ አንድምታ አለው፡፡ አንድም አማራን ለማስመታት፣ አንድም ጌቶቹን እነአሜሪካንን ለማስደሰት፣ አንድም ኦነግን በአማራና በትግሬ ላይ ለማፈርጠም… ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም፡፡ የወያኔን ጠባይ ጠንቅቆ የሚያውቀው አቢይ የዚያን አካባቢ አማራ በወያኔ የበቀል ጅራፍ እንዲገረፍ በመፈለጉ ይመስላል ይህን ድንገተኛ ትዕዛዝ ያስተላለፈው፡፡ ወያኔ ለመከላከያ ሥጋ ሸጠሃል ብሎ ንጹሕ የሉካንዳ ቤት ሠራተኛን መሆኒ ላይ በቢላዎ ማረዱን እየሰማን፣ ለመሀል አገር ሰው የመጠጥ ውኃ ሰጥታችኋል ያላቸውን ሣምራውያን ትግሬዎችን ወያኔ በጥይት እንደፈጃቸው እየሰማን፣ አካባቢያችሁን አረጋጋችሁ ብሎ ትግሬ ወጣቶችን ወያኔ በጩቤ ማረዱን እየሰማን፣ ባልሽ የት ሄደ ብሎ ንጹሕ ሴት ከሦስት ልጆቿ ፊት አንገቷን ማረዱን እየሰማን፣ በውሻ ዕብደት ተለክፎ ያገኘውን ሁሉ በመግደል የሚረካ ወያኔ ስንትና ስንት የጭካኔ ተግባር እየፈጸመ መሆኑን እየሰማን… አሁን ደግሞ የራያን ሕዝብ ለዚህ ጭራቅ አጋልጦ ሲሰጥ የዚህ አቢይ የሚባል ሰውዬ ዐረመኔነት ገደብ እንደሌለው እንረዳለን፡፡ ይህ አስመሳይ ሰው በኮረምና አላማጣ ሕዝብ እያስፈጀ አዲስ አበባ ላይ ግን ችግኝ ይተክላል፡፡

ለማንኛውም አማራዎች ከብአዴን ዕቅፍ ውጡ፡፡ “ዘጠኝ ሞት መጣ” ቢለው “አንዱን ግባ በለው” አለው ይባላል፡፡ የጊዜ ጉዳይ እንጂ በአቢይም ሆነ በወያኔ መሞታችሁ ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህ ሞት ያው ሞት ነውና አስገዳያችሁን ባለመታዘዝ አንዱን ሞት አጥብቃችሁ ታገሉት፡፡ ፋኖና ልዩ ኃይልም የሤረኞችን ትዕዛዝ በማክሸፍ ሕዝባችሁን አድኑ፤ ርስታችሁንም ጠብቁ፡፡ አማሮች በሕይወት መኖር ከፈለጋችሁ በራሳችሁ የጎበዝ አለቃ እየተመራችሁ ኅልውናችሁን አረጋግጡ፡፡ ይህን የምለው እንደሰው የሚሰማኝን ለመተንፈስ ያህል እንጂ የመጨረሻው አሸናፊ ኢትዮጵያዊነት መሆኑን ዘንግቼው አይደለም፡፡

ሶማሊያና ቬትናም ያጥረገረጓት አሜሪካም የራሷን የቤት ሥራ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ከኅያው እግዚአብሔር ትቀበላለች – የተጻፈላት አለ፡፡ የግብጽም፣ የኦህዲድም ጀምበር እየጠለቀች ናት፡፡ ዕድሜ ለአቢይና ለምዕራባውያን ሕወሓት ለጥቂት ጊዜ መንፈራገጧ አይቀርም፡፡ የኢትዮጵያ ታሪካዊ የውስጥና የውጪ ጠላቶች ኅብረት ፈጥረው ለጊዜው ወጧ እንዳማረላት ሴት በደስታ እየፈነጩ ናቸው፡፡ የራሄልን ዕንባ ያበሰው አምላከ ኢትዮጵያ ግን ኢትዮጵያን ጥሎ አይጥላትምና ጠላቶቻችንን በራሱ ጊዜ ምንዳቸውን ይሰጣቸዋል፡፡ ግን በርትተን ወደርሱ እንጸልይ፡፡ አልዓዛርን በአራተኛው ቀን ከሞት ያስነሳው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሀገራችንንም ከሞት አስነስቶ ትንሳኤዋን በቅርብ ያሳየናል፡፡ ግፈኞች ግን ለመጪው ትውልዳቸው በማሰብ ለከት ካጣው ዕብሪታቸውና ከግፋቸው እንዲቆጠቡ ምከሯቸው፡፡ ሤራ ዞሮ ዞሮ ሤረኛውንም መጉዳቱ አይቀርም፡፡ በሤራና በሸር ያለፈለት የለም፡፡ በሤራና በሸፍጥ የተወሰነ ድል ለተወሰነ ጊዜ መጎናጸፍ ይቻል ይሆናል እንጂ መጨረሻው እንደማያምር በታሪክ የተረጋገጠ ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ከትህነግ የበለጠ ምሣሌ የሚሆን አይኖርም፡፡ ትህነግ በዚያ ሁሉ የተንኮልና የሸር ጉዞዋ ያተረፈችው ያየነውን ሁሉ መቅሰፍት ነው፡፡ የቀን ጉዳይ ነው፡፡ ቀኑን ጠብቆ ሁሉም የጁን ያገኛልና ዛሬ ቀን ሰጠን ብላችሁ አማራን በተገኘበት የምትጨፈጭፉና የምታስጨፈጭፉ ወገኖች ለራሳችሁ ስትሉ ከዚህ ዕኩይ ድርጊታችሁ ብትቆጠቡ መልካም ነው፡፡ የሤራ ፖለቲካ ራስንም ጭምር ያጠፋልና እነአቢይ ወደኅሊናቸው ቢመለሱ እነሱም ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ ከፍ ሲል ለመጠቆም እንደሞከርኩት እነአሜሪካንን እርሱ ፈጣሪ የደገሰላቸው ስላለ የርሱን ፍርድ መጠበቅ ነው፡፡ ኃያል ፈጣሪ ብቻ ነው፡፡ የሥጋ ለባሽ ኃያልነት ጊዜያዊና ኃላፊም ነው፡፡ ኢትዮጵያም በዘመኗ ከአራት የዓለም ኃያላን ሀገራት አንዷ ነበረች፡፡ የማያልፍ የለም – እንደቃሉ ሰማይና ምድርም ጭምር፡፡ በተረፈ አይዞን!! ጊዜው ቅርብ … እጅግ በጣምም ቅርብ ነው፡፡ ከክፋትና ከሀሰት መራቅን ግን እንለማመድ፡፡…

EMAIL: ma74085@gmail.com

Filed in: Amharic