>
5:15 pm - Friday May 11, 5618

በእነ እስክርን ጉዳይ - ዐቃቤ ሕግ "ዛሬም ምስክር የለኝም" ማለቱ ተሰማ...!!! (ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ)

በእነ እስክርን ጉዳይ – ዐቃቤ ሕግ “ዛሬም ምስክር የለኝም” ማለቱ ተሰማ…!!!

ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ

የግፍ እስረኞች እነ እስክንድር  በችሎት ለተገኙ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል…!!! 
 
በግፍ  እስር ላይ የሚገኙት የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ  አመራሮች እስክንድር ነጋ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ አስቴር ስዩምና አስካለ ደምሌ በዛሬው ዕለት  ሐምሌ 8 ቀን 2013 ዓ.ም በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የፀረ ሽብርና ሕገ መንግሥት ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በአካል ቀርበዋል።
… በቀደመ ቀጠሮ ባለፈው ትእዛዝ ከፍተኛ ፍርድቤቱ ለዐቃቤ ሕግ በእነ እስክንድር ላይ በግልጽ ችሎት ለዛሬ ምስክሮችን እንዲያቀርብ ለመጨረሻ ጊዜ ማዘዙ ይታወሳል።
… ይሁን እንጂ ዛሬም ዐቃቤ ሕግ ምስክር ለማቅረብ የደኅንነት ስጋት አለብኝ፤ ስለዚህ ለምስክሮቼ  ከመንግሥት የሎጅስቲክስ፣ የበጀት እና ሌሎች ቁሳቁሶች እስኪሟሉልኝ ድረስ ምስክር ማቅረብ አልችልም። ስለዚህ ፍርድ ቤቱ በድጋሚ ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ይሰጠኝ ዘንድ አመለክታለሁ በማለት የፍርድ ቤቱን ትእዛዝ ጥሶ የተለመደ ጥያቄውን አቀርቧል።
የግፍ እስረኞች  ጠበቆች በበኩላቸው ዐቃቤ ህግ ምስክሮችን እንዲያቀርብ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል ። ይሁን እንጂ ዐቃቤ ህግ የፍ/ቤት ትዕዛዝ አላከበረም።  በቸልተኝነት የትዕዛዝ ጥሰት ፈፅሟል። ከዚህም በተጨማሪ አንድ አመት ሙሉ ደንበኞቻችን ዐቃቤ ህግ ምስክሮች ማቅረብ ባለመቻሉ በፍትህ እጦት ለእስር ተዳርገዋል ። አመቱን ሙሉ የተለያየ ምክንያት በማቅረብ ዐቃቤ ህግ የፍርድ ቤቱን ሂደት ሆን ብሎ ሲያዘገይ ቆይቷል። በመሆኑም የዐቃቤ ሕግ ጥያቄው የህግም የሞራልም መሰረት ስለሌለው መዝገባቸው ተዘግቶ በነፃ እንዲሰናበቱ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።
የግራና ቀኝ ክርክሩን ያደመጠው ፍ/ቤቱ፤ በምስክሮች ደህንነት ላይ ለአንድ አመት ክርክር ሲያካሂድ መቆየቱን አስታውሷል። ስለሆነም  ዐቃቤ ህግ ያቀረበው አቤቱታ ቀጠሮ የሚያስቀይር ሆኖ አላገኘሁትም በማለት ዐቃቤ ህግ አሉኝ የሚላቸውን ምስክሮች ነገ ሐምሌ 9 ቀን 2013 ዓ.ም
  እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ተሰጥቷል።
… በፍርድ ቤቱ ትእዛዝ መሰረት ምስክር የመስማት ሂደቱ ባጠቃላይ የተቀጠረው ዛሬን ጨምሮ ለተከታታይ አምስት ቀናት በመሆኑ ነገም ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ጀምሮ ይቀጥላል።
… አዲስ አበቤ ሰምተሃል። በመሆኑም ሁሉም አዲስ አበቤ በነገው ዕለት ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት በፊት በከፍተኛ ፍርድ ቤት በመገኘት ለእነ እስኬው ድጋፉን ይሰጥ ዘንድ ጥሪ ቀርቧል።
… በተጨማሪም እነ እስክንድር ነጋ አቅርበው የነበረውን የቂሊንጦ እስር ቤት አያያዝ በተመለከተ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ሰጥቷል።
… በመሆኑም ከዚህ ቀደም ምግብ ከምታደርሰዋ ግለሰብ ውጭ ሌሎች ጠያቂዎችን አናስተናግድም፣ ከባለቤቱ ጋር በውጭ በስልክ አናገናኝም፣ የፀበል፣ የቅባ ቅዱስ የመሳሰሉ ፈዋሽ የእምነቱን መንፈሳዊ ነዋየተ ቅዱሳት አናስገባም፣ የመጽሐፍ፣ የመጽሔት እና መሰል ጉዳዮችን አናስገባም በማለት እስር ቤቱ ይዞት የነበረው ፀረ ኦርቶዶክሳዊነት አቋም እንዲሻርና ተጠርጣሪዎች በቂ አገልግሎት እንዲያገኙ ፍርድቤቱ ወስኗል። ጸበል አትጠጡ ። ሆሆይ። ጉደኛ መንግሥት እኮ ነው በማርያም።
… ከወትሮው በተለየ መልኩ ዛሬ ከፍተኛ ቁጥር ያለው አዲስ አበቤ በልደታ ከፍተኛ ፍርድቤት ተገኝቷል። ፍትህ አዳራሽ ሞልቶ (ችሎት የሚካሄድበት) በቅጥር ግቢውና ውጭ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ደጋፊ ዝናብ ሳይበግረው በፅናት የእነ እስክንድር ዓላማ አጋር መሆኑን አሳይቷል።
የግፍ እስረኞች እነ እስክንድር  በችሎት ለተገኙ ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል ።
… ከአሸባሪዋ ህወሓት፣ ከአውዳሚዋ ህወሓት ጋር የሚደራደረው መንግሥት ከእነ እስክንድር ጋር ጠቡ ምን እንደሆነ ከሳሽ ሆኖ እንዲቀርብ የተደረገው ዐቃቤ ሕጉ ራሱ ሊገባው እንዳልቻለ የፍርድ ቤት አካባቢ ሰዎች ይናገራሉ።
• ዐቃቤ ሕጉ ከነገ ጀምሮ በተከታታይ አራቱንም ቀናት የታዘዘውን ምስክሮች ማቅረብ ካልቻለ ፍጻሜው ፍርድ ቤቱ ፋይል ዘግቶ እነ እስክንድርን በነፃ ማሰናበት ብቻ ነው ተብሏል።
• ድል ለዲሞክራሲ
Filed in: Amharic