>

ጆሮ ያለው ይስማ አቢይ አማራውን ከድቶዋል  (ሲናጋ አበበ)

ጆሮ ያለው ይስማ አቢይ አማራውን ከድቶዋል

ሲናጋ አበበ


በአቢይ መንግሥት ላይ የዘመተው የትግራይ ሀይል በማይካድራ ላይ የኢትዮጰያ ጦር በወገን መሐል ነኝ ብሎ ዘና ብሎ ባደረበት ሰዓት ክህደትና ባንዳነት ባህሪው የሆነው ለዝንተ ዓለም ይህቺን አገር እገዛለሁ ብሎ ሲቃዥ የነበረው ሕውሀት ሌሊት በውድቅት ጦርነት ከፍቶ ወደ አንድ ሺህ የሚሆኑትን አማሮች በመብረቃዊ ጥቃት ለወሬ ነጋሪ ሳያስተርፉ ጨርሰዋቸዋል፡፡ እጅግ አረመናዊና አህዛባዊ ድርጊት፡፡በምንም መልኩ ክርስቲያን ነው ተብሎ ከሚገመት አገር መታየቱ ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው፡፡

        በዚህ የጭካኔ ተግባሩ ተወግዶ በሕግ ማዕቀፍ ሥር እንዲስተዳደር የፌዴራል መንግሥቱ አፀፋውን እርምጃ ወስዶ በሶስት ሳምንት ውስጥ አመድ አድረጎት፤ የውጭውን ተጽዕኖ ለማርገብ ክልሉን ለቆ ወጥቶዋል፡፡ የቀጣዩ ሂደት ዝርዝር የሚታወቅ በመሆኑ አንባቢን ላለማሰለቸት አልፌዋለሁ፡፡

           አሜሪካ ዘላለሙን በችግራችን ጊዜ የማትደርስ ጥቅሙዋንና በአካባባዋ ባሉ የጥቅም አሳዳጆች ቡድኖች ተጸእኖ የምትወድቅ፤ በመርህ የማትመራ አገር መሆኑዋን በተደጋጋሚ በኢትዮጵያ ላይ ከወሰደቻቸው ውሳኔዎች ላይ በመመርኮዝ ድምዳሜ ላይ መድረስ እንችላለን::

          ኦባማና አስተዳደሩ የለየለትን የመለስ አምባገነናዊ የአናሳ ብሄረሰብ መንግስት በሕዝብ ምርጫ በሥልጣን ኮርቻ ላይ የተፈናጠጠ ዴክራሲያዊ አስተዳደር የተዘረጋበት አገር ብሎ ዓይኑን በጨው አጥቦ  አቆለጳጵሶ  የመሰከረለት እንደነበር የቅርብ ቀን ትዝታችን ነው፡፡ ከኦባማ ርዝራዦች ተርፈው ለበድኑ ባይድንም ለማገልገል ከተሾሙት ውስጥ ሱዛን ራይስ የተባለችው ከመለስ ጋር እጅግ በጣም በተሳሰረ መልኩ የቅርብ ግንኙነት የነበራት ፤መለስ ከመቃብር ሆኖ ይመለከታትና ይገስጻት ይመስል በታማኝነት የሱን አጄንዳ “ከጳጳሱ ቄሱ” እንዲሉ የባይደንን አስተዳደር ቀስፋ ይዛ ይህ የጃጀ ፕሬዚዴንት ኢትዮጵያን በማስፈራራት በኢትዮጵያ ላይ ጦሩን እንዲሰብቅ እያደረገችው ነው፡፡

     ዱቄት ከሆነው አሸባሪ ጁንታ ጋር ቁጭ ብላችህ ተደራደሩ፤ የአማራ ልዩ ሀይል ከቀድሞው የአማራ ግዛቱ ከወልቃይትና ጠገዴ አና ከራያ ለቆ እንዲወጣ በማለት እያስፈራሩና ማዕቀብ እየጣሉ ሊጎዱን ተነሳስተዋል፡፡ ዱቄቱ አፈር ልሶ በመነሳት የትግራይን ሕጻናቶች፤ ገበሬዎችንና ሽማግሌዎች ሳይቀር አሰልፎና አስታጥቆ ግዛቴን አስመልሳለሁ ብሎ ሲዘምት የአማራው ልዩ ሀይል አይቀጡ ቅጣት አድርሶበት ጠላት ሬሳ በሬሳ ሆኑዋል፡፡

      የአሜሪካንና የአውሮፓውያን ተጽእኖ እየከበደው የሄደው አቢይና ፓርቲው ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ሆኖ ከመቁዋቁወቀም ይልቅ የአማራው ልዩ ሀይልና የመከላከያ ሠራዊት በራያ አካባቢ ድል በድል በሆነበት ሰአት  ጦርነቱን አቁሞ እንዲመለስ ትአዛዝ ማስተላለፉ ትልቅ የክህደት ሥራ መሆኑ ይታያል፡፡ የአማራው ልዩ ሀይልና የመከላከያ ሠራዊት የያዘውን መሬት ለቆ እንደወጣና የጠላት ሀይል እንዲቆጣጠረው ማድረጉ የክህደትም ክደት ነው ፡፡ ለልዩ ሀይሉና ለጦሩ የተላለፈው የአፈግፍጉ መልዕክት ያልደረሰው  የወገን ሀይል በወያኔ ጨካኝ ቡድን እንዲጨፈጨፍ የተፈረደበት ነው ፡፡ ለዚህ እልቂት ተጠያቂው አቢይና አቢይ ብቻ ናቸው፡፡

       አቢይ ከያዘው ሥልጣን በላይ የሚበልጥበት የሌለውና ፤በሕዝብ ደም የሚነግድ መሆኑን ከዚህ በፊት በየክልሉ ዘረ ተኮር ጭፈጨፋ የተመለከትናቸው ህያው ምሥክሮች ናቸው፡፡

      የአማራው ክልል መስተዳድር፤ የአማራ ብህራዊ ንቅናቄ፤የመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት በአሜሪካና በአውሮፓ ያሉ አክቲቪስቶች ፤የአማራ ድርጅቶች የወያኔን ጥቃት ለመቀልበስ የክተት አዋጅ አውጀዋል፡፡

      ከአማራው ልዩ ሀይል ቆራጥ እንቅሳቃሴ በተጨማሪ ለአቢይ ሌላ እንቅልፍ የሚነሳው የአማራው ክልል የግዛት ይዞታና እምቅ ሀብት በኢትዮጵያዊነቱ የማይደረደር ቆራጥ መሆኑ ለአቢይና ለኦሮሞው ብልጽግና የኦሮሙማ ምሥረታ ህልሙን ስለሚያጨልምበት በአጋጣሚው በመጠቀም አማራውን ለመደቆስ እነሽመልስ አብዲሳ በድብቅ የሚዶሉቱትን  ተግባራዊ ለማድረግ ይመስላል፡፡

       በቃ ኢትዮጵያ የጦርነት አውድማ ለመሆን እየተገፋፋች ስለሆነ የሚመጣውን መጋፈጥ ነው፡፡

        ኢትዮጵያ ምንጊዜም እግዚአብሔር የማይርቃት አገር ነች፡፡ በሱ ሐይል ትታደጋለች እስከዚያው ግን ጽዋው መራራ መሆኑ ለሁሉም ግልጽ ይሁንለት፡፡

                                                 

Filed in: Amharic