>

የህውሓት መንታ ሽንፈት....!!!! (አሳዬ ደርቤ)

የህውሓት መንታ ሽንፈት….!!!!

አሳዬ ደርቤ

 

*…. የምር ግን ብልጽግና ትሕነግን ደምስሶ ኢትዮጵያን አሸናፊ ማድረግ ይፈልጋል ወይ? ‹‹ታግለናል›› ከማለት ባለፈ ‹‹ድል አድርገናል›› ለማለት የሚያስችል ዘመቻ እያካሄደ ነው ወይ?
ጀግኒት እንዳለችው ‹‹ክልሉን ለማስከበር የአማራ ልዩ ሃይልና ሚኒሻ ከበቂ በላይ ነው፡፡ የኢትዮጵያን አንድነት ለማሳየት ግን የሁሉም ክልል ደጀንነትና ሕብረት ያስፈልጋል፡፡››
ትሕነግ በሽፍትነት ከኖረበት የደደቢት በረሃ ወጥቶ ቤተ-መንግሥት ውስጥ እስኪሸብት ድረስ አማራን በጠላትነትና በአሀዳዊነት ሲፈርጅ ብሎም  ይሄን ሕዝብ ይታገሉ ዘንድ ብሔር ብሔረሰቦችን ሲያደራጅ የኖረ ድርጅት ነው፡፡
የብሔር ብሔረሰቦችን ማንነት ማስከበር ቀርቶ ቁጥራቸውን በውል ማወቅ ተስኖት ‹‹ከሰማንያ በላይ›› እያለ አማራ ጠልነት የፌደራሊስትነት መገለጫ ይሆን ይመስል እልም ያለ በዝባዥ አሃዳዊ መንግሥት መስርቶ ሲዘርፍና  ሲያወናብድ የኖረ ፓርቲ ነው፡፡
በጌታቸው ረዳ አንደበት ‹‹እሳትና ጭድ›› ተብለው በተገለጹት ሕዝቦች ትግል ከፌደራል ከተባረረ በኋላም ሲነዛቸው የነበሩ ፕሮፖጋንዳዎች የጠቅላይ ሚኒስትሩን ማንነት ቀምተው በአማራነት የሚፈርጁ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብን ለእርስ በእርስ መጠፋፋት የሚያዘጋጁ፣ ከአማራዎች ይልቅ ሱዳኖች ወዳጁ መሆናቸውን የሚያውጁ ነበሩ፡፡
የመከፋፈል ፍልስፍናውን በማጠናከርም ከግብጽና ሱዳን የሚላክለትን ድርጎ ኢትዮጵያን መሰነጣጠቅ ለሚፈልጉ ድርጅቶችን ሲያካፍልና ሲያስታጥቅ ነበር፡፡
ኢሳያስን ወዳጅ ማድረግ እንደማይቻል ሲገባውም ኤርትራውያንን ‹‹ቆለኞቹ›› እና ‹‹ደገኞቹ›› እያለ ከመከፋፈል ባለፈ ፕሬዝዳንቱን ለማስገደልም ሲጣጣር ነበር፡፡ (ሌላው ቀርቶ በኢትዮጵያ ሥም የተደራጀውን የሰሜን እዝ ላይም ጥቃት ሲፈጽምም በማንነት ሸንሽኖ ነበር፡፡)
ታዲያ የትሕነግ አሸናፊነት በመከፋፈል መርሕ ላይ የተመሠረተ እንደመሆኑ ሽንፈቱና ሞቱ ደግሞ ከኢትዮጵያ አንድነት የሚቀዳ ነው፡፡ በመሆኑም ትሕነግ ከሰሞኑን ያጋጠመው መራር ሽንፈት መንታ ሆኖበታል፡፡ በዚህም መሠረት የሚፎክርበት ታጣቂው በሠዓታት ውስጥ በአማራ ሠራዊት ተለብልቦ ከመሸኙቱም በላይ ከየስፍራው በሚተምመው የኢትዮጵያ ሠራዊት ደግሞ ስነ ልቦናውን አንኮታኩቶ ‹‹ወደ ራያ የሄድኩበት እግሬ በተሰበረ ኖሮ›› ብሎ እንዲመኝ አድርጎታል፡፡
➜ትሕነግ ብልጥ ነኝ ብሎ የሚያስብ ሞኛ ሞኝ ድርጅት በመሆኑ ሲዳማ ክልል ስትሆን ‹‹እልልልልል›› የሚል መግለጫ ስላወጣ ብቻ የሲዳማ ሕዝብ በእልልታ የሚምታታ ይመስል መላሹን ክዶ ከአፋኙ ጋር የሚሰለፍ ይመስለዋል፡፡
➜‹‹የትኛውም ሕዝብ ያስባል›› ብሎ ስለማያስብ አንድ የወላይታ መምሕር ጋብዞ ‹‹አጼ ምኒልክ በወላይታ ሕዝብ ላይ ግፍ የመፈጸም ሐሳብ ነበረው›› ማስባል ከቻለ ድፍን የወላይታ ሕዝብ ከእሱ ጋር የተሰለፈ ያህል ይሰማዋል፡፡
➜ልክ እንደሱ ቀየ ዳውድ ኢብሳና የኦሮሞ ሕዝብ አንድ ሆነው ይታዩታል፡፡ አብዲ ኢሌና ሶማሌ ይምታታበታል፡፡
የሰሞኑ ዘመቻ ታዲያ ወደ ሞት ቀጠና ከሚነዳው ሠራዊት ባለፈ ክልሉን እና እራሱን ሲደልልበት የኖረውን የውሸት ትርክት አፈር ድሜ ያስበላ ነው፡፡
በዚህም መሠረት፡-
ጥያቄ ለበልጻጊው መንግስት
➜ህውሓት የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ ሲከፍት ድምጹን የሚያጠፋው መንግሥት ውጊያው ሲጀመር አጸፋውን በመመለስ ፈንታ ምሽጉን አስረክቦ የፕሮፖጋንዳ ጦርነት ውስጥ የሚዘፈቀው ስለምን ይሆን?
የዚህ አይነቱ አካሄድ በየግንባሩ የተሰለፈውን ሠራዊት ለስልችትና ለሞራል ውድቀት እያደረገው አይደለም ወይ?
➜በኮረምና አላማጣ የነበረው ጦር ለምን እንደወጣ ግልጽ መረጃ  በመስጠት ፈንታ ድብብቆሽ መጫወት ለምን አስፈለገ?
➜አሸባሪ አማጺያንን የሚደመስሰው አየር ሃይላችን ከአየር መንገዳችን ጋር ተቀላቅሎ ሲቪሎችን ማጓጓዝ ጀመረ ወይ?
➜ትሕነግን ለመደምሰስ ከየክልሉ የተውጣጣውን ጦር ዝም ብሎ ከማሰልፍ ይልቅ ጠላትን ለማሸነፍ የሚያስችል የአጭር ጊዜ የአቅምና የአቋም ግንባታ ፈጥሮ ማዝመት አይሻልም ነበር ወይ?
➜ከፍተኛው አመራር የችግኝ ተከላውን ለግብርና ሚኒስቴር አስረክበው የችግር ነቀላው ላይ ቢመክሩና ቢሰማሩ አይሻልም ወይ?
➜የምር ግን ብልጽግና ትሕነግን ደምስሶ ኢትዮጵያን አሸናፊ ማድረግ ይፈልጋል ወይ? ‹‹ታግለናል›› ከማለት ባለፈ ‹‹ድል አድርገናል›› ለማለት የሚያስችል ዘመቻ እያካሄደ ነው ወይ?
➜ህውሓት የከባድ መሣሪያ ባለቤት የሆነውና ነፍስ እየዘራ የመጣው በእራሱ ብርታት ወይስ በተጋጣሚው የአመራር ድክመት?
➜‹‹የሒሳብ ማወራረጃ እናደርገዋለን›› እየተባለ ከሚፎከርበት ክልል የወጣ አክቲቪስት የአቶ አገኘሁ ተሻገርን ንግግር በአደባባይ እየዘረገፈ ሕዝብን የመከፋፈያ ቀርቶ የመወያያ ርዕስ ማድረግ ይገባዋል ወይ? ብአዴንስ ከእራሱ የሥልጣን ሽኩቻ ወጥቶ የሕልውና ዘመቻ ቢያደርግ አይሻልም ወይ? በወልቃይትና በራያ ጉዳይስ የያዘው አቋም ተመሳሳይ ነው ወይ?
Filed in: Amharic