>

ህወሀቶች ኢህዴንን ከመቃብር አውጥተው በአጋር ፓርቲነት ከጎናቸው ለማሰለፍ እየጣሩ ነው! (ጌታቸው ሽፈራው)

ህወሀቶች ኢህዴንን ከመቃብር አውጥተው በአጋር ፓርቲነት ከጎናቸው ለማሰለፍ እየጣሩ ነው!
 
ጌታቸው ሽፈራው

ኢህዴን ትህነግ ጫካ እያለ ያቋቋመው አሁንም ድረስ ሸንኮፉ ያልተነቀለ ክፉ ውላጁ ነው። ግማሹን ከኢህአፓ ተገንጥሎ ከወጣው ቡድን አዋቀረው። ግማሹን ከምርኮኛ መለመለ። ከተለያዩ ብሔሮች የተወጣጣውን ይህን ቡድን ቀስ አድርጎ በዋነኛነት ብአዴንና ኦህዴድ አደረገው። 27 አመት በሕዝብ ላይ የጋለበው ይህን ስሬቱን ነው። ጉድህን አልሰማህም!  አሁንም ኢህዴን መሰል ሌላ  አሻንጉሊት ለማቋቋም ወዲያ ወዲህ እየተባለልህ ነው። የአሁኑ ደግሞ የሚገርመው  ይህን ቡድን በዋነኛነት በማዋቀር የተቀመጡትም፣ የቡድኑ አባላትም “40 አመት ውሃ ውስጥ ቢዘፈዘፍ አይረጥብም”  የተባሉት “ድንጋዮች”  ናቸው። የድንጋዮች ፖለቲካ እንዳንለው ብዙዎቹ ሲጫኗቸው ወለም ዘለም የሚሉ፣ ለመሰረትነት ቀርቶ በድንጋይ መሃል፣ ሲሚንቶ ሊለቀለቅባቸውም በአሸዋነት ያልፀኑ ናቸው። የሆነ ሆኖ ፖለቲካም ድንጋይም አይነት አለው። ዝም ብለህ ጠርጥር።  ሌላ ኢህዴን እየመጣልህ ነው።
በአንድ ወቅት ልደቱ አያሌውና ስዬ አብርሃ በሚዲያ ክፉኛ ተወራውረው ነበር። ያኔ ስዬ ዋነኛ ተቃዋሚ ሆኖ፣ ልደቱን የመንግስት ደጋፊ ነው ብሎ ከዋናዎቹ ተቃዋሚዎች ጋር ሆኖ የተከራከሩበት ወቅት ነበር። ብቻ በወቅቱ በተቃዋሚዎች ሲወገር የነበረው ልደቱ እድል ሰጥቶት ስዬን ክፉኛ ደልቆታል። አቶ ልደቱ በአንድ ጋዜጣ ላይ ባሳተመው ፅሁፍ ስዬ አብርሃን ባሕር ውስጥ የከረመ ድንጋይ ቢጨምቁት ውሃ ጠብ አይለውም ብሎ ፅፎበታል። “አቀመሰውኮ” ተብሎ ነበር። ፖለቲካው ውስጥ ብትኖርም አይገባህም ለማለት ያመሳሰለው የድንጋይነት ጉዳይ ስዬን ስሜታዊ አድርጎት ነበር። አሁን ስዬና ልደቱ በዛን መጠን ተራርቀው ይጨፋጨፋሉ ወይ ቢባል አይመስለኝም።  ስዬ ያኔ ከዋናዎቹ ተቃዋሚዎች ጋር ሆኖ ይቃወመው የነበረው ትህነግ ዋነኛ ክንፍ ሆኖ ሌላ ኢህዴን እያደራጀ ነው።  ልደቱ ደግሞ ከሻዕቢያዎች ሕወሓቶች ይሻሉኛል ብሎ በአደባባይ ተናግሯል። ስዬ ደግሞ በአንድ ወቅት ትህነግ ያባረረው፣ ያሰረው ተቃዋሚነቱን አራግፎ የወየነ አዲስ አደራጅ ሆኗል። ለአመታት የፖለቲካ ባሕር ውስጥ ከርሞ አይርስም የተባለው ስዬ የኦሮሞና የአማራ ወኪል ፍለጋ ላይ እየኳተ ይገኛል። ጠርጥር! ኢህዴን ብራንድ ቀይሮ እየመጣልህ ነው!
ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት የትንፋሽ ሕመሙን እየታገለ ስለ ጦርነት ሲፎክር የነበረው ስዬ አብርሃ፣ ፍርድ ቤት ነፃ ሲለው አንጠልጥለው ካሰሩት “ጓዶቹ” ጋር ገደል ለገደል መደበቅ እጣ ባይገጥመውም በፊናው ዓለምን እየዞረ እያደራጀ ነው። ከውጭ ተንከልክለው መጥተው ከሰማይ የአየር ድምፅ ሲሰሙ ደንግጠው ገደል የገቡትን ክፉ አጋጣሚ  ቢያልፈውም እነሱን ከጫካ ለማውጣት ቁልፍ ሰው ሆኖ እየሰራ ይገኛል። ስዬ መቀሌ ደንፍቶ አሜሪካ ነው የገባው። ግን አሜሪካ አልቀረም። ወደ ሱዳን ተመላልሷል። በወልቃይት በኩል እነ ጌታቸው ረዳና ምግበን እንዲቀላቀሉ የተላኩ የሱዳን ሰልጣኞችን እነ ስዬ አግኝተዋቸው ነበር። ስዬ ስለ ፖለቲካም ስለ ወታደራዊ ሁኔታም አሰልጣኝ ነበር። ሰልጣኞቹን ወልቃይት ሰልቅጣ አስቀረቻቸው እንጅ።  ስዬ አብርሃና ጓደኞቹ ቀጣይ አማራን እንዴት ከሶስትና ከአራት ከፋፍለው “ትንሽ” እንደሚያደርጉት ለሰልጠኞቹ አስተምሯል። ምን አልባትም አንዳንድ የአማራ ክልል አመራሮች የማያስታውሱትን ወረዳና ቀበሌ ሳይቀር እየጠሩ አማራን ነፍስ እንዳይዘራ አድርገው በህልም  ከታትፈውላቸዋል። ደግነቱ ይህ እነስዬ አሰልጥነው የላኩት  ከ300 በላይ ኃይል ጥቂት ፋኖዎችን እንኳን ጥሶ የማለፍ  አቅም አልነበረም። የአማራ ልዩ ኃይና መከላከያ ሲደርስ ደግሞ በጨርቅና በፌስታል የቋጠራትን ሀሽሽ ሳይጥል ተይዟል።
ይህን ሀሽሽ ስንቁ ኃይል አማራን እንዴት መበተን እንዳለበት አሰልጥነው የላኩት እነስዬ አብርሃ ታዲያ በውጩ ዓለምም አላረፉም። በእግር ባይሆንም ጫካ ላይ ካሉት ሽህ እጥፍ ሲያቆራርጥ ይውላል። ቀጣዩን ኢህዴን ለማዋቀር ነው አላማቸው። የድኖው ኢህአዴን  የተዋቀረው  አብዛኛውም   የትግራይ ክፍል ተቆጣጥሮ የነበረውን ትህነግና ሕዝቡን ተገን አድርጎ ነበር። አሁን መሬት ላይ ይህን ክህደት የሚሰራ የተገኘ አይመስልም። ቢያንስ ለጊዜው። ስለሆነም ከትግራይ ሳይሆን ከውጩ ዓለም ትህነግ ሲነካ በሕዝብ ስም መግለጫ የሚያወጡትን ሀገራት ከለላ አድርገው ቀጣይ ኢህዴን ይሆነናል ያሉትን  ቡድን ማዋቀር ጀምረዋል።  የድሮውን ሳንነቅል፣ ሌላ ሰንኮፍ እያዋቀሩ ነው!  የከፋው ደግሞ ይህኛው እንደ ድሮው ለስልጣን መወጣጫ አይደለም። በይፋ እንደሚናገሩት ሀገር ለማፍረስ ይጠቅመናል ብለው ነው!
የአሁኑ ኢህዴን ብዙ አጋጣሚ አለው። እንደ ድሮው ዛፍ ስር መሰብሰብ አይጠበቅበትም። ተራራና ገደል ዘልቆ አይደለም አዛዦቹን የሚያገኘው። በዘመናዊ ሆቴል ነው። መጀመርያ ጥቃት የሚፈፅመው ደግሞ ሕይወቱን በሚያጣበት ሁኔታ አይደለም። ታማኝነቱን በሚገባ እያሳየ ያለው በሚዲያ ወጥቶ ሕዝብን በማወናበድ፣ ታዛዥነቱን ሲለምደው ደግሞ ለትህነግ ቀጥተኛ ሽፋን በመስጠት ነው።  ለዚህ ደግሞ በኢትዮጵያ ስም እየነገደ ለትህነግ እየሰራ ያለው ቴዎድሮስ ፀጋዬ በደሕና ጊዜ አማራው ገንዘብ ሰብስቦ ያቋቋመለት መስደቢያ ሚዲያ አለች። “ርዕዮት” ሚዲያ የአዲሱ ኢህዴን መዋጊያ ሜዳ ከሆነች ሰነባብታለች። የትህነግ ከፍተኛ ወታደራዊና ፖለቲካ አመራሮች “የአማራ ልሂቃን” እያሉ ውርጅብኝ ከማዝነባቸው በፊት ዋናዋ አስተኳሽ፣  የጠላት አብሪ ኃይል  ሆና አማራውን ረግማለች፣ ጫካ ያሉት የትህነግ አመራሮች አማራን በልሂቁ በኩል ጥቃት ሲከፍቱበት እንዳንደነግጥ ለማለማመድ ቀድማ ሞክራ፣ ጫካ ያሉት ተከትለዋት ጥሬ ጥላቻቸውን ለቀውብናል። ጫካ ያሉት አማራ ላይ ሂሳብ እናወራርዳለን ከማለታቸው በፊት የአማራ ሕዝብ በትግሬ ላይ ግፍ እየሰራ ነው ብላ የትግራይ ሚዲያ ኃውስን ደረቅ ጥላቻ አዋዝታ አቅርባለች። እነ ጌታቸው ረዳ፣ ፃድቃን ሳምንት ባልበለጠ ጊዜ ተከትለው በአማራው ላይ የጥላቻ ዘመቻ ማጧጧፋቸውን አንዘነጋውም። የአዲሱ ኢህዴን መስራቾች ስለ ሚዲያ ሲያነሱ አንድ፣ ሁለት፣ ሲሉ  የቆጠሯት ርዕዮት የምትባለውን ሚዲያ ነው። አማራን በልሂቅ አልፎም በሕዝብ ደረጃ ፈርጃ ጥቃት ስታለማምድ የተነቃባት ይች የቀጣይ ኢህዴኖች የትግል ሜዳ  ሌላ ስራ ተሰጣት። የአማራን ጉዳይ ያገባናል የሚሉ የቀድሞ ኢህዴኖችን ቀባብታ አመጣቻቸው። ያሬድ ጥበቡና ታምራት ላይኔ!  እነዚህ ወክለው ሲመጡ? የዘመኑ የፖለቲካ ተአምር ልንለው እንችላለን።
ይህ ጉዳይ እንዲገባው የሚፈልግ በቅርቡ ሁለቱ ሰዎች ከቴዎድሮስ ፀጋዬ ጋር ያደረጓቸውን ውይይቶች ማየት ብቻ በቂ  ነው። እባክዎትን ብዙ ሳይደክሙ “የኢትዮጵያ መከራ መውጫ በሮች” ብለው የተወያዩበትን ይመልከቱ። ጊዜ ካለዎት ከዛም ቀጥሎ ያሉትንም አይተው ለመጠርጠር ይዘጋጁ። ቴዎድሮስ ፀጋዬ በቀየኑ እያለማመደ ወደ ትህነግ ትግል ጎራ ከዘፈቃቸው ቆይቷል። ለትህነግ ፊት ለፊት መሟገትን ከሰብአዊ መብት ተሟጋችነት  ጋር ተምታትቶባቸዋል። ይህ ግን ግብ አይደለም። ከሚዲያ አለፍ ብሎ የሚያገኛቸው ሰው ይጠበቃል። ሱዳን ድረስ መጥቶ አማራን እንዴት እንደሚበትኑ ለትህነግ ታጣቂዎች ያሰለጠነው ስዬ አብርሃ  በአማራ ላይ ያለውን ጥላቻ ዋጥ አድርጎ ስለ አማራው ሕዝብ በመግቢያነት አውርቶ፣ ስለ ኢትዮጵያ ትንሽ ብሎ ለቀጣይ ኢህዴን ለማመቻቸት አግኝቶ አውርቷቸዋል።  ስዬ አብርሃ ካገኛቸው በኋላ ሁለቱ የኢህዴን ሰዎች ለይቶላቸዋል። እንዳልኩት ያችን ተሳዳቢ የዩቱዩብ ሚዲያ ገባ ብሎ ማየት ብቻ በቂ ነው። እነዚህ ሰዎች በእርጅና ዘመናቸው የድሮ አቧራቸውን አራግፎ እንደ አዲስ ማምጣት ያስፈለገው ፊት ለፊት የሚመጣ ወጣት  ጠፍቶ ነው። የትናንቱን ውሎ ብቻ ተመልከት። ወጣ የተባለ የድምፅ ቅጅ ላይ የአማራው ፌስቡከኛ ይነታረካል ሲባል “ቅድሚያ ለዘመቻው” ብዙ አስደመመ። የተናደዱ ስለ ትልቅ አላማ ስሜታቸውን ዋጥ አደረጉ። የታሰበው ሲቀር   የትህነግና ኦነግ ብሔርተኛ አጀንዳ ሆኖ ቀረ። የሚወቀሰው የአማራ ማሕበራዊ ሚዲያ ተሳታፊ ሳይቀር ለትልቅ አላማ ሲል ሰከነ። ለአዲስ የኢህዴን ፕሮጀክት አደራጆች ክፉ ዜና ነው። በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያለው አብን ደግሞ እጅጉን አስቸገረ።  በሀገር ሕልውና ላይ አይደራደርም። ትህነግን የእሱን ያህል ቆርጦ፣ በሽብር ይፈረጅ ብሎ የታገለው የለም።  ከሁለት አመት በፊት ትህነግን በሽብር ፈርጁልኝ ብሎ መግለጫ አወጣ። አሁን ትህነግን የሚጠሉም ሳይቀር እንደ ሞኝነት አዩበት። አብን ግን ቀጠለ። ባለፈው አመት ትህነግ “የፌደራሊስ ኃይሎች” ከሚላቸው የሀሰት ትርክተኞች ጋር ሆኖ ሀገር ላይ ያለመውን  ክፉ ህልም ሲመለከቱ ምርጫውን “ይቅርብን” አሉ አብኖች። ወጣቶች ብቻ ሳይሆን ስሜታዊ አድርገው የሚመለከቷቸው ከእነሱ ጠብቀውት የነበረው ይሄን ስክነት አልነበረም። ቀጠለ። ትህነግ ጦርነት ሲያውጅ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ከፊት ከቆሙት መካከል ቀዳሚዎቹ ሆኑ።  መንግስት ሲደክም በሀገር ጉዳይማ ቀልድ የለም ብለው ለዓለም አቀፍ ማሕበረሰቡ ትግራይ ውስጥ ስለሚወራው ውዥንብር ሳይቀር አስረድረው የኢትዮጵያን ሁኔታ በራሳቸው መንገድ ለሚጎትቱ ምቾት አልሰጥ አሉ። ለቀጣይ ኢህዴንነት የሚመች ብዙም አዲስ ትውልድ እንደሌለ ቢያንስ በእነሱ ዘንድ አሳዩ። ሁለተኛውን ኢህዴን ለማደራጀት የተነሱት የትህነግ የውጭ ክንፍ አባላት በሁለተኛው ምርጫ ወቅትም ሌላ እድል አለን ብለው ተስፋ ሰነቁ። አብን ግን የያዘውን ይዞ፣ በምርጫው ወቅት ባማረረው ካድሬ ራሱን ገፍቶ ዳር ከመቆም ሀገር በለጠችበት። ቀጣዩን ኢህዴን “40 አመት ውቅያኖስ ውስጥ ቢኖሩ የማይርሱ ድንጋዮች” ማዋቀር ብቸኛው እጅ ላይ ያለ አማራጭ ሆነ። ቀጣዩን ኢህዴን የሚያደራጀው የትህነግ ተወካይ በራሱ “40 አመት ውቅያኖስ ውስጥ ተነክሮ  ባጅቶ ቢጨምቁት ውሃ የማይወጣው ድንጋይ” የተባለለት ስዬ ነው።  በትህነግና በምዕራባዊያኑ አብን ስለ ሀገር ዘመቻውን ሲደግፍ እንደ መንግስት አካል ተቆጠረ። አንዳንድ የምዕራባዊያን ሀገራት ለፈለጉት አላማ ፈፅሞ አልተመቸም። እንደ መንግስት አካል ቆጥረውት የድሮዎቹን፣ የ40 አመት ውቅያኖስ ኗሪዎችን እንደ አማራ አድርገው እያገኟቸው ነው። አማራን ያስወገሩት፣ እንደ አዲስ ታጥበው ሌላ ማስጠቂያ ለመሆን ተዘጋጅተዋል። ባታምን  ጠርጥር! ለሌላ ክፉ ዘመን  ተሰጥተህ እንዳትመነጠር!
እነ ስዬ አብርሃ የድሮዎቹን ኢህዴን ብቻ አልተማመኑም። ሌሎች ሚዲያዎች ላይ ያሉትንም እየሞካከሯቸው ነው። ርዕዮት የተሰኘችው የትህነግ ሁለተኛ ሚዲያ ደግሞ መፈተኛ ነች። ከአንዱ ሚዲያ ተሻግሮ ርዕዮት ላይ ሲፈተን አላየህም? ከዚህ ፈተና በኋላ የሚሰጠው ተልዕኮ ደግሞ ኃይል መበተን ነው። ማወዛገብ። ርዕስ መፍጠር። ደግነቱ ሰሞኑ ለውጦች አሉ። የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ አማካሪ ምክር ቤት ሳይቀር “አንዳንድ ኢትዮጵያዊ አቋም አለን የሚሉ ሚዲያዎችም” ብሎ ተገቢ ትችት ሰጥቷቸዋል።  ከዛ በኋላ ቀይ መስመር ታያቸው መሰለኝ ትንሽ ገታ ያደረጉት እንዳሉ ትታዘባለህ።  የባልደራስ አማካሪ ምክር ቤት ሚዲያዎችን ትህነግን እየደገፉ፣ ሕዝብን እያወዛገቡ እንደሆነ ወቅሷቸዋል። በግል የስልጣን መና ያሳዩት  ከእነ ስዬ ጋር ወለም ዘለም ማለቱን ሊቀጥል ይችላል።  “ለውጥ” ሲባል ፈልጎ ያጣውን አሁን የሚያገኝ ከመሰለው የሚቀጥል ይኖራል።  በጥንቃቄ ለተመለከተው እየቆየ ይለያል!
የሆነ ሆኖ መሬት ላይ ያለው ጥቃት አፋር ድረስ እግሩን እንደዘረጋው ሁሉ በውጭ ያለው ብዙ አድማስ አካልሏል።  እንደ ድሮው ኢህዴን ከአማራው ብቻ ሳይሆን በኦሮሞውም ዘንድ ሰው ፍለጋ ላይ ሞክረዋል።  “የለውጥ ኃይል” ከተባለው መካከልም አሰላለፍ የለወጠውን እነስዬ ለማግኘት ጥረዋል። “ኢትዮጵያ ሱሴ” ስላለ ብቻ የሚያልፉት አይደለም። በኦሮሞ በኩል ይወክላል የተባለውን ኢህዴን ይመራዋል ተብሎ በእነ ስዬ በኩል ተስፋ የተጣለበት የተገፋው የሱሴ ቡድን ነው። እነ ስዬ ይህን ቡድን ለማነጋገር ብዙም ሀፍረት የለባቸውም። የኦነግ ብሔርተኛው የከረመው ከትህነግ ጋር ነው። ኦ ኤም ኤን ሲሰራ የከረመው የትህነግን ፕሮፖጋንዳ ነው። ሰሞኑን ደግሞ ቅሬታ አለባቸው የተባሉትን የኦሮሞ ዳያስፖራ አባላት ለትግራይ አቻዎቻቸው ጋር ለማነጋገር ጥረት ተደርጓል። ይህን አሰላለፍ የቀየረባቸው ሌላ ችግር ተፈጠረ እንጅ። የኦሮሚያ ልዩ ኃይልም ትህነግ ላይ የሚደረገውን ዘመቻ ተቀላቀለ። በጥረታቸው ላይ ቀዝቃዛ ውሃ እንደቸለሰ ይቆጥሩታል።
የዘንድሮው ኢህዴን ታምራቱ ብዙ ነው። ከምርጫ 1997 ዓ/ም  በኋላ በአስታራቂ  ሽማግሌ ስም ኢህአዴግን ካገዙት መካከል ዳንኤል የተሰኘ  ፓስተር ሳይቀር የእነ ስዬው ቡድን አይን አርፎበታል። ከእስር በኋላ ፖለቲካ አልፈልግም፣ ጌታ ጠርቶኛል ያለው ታምራት ላይኔ ብቻ ሳይሆን ሌላም የእየሱስን ስም እየጠራ ከመንግስተ ሰማያት በፊት ስልጣን የሚመጣ የሚመስለው ከፖለቲካው የማይርቅ “ነብይ” አላጡም።
 በዲፕሎማሲው ዘርፍ አስተባባሪው ብርሃነ ገብረ ክርስቶስ ነው። አሜሪካም ብራሰልስም አምባሳደር ሆኖ  አገልግሏል። ዲፕሎማቶችን ያገኛል። በስሩ ብዙ ሰዎች አሉ። አሁንም ድረስ አዲስ አበባ ላይ እንግሊዘኛ ጋዜጣ የሚያሳትም ሰውም ከስሩ አድፍጦ ለትህነግ ይሰራል። በስራ ልምድ ያገኛቸው የነበሩትን ጋዜጠኞች፣ ዲፕሎማቶች ያገኛል።  ይህ ሰው ከሁለት አመት በፊት  ወደ ውጭ እንደወጣ ነው። እንደ አዲስ ስታንዳርድ  ኃላፊዋ ፊት ለፊት ወጥቶ ብዙም አላስነቃም። አራዳ መሆኑ ነው! ካልጠረጠርክ ብዙው በአንተ ላይ የቀጣይ ኢህዴን እያደራጀ ታገኘዋለህ። የቀድሞው ሰንኮፍ ሳይለቅህ!
የአዲሱ ኢህዴን ተስፋ ሜዳ ላይ አይደለም። “ሜዳ ላይ ያለውን ለእኛ ተውት” ያላቸው  ብዙ አቅም ያላቸው አካል አለ። ” ብቻ ሕዝብ ላይ ስሩ” ተብለዋል። አንዳንዶቹን ስለ ኢትዮጵያ ቀጣይ እጣ ያወሯቸዋል። ብዙዎቹን  ከንቱ አማኞች ወደፊት ስለሚያገኙት የስልጣን መና ይነግሯቸዋል። ለዛም ነው “የውጭ ጫና” ሲባል ደርበው ለመጮህ የሚሞክሩ የበዙት። ወለም ዘለም የሚለው አብዛኛው በተዘዋዋሪ፣ የተወሰኑት በቀጥታ ይህ ፕሮጀክት እንዳለ ተነግሯቸዋል። በወቅታዊ ጉዳይ ዘወር ስትል ሲወዛገብ የምታየውን በቀናነት ጠርጥር። ይህ ፕሮጀክት አወናብዶት ሊሆን እንደሚችል ጠርጥር። አልፎ አልፎ እንዲያው አልፎ አልፎ በቀጥታም ቢሆን የቀጣዩ ኢህዴን አካል ሊኖር እንደሚችል ጠርጥር። የትም የማታውቀው፣ በትህነግ ዘመን ምንም ትንፍሽ ሳይል ዛሬ ደርሶ፣ እንዲያው ፌስቡክ ላይ ቪዲዮው እየተቆረጠ የተዛመተ ተሟጋች ሆኖ ያገኘኸው ሰው የለም? ከየትም አምጥቶት አይደለም። ፕሮጀክት ፕሮፖዛሉን ሲያይ ተደምሞ  ካልሆነ ድሮ አይሞክራትም ነበር? ከቅርብ ሰዎቹ ጋር የእግዜር ሰላምታ ትቶ ሰሞኑን ከምንም ተነስቶ “ሁሉን አቀፍ ድርድር” የሚልህን ዘመናዊ ፖለቲካ ልምሰል ባይ ውሃ ውስጥ ተዘፍቀው ውሃ ጠብ ያላላቸው በፕሮጀክታቸው አቅፈውት ከሆነ ብለህ  ካልጠረጠርክ ጉድ መሆንህ ነው!
ሌላ እስክንጠረጥር ለዛሬው አበቃሁ!
ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት ከስር ያሉትን የፌስቡክና የቴሌግራም ገፆችን ይጎብኙ!
Filed in: Amharic