>

‹‹ታሪክ እራሱን ይደግማል ወይ?›› ለሚለው ጥያቄ መንጌ የሰጠን አስገራሚ መልስ...!!! አሳዬ ደርቤ

‹‹ታሪክ እራሱን ይደግማል ወይ?›› ለሚለው ጥያቄ መንጌ የሰጠን አስገራሚ መልስ…!!!
አሳዬ ደርቤ

‹‹አዎ ታሪክ እራሱን ይደግማል፡፡ ኢትዮጵያ ላይ ደግሞ በተመሳሳይ ታጋዮችና በተመሳሳይ የትግል ስልቶች ተመሳሳይ ታሪኮች ሲደገሙ እያየን ነው፡፡ ለማስረጃም ያህል…
እኔ ኢትዮጵያዊ መሪ ብሆንም እነዚያ የእፉኝት ልጆች ግን አማራ መሆን ኩራት እንጂ ውርደት ያመጣ ይመስል ያለኝን ዜግነት ቀምተው የሌለኝን ማንነት በመስጠት እኔን ብቻ ሳይሆን ሥርዓቱንም ‹‹የአማራ ነው›› እያሉ ያጥላሉት ነበር፡፡ ባሁኑ ሰዓትም በእነሱው ሕገ-መንግሥት የሚመራውን ሥርዓትና የአራት ኪሎውን መንግሥት ‹‹የአማራ ነው›› እያሉ ያንኑ ስብከት ይደግሙት ይዘዋል፡፡
በሁለተኝነት ደግሞ ይህ አሸባሪ ሃይል የእኛን ሥም ለማጉደፍ ሲል የወለደውን ሕዝብ በቦንብ በመጨፍጨፍ እኛን ጠልቶ ከእሱ ጎን እንዲሰለፍ ያደርግ ነበር፡፡ አሁንም ወደ ጦርነት አስገብቶ እራሱ ባስገደላቸው ሕጻናት አስከሬን እየነገደ ነው፡፡
በሦስተኝነት ያኔ የዚህ ቡድን ደጋፊ የነበረችው አሜሪካ አሁንም የዚያው ጥገኛ ቡድን ደጋፊ ሆና ያንኑ ታሪክ ለመድገም እየጣረች ትገኛለች፡፡
ሌላው ደግሞ ይህ ቡድን በወቅቱ የነበረውን ርሐብ እንደ ትግል ስልት ይጠቀምበት ነበር፡፡ እኛም ድሃው ሕዝባችን በርሐብ እንዳያልቅ በሚል ስጋት በተዘዋዋሪ መልኩ አሸባሪውን ሃይል የሚያደልብ ስንቅ ስናቀብል ነበር፡፡ አሁንም የተለመደው ርሐብ የትግል ስልት ሆኖ በዚያው ሕዝብ እነዚያው ግለሰቦች ያንኑ ታሪክ ለመድገም ሲሞክሩ የወቅቱ መንግሥትም እኛ በተሸነፍንበት መንገድ በመጓዝ ለትጥቅና ስንቅ መግዣ የሚውል መቶ ቢሊዮን ብር ሲጎዘጉዝ ከርሟል፡፡
በመጨረሻም ይህ አሸባሪ ቡድን ከእራሱና ከከርሱ ባለፈ አገር ቀርቶ ብሔር እንደሌለው ብናውቅም፣ ቡድኑ ግን ‹‹ብሔር ብሔረሰቦች›› እና ‹‹ዲሞክራሲያዊ መብቶች›› በሚሉ የትግል አጀንዳዎች ያጭበረብር ነበር፡፡ ይሄም ፕሮፖጋንዳው እኛ ጋር ከነበረው ድክመት ጋር ተዳምሮ የአማራውን እና የሌሎችንም ድጋፍ ስላስገኘለት ድል ማድረግ ቻለ፡፡
 የሚገርመው ነገር ታዲያ 27 ዓመት ሙሉ ሥልጣን ላይ ሲቆይ ከእኛ የተረከባቸውን ብሔር ብሔረሰቦች መብትና ማንነታቸውን ሊያስከብር ቀርቶ ቁጥራቸውን ሳያውቅ ነው ከሥልጣኑ የተባረረው፡፡ ‹‹ምን ይሉኝን›› የማያውቀው በዝባዥ ሃይል ግን በዚያው የውሸት ትግል ተመሳሳይ ድል ለማግኘት እየዳከረ ነው፡፡
ሆኖም ግን ቻይናዊው የጦር ጄኔራል ሳን-ዙ ‹‹ተመሳሳይ ታጋዮች፣ በተመሳሳይ የትግል ሜዳዎች ላይ ከሚተገብሯቸው ተመሳሳይ የትግል ሥልቶች የሚገኝ ብቸኛ ውጤት ሽንፈት ይባላል›› እንዳለው ወመኔው ሃይል የለኮሰው ጦርነት ሽንፈቱን ብቻ ሳይሆን የሞት ጽዋውንም የሚጎነጭበት ነው፡፡
.
ምክንያቱም በተመሳሳይ የውሸት ፕሮፖጋንዳ ተታሎ ሁለት ጊዜ አገሩን የሚጎዳ ሕዝብ ስለሌለ ብሔር እያለ ሲያታልላቸው የኖሩት ሁሉ አሁን ላይ አገር ሆነው በሕብረት ዘምተውበታል፡፡ ያን ጊዜ በትከሻው አዝሎ ወደ ቤተ-መንግሥት የሸኘው የኤርትራ ጦርም ዛሬ ላይ ወደ መቃብር ቤት የሚሸኘው ሆኗል፡፡
በትግል ማኒፌስቷቸው ላይ ጠላት ብለው የፈረጁት አማራም ያኔ ከዜግነቱ ባለፈ አማራነቱን የማያውቅ በመሆኑ መንግሥት ሆነው ይገድሉት ዘንዳ ሲረዳቸው ነበር፡፡ ባሁኑ ሰዓት ያለው አማራ ግን እራሱን ብቻ ሳይሆን ጠላቱንም ለይቶ የተደራጀ በመሆኑ በዚያው ማኒፌስቶ ያንኑ ውጊያ ደግመው ጦርነት የለኮሶትን አሸባሪዎች ‹‹ትግሉን እንጂ ድሉን መድገም አትችሉም›› ብሎ እየደቆሳቸው ይገኛል፡፡ እኛም በሽብር ቡድኑ መቃብር ላይ የምንወዳት አገር አሸናፊነት እውን ሆኖ እስክናይ ድረስ ሞት እንዲታገሰን በመጸለይ ላይ እንገኛለን፡፡
ኢትዮጵያ ትቅደም!”
Filed in: Amharic