>

የወታደር ልጅ ነኝ...!!! (ዳንኤል ገዛህኝ)

የወታደር ልጅ ነኝ…!!!


ዳንኤል ገዛህኝ


 

ስወለድ ጀምሮ ጦርነት መሀል ነው የተወለድኩት። የአራስነት ወራቶችን ምሽግ ውስጥ ለማደግ የተገደድንበትን ከጥይት ጩኽት ጋር ተዋህደን ማደጋችን ለቤተሰባችን የማይረሳ ታሪክ ነው።አባቴ በዝያው ጦርነት ገና በወጣትነት እድሜው እየተዋጋ ሳለ ለአስራ አንድ አመት ምርኮ ተዳርጓል። በዝያው የውትድርና ህይወት ሳይደላው በሞት ተለይቷል። አፈሩን ገለባ ያድርግለት። በልጅነቴ ቤተሰባችን ይኖርበት የነበረው ቤት ከጦር ካምፕ ጋር የተያያዘ እና ውሎ እና አዳራችንም ከሰራዊቱ ጋር የተቆራኘ በመሆኑ በአብዛኛው ወታደራዊ ዜናዎች ለቤተሰባችን ቅርብ ነው። በተለይ ምስራቅ ኢትዮጵያ ከ1969 የኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት ዋናው ወረራ በሁዋላ ጦርነቱ በኢትዮጵያ የበላይነት ቢደመደምም ነገር ግን የቀድሞው በኮሎኔል መንስቱ ሀ/ማርያም የሚመራው ሰራዊት በተደጋጋሚ በሚደረግበት የሶማሊያ ሀይሎች አንዴ በረድ አንዴ ሞቅ የሚል ትንኮሳ ሰራዊቱ እንደ ሰሜኑ ሁሉ ጦርነት ውስጥ ቆይቶ ነበር። በዚህ ጦርነት መሀል በልጅነቴ የማልዘነጋቸው ወታደሮች እንደወጡ ሲቀሩ አስታውሳለሁ።
በተለይ የልጅነት ህልሜን አንድ ደረጃ ከፍ ያደረገው የአክስቴ ልጅ መቶ አለቃ መኮንን አባተ መቼም መቼም የምረሳው ሰው አልነበረም። የጦር መኮንን አዋጊም ተዋጊም ፣ የተዋጣለት የእግር ኳስ ተጫዋች ፣ ንቁ መኮንን፣ ቀልጣፋ ተክለ-ቁመና ነበረው መቶ አለቃ መኮንን አባት አፈሩን ገለባ ያድርግለት ነፍሱን ይማረው። ሀዬ በምትባል በምስራቅ ኢትዮጵያ አውደ-ግንባር ላይ ደረቱን ተመቶ ለቁስለኝነት ሳያድር በዚያው አሸለበ። እንደ መቶ አለቃ መኮንን አባተ ሌሎችም ቁጥር ስፍር የሌላቸው በአካባቢዬ የማያቸው በስነ-ምግባር የታነጹ በህዝብ ፍቅር ያበዱ ወታደሮች ቀልቤን ሲገዙት በፍቅራቸው ሲያሳብዱኝ አድጌያለሁ።በልጅነቴ ወታደር የመሆን ጉጉቴ ከፍተኛ ነበር።በተለይ  በ1980 ዎቹ ሀገራችን ኢትዮጵያ ሁሉ ነገርዋን ወደ ሰሜኑ ጦርነት ባደረገችበት ወቅት በየአካባቢው ወታደራዊ ምልመላ ይከናወን ነበር።
በዚያ ወቅት የእኔ እድሜ በሀገሪቱ ስታንዳርድ ለውትድርና አልደረሰም። የነበረኝ አማራጭ እድሜዬ እና የአካዳሚክ ደረጃዬ ብቁ እስኪሆን መጠበቅ የግድ ነበር። ግን ይህ ይሆን ዘንድ እግዚአብሔር ሳይፈቅድ ቀረ። በ1983 እኔ ገና የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ነበርኩ ። ይሁን እና ቀደም ሲል ወደ ወታደራዊ መኮንን ካዴት ኮርስ ለመግባት አስራሁለተኛ ክፍልን ማጠናቀቅ ይጠይቅ ነበር። ነገር ግን ሀገሪቱ ውጥረት ውስጥ ስትገባ የሚያስፈልጋት ሰራዊት ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ ከአስረኛ ክፍል መቀጠር እንደሚቻል መመርያ ወጣ። ይህ ለእኔ ጥሩ ዜና የነበረ

ቢሆንም እድሜዬ ሳይደርስ ወደ አስረኛ ክፍልም ሳልሸጋገር ገና ዘጠነኛ ክፍል ሳለሁ የመንግስት ለውጥ ተደረገ። እናም በህይወቴ ወታደር አለመሆኔ ሲቆጨኝ ይኖራ
ል። እናም በለውጡ ሀገሪቱ ጭራሽ የነበራትን ብቁ ሰራዊት በትኖ ከጥቅም ውጭ የሚያደርግ ስርአት በኢትዮጵያ እውን ሆነ። ይህ ለኢትዮጵያውያን አስከፊ ጉዳይ ሆኖ ቆይቶዋል። ይሁን እና ከሰላሳ አመት በሁዋላ በኢትዮጵያ ወታደር የሚከበርባት ሀገር ብቻም ሳትሆን ዜጎች ለሀገራቸው የሚከፍሉበት በውትድርና ሞያ የሚሳተፉበት ከብሄር አስተሳሰብ በጸዳ መልኩ አገልግሎት የሚሰጡበት መድረክ መመቻቸት ጀምሮዋል። ከጥቂት ወራት ቀደም ብሎ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለወጣ የመንግስት የውትድርና ቅጥር ምላሽ የሰጠው ተመዝጋቢ ቁጥር ከሺህ የሚዘል አልነበረም። ከሰሞኑ የሚታየው በውትድርና ለማገልገል የመፍቀድ እና መነሳሳት የወታደር ልጅነቴን ይበልጥ እንድወደው ብቻም
 ሳይሆን ለሀገራቸው ለመዝምት በየክልሉ የተሰለፉ ምልምል ወታደሮችንም መልካም እድል እንድል ይገፋፋል።
በስተመጨረሻም ከሰሞኑ ለንባብ የበቃው የሻለቃ ወይንሃረግ በቀለ የወታደር ልጅ ነኝ መጽሀፍ በወጉ ሊነበብ የሚገባው ቁም ነገር መሆኑን ልጠቁም እወዳለሁ ወታደርነት ክቡር ሞያ ነው። ህይወት ለሀገር የሚሰጥበት ሰማእታዊ ሞያ።
Filed in: Amharic