>
5:28 pm - Thursday October 10, 8002

የመንግሥት ቅየራው ነገር… !!! (ዘመድኩን በቀለ)

የመንግሥት ቅየራው ነገር… !!!

ዘመድኩን በቀለ

 የፊውዳሉን አገዛዝ የንጉሠ ነገሥት አፄ ኃይለሥላሴን መንግሥት ዙፋን ገዝግዘው ጥለው፣ ከተማሪ እጅ ትግሉን ቀምተው ከካምፕ ለመጣ ወታደር ሥልጣኑን ሰጥተው ፈላጭ ቆራጩን አንባገነን የደርግ መንግሥት በላያችን ለይ የዘፈዘፉብን ምዕራባውያኑ አልነበሩም እንዴ? ኋላ ላይ የሾሙልንን ደርግ ክደው፣ ከወራሪዋ ሶማሊያ ጎን ተሰልፈው፣ ወያኔና ሻአቢያን አስታጥቀው፣ የከፈልንበትን የጦር መሳሪያ ከልክለው፣ ደርግ ፊቱን ወደ ራሺያ ወደ ሶሻሊስት ሃገራት እንዲያዞር አድርገው 17 ዓመታት ሙሉ የውክልና ጦርነት ከፍተውብን ድቅቅ አድርገው እርስ በእርስ አቀጣቅጠውን ሲያበቁ በመጨረሻ ደርግን አስወግደው፣ ኤርትራን ገንጥለው እኛን ያለወደብ አስቀርተው በወያኔ የተኩልን እነሱ ራሳቸው አልነበሩም እንዴ? መለስ ዜናዊን በአናታችን ላይ ተክለው ሲንከባከቡት፣ 100% አሸናፊ ምርጫውን ሁሉ ሲያሞካሹ ሲያንቆለጳጵሱት የኖሩት እነሱ አይደሉም ወይ? ኃይለማርያም ደሳለኝ ይሁን ብለው ምክረ ሃሳብ የሰጡትስ እነርሱ አይደሉም ወይ?
… በ1997 ዓም ቅንጅት ያሸነፈበትን ምርጫ አክሽፈው ሥልጣን እንዳይዝ ያደረጉት ራሳቸው ምዕራባውያኑ አይደሉምን? ከማናውቀው ድንገቴ ኃይል ጋር ከምንቀጥል ከምናውቀው ሰይጣን ከኢህአዴግ ጋር ብንቀጥል ይሻለናል ብለው የቀጠሉት እነርሱ ራሳቸው አይደሉም ወይ? ፖርችጋላዊቷ ሃና ጎበዜ፣ ወይዘሮ አና ጎሜዥ ምርጫው ተጭበርብሯል ብላ እሪሪ ብትል አንሰማሽም ብለው ከጨፍጫፊው መለስ ዜናዊ ጋር የቀጠሉት እነርሱ እኮ ናቸው። ከምን ራሳችንን እናታልላለን። ተቃዋሚውም፣ ገዢው ኢትዮጵያን ለማስተዳደር በተሻለ መልኩ ለምእራባውያን እኔ ታመኝ ነኝ ብሎ ለሽያጭ ራሱን ያቀርባል እንጂ መች ለሃገሬው ተወላጅ ራሱን ይሸጣል? እየተዋወቅን።
… አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በቄሮና በፋኖ ዐመጽ በበቃኝ ሥልጣኑን ሲለቅ ለንደን ላይ ተሰብስበው ለማ መገርሳን ሾመው ለጨረሱት የኦሮሞ የፖለቲካ ኃይሎች “በቃ እኛ ለማ መገርሳን ለጊዜው አናውቀውም፤ ዐቢይ አሕመድን ሹመነዋል አለቀ ንኩት ዳይ ተበተኑ” ብለው ዐቢይን ያሾሙት እነማናቸው እንዴ? ህወሓትን በቃሽ ዞር በይ ያሏት እና መቀሌ እንድትደበቅ ያደረጓት እነማን ናቸው? ያለ ፕሬዘዳንት ትራንፕ ድጋፍ ዐቢይ ሥልጣኑን ይይዘው፣ ህወሓትም ላይ ጦርነት ይከፍት ነበር እንዴ? በስንት ጸሎት የተገኘ ብለው የደሰኮሩለትን ዐቢይ አሕመድን የሾሙብን እነማን ሆኑና ነው አሁን እንደ አዲስ አዋራ የምናስነሣው?
… በነገራችን ላይ አሁንም ድረስ አማሪካኖቹ ዐቢይን ያኮረፉት እንጂ የሚጠሉት አይመስለኝም። ምን አደረጋቸውናስ ይጠሉታል? እነሱ ዐማራ ሥልጣኑን ከተቆጣጠረ አልታዘዝ ብሎ ያስቸግረናል ብለው ሰግተው ቢሆን እንጂ ዐቢይን እስከ አሁን የጠሉት አይመስለኝም። ከህወሓት ጋር በግልጽ አልደራደርም ስላለ ህወሓትን አጀግነው በቃ ተደራደሩ ብለው እጅ ጠምዝዘው ሊያመጧት ስለፈለጉ ነው እንጂ ዐቢይን የሚጠሉበት አንዳችም ምክንያት አይታኝም። ምን ስላደረጋቸው ይቀየሙታል? ተኩስ አቁም አሉት ተኩስ ማቆም አይደለም ጭራሽ ለቆላቸው ወጣ። ቢያኮርፉበት በዚህች ነው። ተኩስ አቁም ሲሉት ጭራሽ ለቅቆ መውጣቱ ያላዘዝንህን፣ ውጣ በምንልህ ሰዓት መውጣት ስትችል ለምን ከትእዛዛችን ወጣህ ብለው ቢቆጡት እንጂ የተጣሉት አይመስለኝም። አንድ ሲጠይቁት 10 የሚሰጣቸውን ቸር መሪ ምን ይሁነኝ ብለው ይጠሉታል?
… መሪ ስትመርጥልን፣ ስትሾምብን የኖረችን ሃገር ደርሶ በድንገት ጣልቃ እንደገባችብን አድርጎ ስሟን ማጥፋትም ነውር ነው። ሕገ መንግሥቱ እንዳይቀየር አለች። ይኸው አይቀየርም ብሎ በወርቅ ካባ ጠቅልሎ በክብር የያዘላቸው ዐቢይን ምን አድርግ ብለው ይጠሉታል? ለህወሓት የጦር መሣሪያ ከነ ስንቁና ወታደሩ እያቀረበላቸው፣ ከራያ ወጥቶላቸው፣ ቆቦን፣ አዲአርቃይን ጀባ ብሏቸው፣ በአፋር በኩል የጅቡቲን መስመር እንዲይዙት እያመቻቸላቸው፣ ምን አድርግ ብለው ይጠሉታል?
… አንዳንዶቻች ደግሞ ዐቢይ አልታዘዝ ስላለ ነው። በተለይ በዓባይ ጉዳይ አቁም ብለውት አላቆምም። አትሙላ ብለውት እሞላለሁ ብሎ ስለሞላ ” ይህቺ ባቄላ ካደረች አትቆረጠምም” ብለው ጠምደውት ነው ሲሉ እሰማለሁ። በዓባይ ግድብ ጉዳይም ዐቢይ አሕመድ ግብጾች እንዳዘዙት፣ አሜሪካኖችም እንዳሉት ነው ያደረገው። የዋሸው የኢትዮጵያን ህዝብ እንጂ እነ ግብፅን ወላሂ፣ ወላሂ ብሎ ከማለላቸው መሃላ ያጎደለባቸው ቅንጣት ያህል ነገር የለም። ይህንንም በምሳሌ እናስረዳ።
… የህዳሴው ግድብ የፕሮጀክቱ ዕቅድ በመጀመሪያው ዙር ሙሊት 4.9 ቢልዮን ኪዩቢክ ውኃ መከተር… በቀጣይ  ዓመት ደግሞ በሁለተኛው ዙር ሙሊት 13.4 ቢልዮን ኪዩቢክ ውኃ በመከተር በአጠቃላይ በሁለት ዓመት በድምር 18 ቢሊዮን ኪዩቢክ ውኃ ከትረን ሞልተን 13ቱንም ተርባይኖች በማንቀሳቀስ ኃይል በማመንጨት የሙከራ ተግባር እንደሚጀመር ነበር ታቀደ ተብሎ የተነገረን። የተሰበክነውም ይሄንኑ ነበር።
… ነገር ግን እሜቴ ግብፅና ወይዘሮ ሱዳን ደግሞ በእንጀራ አባታቸው በአሜሪካ በኩል አይደለም እንደዚያማ አይሆንም። አይደረግምም በማለት ሄጵ አሉ። ግድቡን መገንባት ገንቡ። ጥቅሙ የእኛውም ጭምር ነው። ከውኃ መጥለቅለቅ እንድናለን። ግድቦቻችን በደለል ከመሞላት ይድናሉ። ነገር ግን ውኃውን ለመሙላት በሁለት ዙር 18 ቢልዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ መከተሩን ግን እርሱት። አይቻልም። አይሆንምም። በሁለት ዙር የምትከትሩት ውኃ ከ10 እስከ 12 ቢልዮን k መብለጥ የለበትም። መሙላት ያለባችሁ በዚህ መጠን ብቻ ነው አሉን። እነ ዐቢይ አሕመድም ለእኛ ሄጵ ያሉ መስለው ጀግና ጀግና እየተጫወቱ በውስጥ መስመር ግን እሺ ጌቶቼ ብለው፣ የግብጥና የሱዳንን እጅ ስመው፣ ወላሂ ወላሂ ቃላችንን አናፈርስም ብለው ምለው… በቃላቸው መሰረትም የፈጸሙት ይህንኑ የግብጽንና የሱዳንን ፍላጎት ነው። ለምን ይዋሻል። ከመጨፈሬ በፊት ለመጨፈሬ እኮ ምክንያት እፈልጋለሁ። ሃይ። ዝለል ስለተባልኩማ ዝም ብዬማ አልዘልም። ለምን የሚባል ነገር እኮ አለ።
… ይሄን ግልጽ ለማድረግ የባለፈውን ዓመት የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት ዕቅድ እንመልከት። ኢትዮጵያችን 4.9 ቢልዮን ኪዩቢክ ውኃ እሞላለሁ ብላ ተነሣች። ያ የተባለውም ውኃ ተሞላ። ይሄ ትክክለኛ እና በዕቅዱ መሠረት እንደተነገረን የተሞላው ነው። ነገር የሚመጣው በቀጣዩ  በሁለተኛው ዙር ይሞላል የተባለውን የዘንድሮውን ስናይ ነው። ዘንድሮ 13 ቢልዮን ኪ ውኃ እንደሚሞላ በፀጥታው ምክር ቤት ጭምር ከተነገረ በኋላ ነገር ግን መንግሥት ሰሞኑን ሞላሁ ብሎ የሚያስጨፍረን 7 ቢ.ኪዩቢክ ውኃ ብቻ ነው። የሁለቱን ዓመት የውኃ ክተራ ስንደምረው የምናገኘው ሂሳብም 11.9 ብቻ ሆኖ እናገኘዋለን። 13ም 18ም የተባለው የዘንድሮ ዕቅድ ወፍ የለም። ይሞከራሉ የተባልነውም 13 ተርባይኖችን ሳይሆን ሁለት ተርባይኖች ብቻ መሆኑንም ሰማነ።
… እንግዲህ ይህ ማለት እነ እሜይቴ ግብጥ በሁለቱ ዓመት ሙሌት ከ10-12 ቢሊዮን ኪዩቢክ ውኃ ከትሩ ብለው ያዘዙን ትእዛዝ እንዲያውም 1ነጥብ ዝቅ አድርገን ነው የፈጸምንላት። ይሄን የምሥራች የሰሙት አልሲሲ ህዝባቸውን በስታዲየም ሰብስበው አይዞአችሁ አትስጉ፣ በኢትዮጵያ ያለው መንግሥት የሚያስፈራን አይደለም። ታዛዥ ነው። እንዲሁ ለበዓሉ ድምቀት እንጯጯህ ብለን ነው እንጂ ከትእዛዛችን የሚወጣ አይደለም። አትስጉ አይነት ዲስኩር ያሰሙት የያዙትን ስለያዙ እኮ ነው። መሀመድ አል አልአሩሲም ሰሞኑን የአልጀዚራ ጋዜጠኛ ስንት ቢልዮን ኪዩቢክ ውኃ ከተራችሁ ሲለው መልሱን ከመመለስ ይልቅ ” እናንተ ስንት ኪዩቢክ ውኃ ቀነሰባችሁ በማለት በገደምዳሜ ሳይመልስ ያለፈው ጨዋታውን በደንብ ስለሚያውቀው ነው። አልአሩሲ በዓባይ ወንዝ ቃለመጠይቅ ብቻ ጀግና ተብሎ ዐረብ እንደሆነ የኢትዮጵያን ባርላማ የተቀላቀለ ጀግናችን ነው።
… እና ማን ተጎዳ? ግብጥ፣ ሱዳን ወይስ ኢትዮጵያ? በተራዘመ የጊዜ ሂደት በ20 ዓመት ውኃውን ሙሉ አሉን። እሺ ብለን እየሞላን ነው? 595 ሜትር ግንብ ለመገንባት ዕቅድ ይዘን 575 ሜትር ገነባን። እና ማን ተጎዳ? ማንስ ተጠቀመ? እንዴት እልልል ልበል? በምኑ ልደሰት? መቼም የተጀመረ ነገር አንድ ቀን ማለቁ አይቀርም በሚለው ካልተጽናናን በቀረ የሆነው ይሄው ነው። ለእኔ ይሄም ቢሆን የሚናቅ አይደለም። ድል ነው። ታላቅ ድል። እውነታው ይነገር አልኩ እንጂ አይደለም 7 ቢልዮን ሁለት ቢልዮን ቢገደብም ተቃውሞ የለኝም። ዋናው መገደቡ ነው።
… የሆነው ሆኖ ከዐቢይ አሕመድ ጋር እስኪወድቅ ድረስ እንዲሁ እየተጯጯሁኩ፣ ውሸቱን በአደባባይ እየሞገትኩ እቀጥላለሁ እንጂ ሌባ ተብሎ ታስሮ በወጣው ስዬ አብርሃ፣ በዝሙትና በሌብነት ራሱን አዋርዶ 12 ዓመት ከርቸሌ ጠጥቶ ለወጣው፣ ቤተ ክርስቲያኔን ለ2 ለከፈለው፣ በበደኖ፣ በአርባጉጉ ዐማሮችን፣ በአሰቦት መነኮሳቶችን ያሳረደው ወንጀለኛው ታምራት ላይኔ ለሚመሰርተው የጨበራ አጭቤ መንግሥት እውቅናም ድጋፍም አልሰጥም። እንደነ ስዩም፣ ናትናኤልና ሙክታሮቪች ዐቢይን የተቀባ ነቢይ አድርጌም አልሰብክም፣ እንደነ በለጥሻቸውና ወሮ እቴነሽ፣ ወይዘሪት ከድጃም የማይሳሳት የዝጋቤር ሰውም አድርጌ አልቆጥረውም። አሁን ለዐቢይ የውሸት ፕሮፓጋንዳ አይጠቅመውም። ለዐቢይ የሚጠቅመው የኮሶ ፍሬ የሆነ መራራ እውነት እንጂ ኤሊፖፕ የሆነ የሀሰት ድጋፍ አይጠቅመውም። ታፋው ላይ ሳንጃ ተሰክቶበት መተንፈስ አቅቶት እያያችሁ ዐቢይን፣ ጀግናዬ፣ የእኔ ልዩ፣ ትችላለህ፣ ሺ ዓመት ግዛን ብትሉት ምንም አይጠቅመውም። ለዐቢይ አሁን የሚያስፈልገው አልቻልክም፣ በስብከትና በተረት ሃገር አይመራም፣ እናም ኢትዮጵያን የምትወዳት ከሆነ ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያንን ሰብስበህ ምከር። ለተሻለም ሰው ሥልጣኑን አስረክብ። ሕገ መንግሥቱን ቀይረህ ታሪክ ሥራ ማለት ነው። ለካድሬና ለቤተ እምነት ወዳጆቹ ይከብዳል። ቢከብድም ግን ሞክሩት። ኣ
… ፍቅር ቢኖር፣ ኅብረት ቢኖር፣ ሌብነት፣ ሴራ እና ሴረኞች ባይኖሩ ኖሮ አቢቹ የኢትዮጵያን ህዝብ እንደ አፉ ከልቡ ቢወድ ኖሮ ሕገ መንግሥቱን አሁን ዛሬ ቢቀይረው በተቃውሞ ከመወገድ ይተርፋል። ከመወገድ ባይተርፍም እንኳ ታሪክ ሠርቶ ያልፋል። ያ ሳይሆን ቀርቶ እንዲሁ ችግኝ እየተከልኩ፣ እየተልሞሰሞስኩ፣ እየተኩነሰነስኩ፣ ተረታ ተረት እያወራሁ እቀጥላለሁ ቢል ግን የእነ ጋዳፊ፣ የእነ ሳዳም ዕጣ ፈንታ ከደጁ ነው።
… ተናግሬያለሁ። ጦርነቱ ከትግራይ ክልል ወጥቶ ዐማራ ክልልና አፋር ክልል ገብቷል። የኦሮሞ ጄነራሎች ዐቢይንም ኢትዮጵያንም በቁሟ ሳይሸጧት አይቀርም። እናም አማሪካን ከመውቀስ ወደ ራስ መመልከቱ ይሻላል ባይ ነኝ። ኢትዮጵያ እንደሁ ትነሣለች። በአንድም በለላም ኢትዮጵያን የነካ መድቀቁ አይቀርም። ቻይና አሜሪካንን ለማስፈራራት የበቃችው ዝም ብሎ እኮ አይደለም። ባለፈው ሳምንት እንኳን ለእነ ግብፅ አግዛ በህዳሴው ግድብ ጉዳይ ለፀጥታው ምክር ቤት ደብዳቤ ጽፋ ግድቡ እንዳይገነባ እንቅፋት ስትፈጥር የነበረችዋ ቱኒዚያ ይኸው ሳምንት ሳይሞላት በህዝባዊ ዐመጽ እየተናጠች ነው። ኢትዮጵያን መንካት ያስቀስፋል። በጎርፍም፣ በእሳትም ያስገርፋል። የሃገር ውስጥ ይሁን የውጪ የኢትዮጵያ ጠበኛ፣ ሴረኛ፣ የጊዜ ጉዳይ እንጂ ይደቃታል። ይብላኝ ለሚያሴሩባት፣ ለሚሸጧት እንጂ ኢትዮጵያማ ትነሣለች። ማንም የማይመርጥልን፣ ማንም የማይሾምብን መሪ ከፈለግን የዘር ቦለጢቃን፣ የጎሳ፣ የቋንቋ የክልል አስተዳደርን አስወግዶ ኘ፣ ከፋፋይ የወያኔን ሕገመንግሥት አቃጥሎ ከጎጥ በላይ በአፍ ሳይሆን ከልብ ኢትዮጵያያን የሚያገለግል፣ ብሔራዊ እርቅ የሚፈጥር መሪ መፍጠር አለብን። ያም ሆነ ይህ ኢትዮጵያ ታሸንፋለች። እኔ የማውቀው ይሄንኑ ነው።
Filed in: Amharic