>

በጥላቻ ያበዱ ወታደሮች በሞሉበት ቂሊንጦ      ወህኒ ቤት የባልደራስ አመራሮች ሮሮ....!!! (ጌጥዬ ያለው)

በጥላቻ ያበዱ ወታደሮች በሞሉበት ቂሊንጦ      ወህኒ ቤት የባልደራስ አመራሮች ሮሮ….!!!

ጌጥዬ ያለው

*…. ቂሊንጦ ወህኒ ቤት ከቃሊቲ እስር ቤት በባሰ ደረጃ የእስር ቤት ውስጥ ሌላ እስር ቤት ሆኗል። ይህ ደግሞ እየሆነ ያለው ከሌሎች የፖለቲካም ሆነ የደረቅ ወንጀል እስረኞች በተለየ ለእስክንድር ነጋና ለስንታየሁ ቸኮል ነው።
 
 በተለይም ከምርጫ በኋላ ጭቆናዎች ጨምረዋል። ፍርድ ቤቱ ያዘዛቸው ጉዳዮች አንዳቸውም ተግባራዊ አልተደረጉም። ፀበልና ቅባ-ቅዱስ አሁንም ማስገባት አልተቻለም። እስክንድር ከባለቤቱ ሰርካለም ፋሲል እና ከልጁ ናፍቆት እስክንድር ጋር በስልክ እንዳይገናኝ ዛሬም እንደተከለከለ ነው።  ቤተሰብ፣ የፓርቲ የትግል አጋሮች፣ የሀይማኖት አባቶችና ሌሎችም እንዳሻቸው ሊጠይቋቸው አልቻሉም።
በቀን አንድ ሰው ብቻ ስንቅ እንዲያቀብል ተፈቅዷል። ይሄንም ከሰኞ እስከ አርብ ከሆነ ከአራት እስከ አምስት በሚደርሱ ፖሊሶች ታጅቦ አቀብሎ ብቻ ይመለሳል።
 ለአንድ ደቂቃ ያህል እንኳን አብሮ መቆየት አይችልም። ለአብነትም ትናንት አርብ ሀምሌ 16 ቀን 2013 ዓ.ም. እንዲህ ሆነ፦ ከግቢው በር ጀምሮ እስረኛ እስከ መጠየቂያው ስፍራ ድረስ አምስት ፖሊሶች አጅበው ወሰዱኝ።  ሌሎች ፖሊሶች እስክንድርን አጅበው አመጡት።  ተጨባብጠን “ሰላም ነው እስኬው” ብዬ ሳልጨርስ  እንድወጣ አዘዙኝ። ለሰላምታ መለዋወጫ ብቻ ሁለት ደቂቃ እንዲሰጡን እስክንድር አጥብቆ ቢጠይቅም አሻፈረኝ አሉ።
የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ለምን እንደማያከብሩ ጠይቋቸው ብዙ ተጨቃጨቁ። አስክንድር በብሽቀት ተመልሶ ገባ።
ዛሬ ቅዳሜ ሀምሌ 17 ቀን 2013 ዓ.ም. ደግሞ ይህ  ሆነ፦ እሁድና ቅዳሜ ዘለግ ላለ ደቂቃ ማውራት ስለሚቻል እስክንድርና ስንታየሁ በዚያኛው ገፅ እኔ በዚህኛው አምድ የሽቦ አጥሩን በደረቶቻችን ተደግፈን እየተጨዋወትን ነው። ከሌሎች እስረኞችና ጠያቂዎቻቸው በተለየ አንደኛው ፖሊስ ከዚያ ማዶ ሌላኛው ከዚህ ማዶ ጆሮዎቻቸውን ከጆሮዎቻችን ለጥፈው የምንባባለውን ማዳመጥ ጀመሩ። ደግነቱ እኛም የአደባባይ እንጂ የጓዳ ሃሳብ አላወራንም፤ እነርሱም አማርኛችንን በአግባቡ ለመረዳት የቁቤ ጆሯቸው ሳያስቸግራቸው አይቀርም።
በዚህ መሀል ጆሮን ከጆሮ ለጥፈው ማዳመጣቸውን እንዲያቆሙ ፍርድ ቤት ያዘዘ መሆኑን ጠቅሶ ፈቀቅ እንዲሉ እስክንድር ጠየቃቸው። “ትዕዛዝ አልደረሰንም፤ አይቻልም” ሲሉ የጥላቻ ሳግ እየተናነቃቸው ነበር። በዚህ የተበሳጨው እስክንድር ተሰናብቶኝ፤ ለእነርሱም የመልስ መልስ ሳይሰጥ ወደ ክፍሉ ተመለሰ። ከስንታየሁ ጋር ጨዋታችንን ቀጠልን። ይበልጥ እየተጠጉን ሲመጡ ከሌላው እስረኛ በተለየ ለምን እነርሱ ላይ ይህንን እንደሚያደርጉ ጠየቃቸው። የፖሊሱ መልስ የሽቦ አጥሩ የቆመበትን አግዳሚ እንጨት በቦክስ እየደበደበ መዛት ነበር።  ሌሎች ፖሊሶችም ተሰባስበው በጋራ ስንታየሁ ላይ ዛቱበት። ስታየሁና ፖሊሶቹ በዚህ ጊዜ የሚነጋገሩት እጅግ በጩኸት ድምፅ ነበር። ሌሎች እስረኞችና ጠያቂዎቻቸው ሁሉ ቆመው ይህንን ሲመለከቱ ደቂቃዎች አለፉ።
ተለያየን፤ እኔም ስጋት ገብቶኝ ተመለስኩ። ስጋቴ ከመንግሥት ትዕዛዝ ውጭ (በርግጥ መንግሥት ተብየውም ከእነርሱ አይሻልም) በጥላቻ ያበዱ ወታደሮች እስክንድርና ስንታየሁ ላይ በግልፍተኝነት አንዳች አካላዊ ጉዳት እንዳያደርሱ ነው። የወህኒ ቤቱን ሓላፊ የአቶ ጫላን የመረረ ጥላቻ ስንጨምርበት ይህ የመሆን እድሉ ከፍተኛ ይመስለኛል።
የሀገር ውስጥ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች፣ መገናኛ ብዙሃን እና ዓለም አቀፍ ተቋማት መዝግቡልኝ።
Filed in: Amharic