>

"ከቀነጨረ አዕምሮ ዋልጌ ንግግር መደመጡ አይደንቅም፤  ግን ያማል....!!!" ዓባይነህ ካሴ 

“ከቀነጨረ አዕምሮ ዋልጌ ንግግር መደመጡ አይደንቅም፤  ግን ያማል….!!!”
ዓባይነህ ካሴ

ጌታቸው ረዳ ንግግር አሳመርሁ ብሎ ብዙ ላይ ታች ሲወጣ ሲወርድ ታይቷል፡፡ ሆድ ያባውን ኾኖበት ብቅሉ አውጥቶበታል፡፡ ሕዝብን ያልሰደበ ለመምሰል ወይም ለማደናገር ቢፈልግም አልተሳካለትም፡፡
የኢትዮጵያን ታላቅነት ተረት ተረት ከማለቱ ባሻገር የዐማራን ሕዝብ ባልተገራ ስድ ምላስ ተሳድቧል፡፡ እየቀባባ ለማታለል የዐማራ ሕዝብን ለማድነቅ አንዳንድ ቃላትን የተጠቀመ ቢኾንም ከቆመበት አዙሪት ሊወጣ አልቻለም፡፡ የቆመበት ወይም የተመሠረተበት ነውና በየትኛውም ብልጠት ለማለፍ ቢሞክርም እየጠለፈ ሲጥለው ታይቷል፡፡
መሠረቱ የዐማራ ሕዝብ ጨቋኝ ነው የሚል ብኩል ወይም ምርዝ አስተሳሰብ ነውና ዞሮ ዞሮ ማደሪያው ይህ “ርዕዮተ ዓለሙ ነው”፡፡  አገኘሁ ተሻገርን ወይም ዐቢይ አህመድን የተሳደበ መስሎ ሕዝብን መስደብ ብልግና ነው፡፡ ይህም ጋጠ ወጥነት የተጣባው ዘረኝነት ምልክት ነው፡፡
በንግግሩ መኻል “እንደ አገኘሁ ተሻገር ያለን ሰው መሪ አድርጎ የሚቀበል ማኅበረሰብ የራሱን ጤንነት ቼክ ማድረግ መቻል አለበት፡፡” የዐቢይን ወደ ሥልጣን መምጣት በተመለከተም “የእኔም ኃላፊነት ነው፡፡ ዐቢይ አህመድ ሲመረጥ መጀመሪያ እጄን አላወጣሁም፡፡ ኹለተኛ ዙር ላይ ግን እኔም እጅ አውጥቻለሁ ስለዚህ ከብሌሙ ነፃ ልኾን አልችልም፡፡” ካለ በኋላ አገኘሁ ተሻገርን እና አቢይ አህመድን የአዕምሮ ሕሙማን በማለት ይደመድማል፡፡ አስከትሎም “እነዚህ ዓይነት የአዕምሮ ሕሙማን መሪ አድርጎ የተቀበለ ማኅበረሰብ ነው ቼክ ማድረግ ያለበት ራሱን፡፡” ይላል፡፡
እነዚህ ኹለት መሪዎች ላይ ያለኝ አለመስማማት እንደተጠበቀ ኾኖ ወደ ሥልጣን የመጡበትንም ሒደት ከመኮነን ሳልዛነፍ ከጀርባቸው ያለውን ሕዝብ መስደብ ግን እጅጉን ያበሳጫል፡፡ ሕዝብ በማንም መለኪያ ምሽጉ ሲሰደብ መስማት ያሳምማል፡፡
ምርጫው ዴሞክራሲያዊ ኾነም አልኾነ ፍትሐዊም ኾነ አልኾነ እነዚህ ሰዎች በኾነ ሕዝብ ተመርጠው ሥልጣን ላይ የወጡ ናቸው፡፡ ጌታቸው ረዳ ራሱ የመጣበት መንገድ ተመሳሳይ ነው፡፡ የእርሱን ዕብድ መኾን ዐይቶ ተሳስቶም ይሁን ተገድዶ የመረጠውን ሕዝብ ዕብድ ብሎ ለመሳደብ መድፈር ፈጽሞ ጤነኝነት አይደለም፡፡ ችግሩ ታማሚው አካሚ ሲመስል ነው፡፡ አገኘሁን ወይም ዐቢይን ለማኮሰስ ሕዝብን በዚህ ደረጃ ጤነኝነቱን መጠራጠር ከቆመበት የባለጌነት ሥሪት ነፃ አለመውጣቱን ያመለክታል፡፡
ይህ አንደበት መልሶ የዐማራን ብሎም የኢትዮጵያን ሕዝብ ላወድስ ልቀድስ ቢል ማን ይሰማዋል? ከተጠመቅህበት የዘረኝነት ሽንፍላ ሳትጸዳ በጎሰቆለ እና በቆሰለ ምላስህ ሺህ ጊዜ ብታወድስ መሥዋዕትህ አያርግም፡፡ ደግሞም ከቀነጨረ አዕምሮ ባለጌ ንግግር ቢፈልቅ አይደንቅም፡፡
Filed in: Amharic