>

የቀነጨሩ ፖለቲከኞች ያቀነጨሯት አገር...!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

የቀነጨሩ ፖለቲከኞች ያቀነጨሯት አገር…!!

ያሬድ ሀይለማርያም

*..   ላለመጻፍ ወስኜ ከራሴ ጋር ስሟገት ከረምኩ። አበው እንደሚሉት የጥሞና ጊዜ ለራሴ ልስጥ ብዮ ነው። የኢትዮጵያ ነገር ግራ ያጋባል። ግራ የገባቸው እና የቀነጨሩ ፖለቲከኞች አገሪቱንም፣ ሕዝቡንም፣ አለምንም ግራ የሚያጋባ ድርጊት እየፈጸሙ ግራ ሲያጋቡን ጥሞናን መረጥን። ግን አንድ ሰው በገዛ ሀገሩ እስከመቼ ዝምታን ይመርጣል? ዝምታ ሲበዛ ግፍን እና ግፈኞችን ማጽኛ ይሆናል።
ከቀዳማዊ ጏይለስላሴ መውደቅ ማግስት ጀምሮ እስከ ዛሬዋ ዕለት ኢትዮጵያ በቀነጨሩ ፖለቲከኞች እጅ ወድቃ አንዱ ከሌላው እየተቀባበለ የክሽፈት ተርታ እንዳሰለፏት አስርት አመታትን አሳለፈች። በትንሽ በትልቁ ጸብ ጸብ የሚላቸው እነኚህ የቀነጨሩ ፖለቲከኞች ከየዙፋናቸው ሆነው በሪሞት በሚመሯቸው ትርጉም አልባ ግጭቶች በመቶ ሺ የሚቆጠሩ የድሀ ልጆች የአሞራ ራት ሆነው ቀሩ። ሰሞኑን ቀይ ምንጣፍ ተነጥፎላቸው እና አበባ ተጎዝጉዞላቸው በቦሌ ብቅ ያሉት ኢሳያስ አፈወርቂ እንኳ ከዛሬዎቹ ጠላቶቻቸው ወያኔዎች ጋር ሆነው ኢትዮጵያን መቀመቅ በሚከቱ ጠርነቶች ክፉኛ አድምተዋታል።
ህውሃትና ሻቢያ ግንባር ገጥመው ከደርግ ጋር ባደረጉት ውጊያ መቶ ሺዎችን ማግደው በምዕራባዊያኑ አዋላጅነት ኤርትራ የምትባል የበሬ ግንባር የምታክል አገር ተወለደች። በግራና በቀኝ የተሰለፉት እነኚህ የቀነጨሩ ፖለቲከኞች አገር ገንጥለው፣ የድሀ ልጅ እርስ በርሱ አፋጅተው እነሱ ከነልጆቻቸው በቀጣዩ የህይወት ባቡር ተንጠላጥለው ጉዞ ቀጠለ። በቀነጨሩ ፖለቲከኞች ተረግዛ የተወለደችው ኤርትራ ከምትድህበት ቀና ከማለቷ ወደ ሌላ ዙር ግጭት ተገባ። ደርግን አብረው የወጉ ባልንጀሮች፤ መለስ እና ኢሳያስ ሥልጣን ያመጣባቸውን ስካር መቆጣጠር ስላቃታቸው ብዙ ነገሮችን ተጋርቶ የሚኖረውን የሁለት አገር ሕዝብ ስንዝር በማትሞላ የባድመ ግዛት ጥያቄ ወደከፋ ደም መፋሰስ ነዱት።
እነኚህ የቀነጨሩ ሁለት ፖለቲከኞች እንደዛሬው ጠቅላይ ኖቤል አይሸለሙ እንጂ በምእራባዊያኑ ዘንድ progressive leaders ተብለው ተሞካሽተው ነበር። እነዚህ በአፍሪካ ቀንድ ተአምር ይፈጥራሉ የተባሉ ፖለቲከኞች፤ መለስ እና ኢሳያስ ስልጣን በያዙ በአስር አመት አለምን ያስደመመና ያስደነገጠ ጦርነት አካሄዱ። በሪሞት በሚቆጣጠሩት ጦርነት ወደ መቶ ሺ የሚጠጋ የድሀ ልጅ አስፈጁ። በገንዘብ የደረሰውን ጉዳት መገመት ይቻላል።
መለስን የሚጠላ የድሀ ልጅ ሳይቀር በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች  “ከባዶ ሽሮ ይሻላል ሽራሮ” እያሉ ወጥተው የአሞራ እራት ሆነው ቀሩ። ባዶ ሽሮ ያስበላቸውን ሥርዓት መታገል ቢያቅታቸው ሞትን መረጡ። የቀነጨሩ ፖለቲከኞች ለድሀ ልጅ ታገልን ቢሉም ሁሌም የሚያቀርቡለት ሜኑ  አንድም ባዶ ሽሮ አለያም ሞት መሆኑን ያሳየ ክፉ አጋጣሚ ነበር። ከዚህ አዙሪት ዛሬም አለመውጣታችን ክፉኛ ያማል። ዛሬም የድሀ ልጅ ባዶ ሽሮና ሞት እንደምርጫ ከፊቱ ተደቅነዋል። መቶ ሺ ወጣት የተገበረላት ባድመ ዛሬም ሰላም አላመጣችም።
አስር አመታት እየጠበቀ የሚያገረሸው የፖለቲከኞች ጸብ ጥጋብ ናላቸውን ባዞራቸው ጭንጋፍ የወያኔ መሪዎች ጸብ አጫሪነት በቅርቡ እንደገና ወደ ሌላ ዙር የደም ጎርፍ ተገባ። ትላንት በባድመ ግንባር አንድ ላይ ተሰልፈው ከሻቢያ ጋር ሲዋጉ የነበሩ ወንድማማቾች ከግራ ቀኝ ተሰልፈው ይጋደሉ ጀመር። ሻቢያ እና ወያኔ፤ ደርግን አብረው ወግተው በማግስቱ እርስ በርስ ፍልሚያ እንደገጠሙት ሁሉ ትላንት ሻዕቢያን በባድመ ግንባር ሲያጠቁ የነበሩ ሁለት ሃይሎች አንዱ የሻቢያ ጠላት፣ ሌላው ወዳጅ ሆነው ትግራይን ዳግም የደም መሬት አረጓት።
በአገሩ የማይደራደረው የመከላከያ ሠራዊት እና ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ እነኚህ የቀነጨሩ ፖለቲከኞች በሚፈጥሩት  ቅራኔና የከሸፈ ፖለቲካ አገሩ አደጋ ላይ በወደቀች ቁጥር ሁሌም  ቅሌን ጨርቄን ሳይል ጠላቷን ሊፉለም ይነሳል። ባለፉት 50 አመታት አገሬን እያለ ከቤቱ ወጥቶ በየጦር ግንባሩ የቀረውን ሠራዊት እና የድሀ ልጅ ቤት ይቁጠረው። በሽታ ከፈነገላቸው ውጭ ጦርነቶቹን የጫሩ እና ዳር ቆመው ያጋደሉ ፖለቲከኞች ግን በያሉበት በምቾት አሉ። መንግስቱ እና ኢሳያስ የህይወት ምስክሮች ናቸው።
ይህ የታሪክ ድግግሞሽ አዙሪት የሚያስተምረን ፖለቲከኞች ሲቀነጭሩ አገርብ አብሮ ይከስማል፤ ይቀነጭራል። ልሂቃን እና ፖለቲከኞች በቀነጨሩበት አገር የጨዋ እና ሥልጡን ፖለቲካ፣ ውይይት፣ ድርድር እና የዲሞክራሲ በአል አብረው ይቀነጭራሉ። በቀነጨሩ ፖለቲከኞች አገር የሁሉም ችግር መፍቻ ጉልበት እና ጦርነት ይሆናል።
በቀነጨሩ ፖለቲከኞች መንደር ሞራል ወይም ይሉኝታ ወይም ነውር አይታወቁም። በስካር መንፈሲ ህጻናትን በጦር ውድማ አሰልፈው ‘ኢትዮጵያን ለመበታተን ሲኦልም ቢሆን እንገባለን’ የሚሉ የወያኔ አሸባሪዎችን ያፈራ ፖለቲካችንን ስናስብ ይች አገር በእግዚያብሄር ተአምር ነው ያለች ቢባል ማጋነን አይሆንም። ይህን የሚናገረው ጀብራሬ የዚች አገር ከፍተኛ ባለስልጣን ነበር።
ለማንኛውም አገራችን ከመቼውም በከፋ ሁኔታ ውስጥ ነች። በግራና በቀኝ የተሰለፊ የቀነጨሩ ፖለቲከኞች፣ እንደ ግብጽ ያሉ ታሪካዊ ጠላቶች፣ በገንዘብ የተገዙ ሆድ አደር ልጆቿ፣ ኢትዮጵያን ወደ ትናንሽ አገሮች ለመቀየር አቅዶ ለዘመናት ምቹ ሁኔታዎችን አድፍጦ ይጠብቅ የነበረ አለም አቀፍ ጏይል ልክ አስከሬን እንደከበቡ ጆፌ አሞራዎች ኢትዮጵያን ከበዋታል። እጅግ ክፉ ጊዜ።
ይህን አደጋ ለመቀልበስ እና ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ለማስቀጠል ስክነት የተሞላው የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ስራ ይጠይቃል። ወያኔ በጀመረችው ሴጣናዊ መንገድ አብረን ከተጓዝን ጉዳይ ትግራይን ከማዋለድም ዘሎ ኢትዮጵያን እንደ ዩጎዝላቪያ ወደ መበታተን ያመራል። ወያኔ በተበታተነች ኢትዮጵያ ላይ የምታብበውን ትግራይ እያለመች እንደምትታገል ምንም ጥያቄ የለውም። የምዕራቡም አለም ይህን እኩይ እሳቤ በገንዘብም ሆነ በምክር እየደገፈ የአፍሪካ ቀንድን ወደ ብዙ ትናንሽ እና ለቁጥጥር ወደሚያመቹ አገሮች ሊቀይራቸው የሚችልበትን እድል እያመቻቸ ይመስላል። ስለዚህ ኢትዮጵያ የገጠማት ችግር እና አደጋ ከወያኔ በላይ የገዘፈ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል።
የወያኔን ጭራ እየተከተሉ በዚህ ወጣች በዚህ ገባች፣ ያን ከተማ ተቆጣጠረች፣ ይሄኛውን ለቀቀች የሙሉት ትንታኔዎች፣ ሰበር ዜናዎች እና የክት ፉከራዎች ከዋናው ፍሬ ጉዳይ ያርቀናል። ትግራይን የሚያክል ክልል ለወያኔ አስረክበን ጨዋታው አላማጣ፣ ቆቦ፣ ራያ፣ ኮረም ላይ በሚካሄዱ ወጣ-ገባ ላይ ሲሆን ነገሩ ካልተገለጠልህ ችግር አለ ማለት ነው። ለማንኛውም በመጣንበት የክሽፈትና የቀነጨሩ ፖለቲከኞች ምሪት ዛሬም ከቀጠልን ከለታት በቅርብ ጊዜ ትግራይ የምትባል ጎረቤት አገር ትኖረን ይሆናል። ጠቅላይ ሚኒስትሯም ከአመታቶች ቆይታ በኋላ በአንድ ቀን እንደ ኢሳያስ አፈወርቂ ቀይ ምንጣፍ ተነጥፎላቸው እና አበባ ተጎዝጉዞ በቦሌ ኤርፖርት የወንድማማቾች ውህደት በሚል እንቀበላቸው ይሆናል።
ያ እንዳይሆን ዛሬ ያሉንን እድሎች በጥንቃቄ መጠቀም ይኖርብናል። ከአገር ሉአላዊነት መልስ የሚደረጉ ድርድሮችን በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ በታሪክ ከተሰሩ ስህተቶች መማርም፣ መዳንም ይቻላል።
በቀነጨሩ ፖለቲከኞች አገር ሲቀነጭር የማንም መጫወቻ እንደሚሆን እና የውጭ ሃይሎችን እንደሚስብ ለመማር ኢትዮጵያ ከበቂ በላይ ተመክሮ አላት።
ሰላም ለሀገራችን!!!
Filed in: Amharic