>

"የጐሳ ፖለቲካ እንደማንኛውም ፍልስፍናና ሀሳብ ተወልዶ አድጐ አርጅቶና በስብሶ ተፈጥሯዊ ሞቱን ሞቷል" (የክብር ዶክተር አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን)

“የጐሳ ፖለቲካ እንደማንኛውም ፍልስፍናና ሀሳብ ተወልዶ አድጐ አርጅቶና በስብሶ ተፈጥሯዊ ሞቱን ሞቷል”

የክብር ዶክተር አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን
ሞገስ ተስፋ (ጎንደር)

*….”እናት ከመጨረሻው አስጨናቂ ምጥ በኋላ አዲስ ልጇን አይታ እንደምትደሰተው ሁሉ ሃገራችንም ከገጠማት ማንኛውም አደጋ ወጥታ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት አሸናፊ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም” 
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን በሙያው ለአገሩ ላበረከተው አስተዋጾ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሰጠ።
የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ዛሬ የተቀበለው አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁንም ባደረገው ንግግር፤  “ሃገራችን ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ የገባችበት ከባድ አጣብቂኝና እጅግ ፈታኝ ሁኔታ በሁሉም ዘንድ የታወቀ ቢሆንም እንኳን፤ እናት ከመጨረሻው አስጨናቂ ምጥ በኋላ አዲስ ልጇን አይታ እንደምትደሰተው ሁሉ ሃገራችንም ከገጠማትና ሊገጥማት ከሚችለው ማንኛውም ከባድ አደጋ በደል ወጥታ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት አሸናፊ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም” ብሏል።
ላለፉት ቀላል ለማይባሉ ዓመታት አገራችንን አስጨንቆ የያዛትና አሁንም ላለችበት ቀውስ የዳረጋት የጐሳ ፖለቲካ አሳብ እንደማንኛውም ፍልስፍናና ሀሳብ ተወልዶ አድጐ አርጅቶና በስብሶ ተፈጥሯዊ ሞቱን ሞቷል ሲልም ነው የክብር ዶክተር ቴዎድሮስ ካሳሁን የተናገረው።
ከዚህ በኋላ መላው የሃገራችን ህዝብ  በተለይም ወጣቶች በጎሳና በዘር እንዲሁም በሃይማኖት ልዩነት ሳትናወጡ ከመቼው ጊዜ በላይ በአንድነትና በፍፁም ኢትዮጵያዊ ብሔራዊ ስሜት በተጠንቀቅ ፀንታችሁ መቆም ያለባችሁ መሆኑን በአፅኖት ለማሳሰብ እወዳለሁ ሲልም መልዕክቱን አስተላልፏል።
“እኛ የአዲስቷ የኢትዮጵያ ትንሣኤ የአባቶቻችን ልጆች ኃይላችን ጉልበታችን እና መመኪያችን ፈጣሪያችን እግዚአብሔር ነው፤ ራዕያችንም ፍቅር ሠላምና ፍትህ የሰፈነባት ታላቅ እና ገናና አንዲት ኢትዮጵያን ማየት ነው፤ ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር፤ ፍቅር ያሸንፋል” ሲልም ነው አርቲስቱ ንግግሩን የቋጨው።
Filed in: Amharic