>

የኢትዮጵያን ታሪክ እና ውለታ ያላገናዘበው በቅጡ ሊፈተሽ የሚገባው ‘የፐብሊክ ዲፕሎማሲያችን’ እና ‘የዲፕሎማቶቻችን’ ጉዳይ…(በዲ/ን ተረፈ ወርቁ) 

የኢትዮጵያን ታሪክ እና ውለታ ያላገናዘበው በቅጡ ሊፈተሽ የሚገባው ‘የፐብሊክ ዲፕሎማሲያችን’ እና ‘የዲፕሎማቶቻችን’ ጉዳይ…

(ክፍል -1)

በዲ/ን ተረፈ ወርቁ 


በዚህ ርእሰ ጉዳይ ላይ ጥቂት የመወያያ ሐሳቦችን ከመሰንዘሬ በፊት ለርእሰ ጉዳዩ ጥሩ መንደርደሪያ የሚሆን አንድ ገጠመኜን ላስቀድም፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት በመዲናችን፣ በአዲስ አበባ ላይ በተካሄደ የአፍሪካ ኅብረት ዓመታዊ ስብሰባ ላይ የአፍሪካ ቀዳማይ እመቤቶች ስለአፍሪካ ጉዳይ ተፈጥሮ የቸረቻቸውን የሴትነት ጥበብና ብልሃታቸውን፤ (‘‘የሴት ምክር የእሾኽ አጥር፤ የሴት ብልሃቱን የጉንዳን ጉልበቱን’’ እንዲሉ ኢትዮጵያውያን አበው ወእመው) በመጠቀም ኁልቆ መሣፍርት ለሌለው ለአፍሪካና ለአፍሪካውያን ችግሮች ምክር ለመለገስና መፍትሔ ለማመላከት እነርሱም በዚሁ በመዲናችን ለስብሰባ ተቀምጠው ነበር፡፡

ታዲያ በዚህ የአፍሪካ ቀዳማይ እመቤቶች ስብሰባ ወቅት ከውጪ ጉዳይ ሚ/ር መስሪያ ቤት አንድ የስልክ መልእክት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ የኢትዮጵያ ጥናት እና ምርምር ተቋም ይደርሳል፡፡ መልእክቱም የዛምቢያዋ ቀዳማይ እመቤት የኾኑት ዶ/ር ማውሪን ምዋናዋሳ የቀድሞውን የኃይለ ሥላሴን፣ ገነተ ልዑል ቤተ-መንግሥትን የአሁኑን የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ቤተ-መዘክር/ሙዚየም መጎብኘት ስለሚፈልጉ ፕሮግራም እንዲያዝላቸው የሚያሳስብ ነበር፡፡

በወቅቱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም የሥራ ባልደረባ ነበርኩና ‘ለጥቁሯ እንግዳ’ ለዛምቢያዋ ቀዳማይ እመቤት፣ ለዶ/ር ምዋንሳ ከአለቃዬ ጋር በመሆን ‘የታሪክ ገለጻ’ እንዳደርግ ዕድሉን አግኝቼ ነበር፡፡ ቀዳማዊ እመቤት ዶ/ር ማውሪን ምዋንሳ በዩኒቨርሲቲው የሥራ ኃላፊዎችና በተቋሙ ሠራተኞች ‘የእንኳን ደህና መጡ!’ አቀባበል ከተደረገላቸው በኋላ ባደረጉት ንግግር እንዲህ ነበር ያሉት፤

በአዲስ አበባ ከሚገኙ ታሪካዊ ስፍራዎችና ቤተ-መዘክሮች ሁሉ ይህን የቀድሞውን የግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቤተ-መንግሥትን፣ የአሁኑን አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ለመጎብኘት የመጣሁበት አንድ ትልቅ ምክንያት አለኝ፡፡ ይኸውም፤ ባለቤቴና የሀገሬ የዛምቢያ ፕሬዚደንት የሆነው ዶ/ር ሌቪ ምዋንሳ ከ40 ዓመታት ገደማ በፊት በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ነፃ የትምህርት ዕድል/ስኮላር ሺፕ አግኝቶ የተማረው ንጉሡ ቤተ-መንግሥታቸውን ዩኒቨርሲቲ አድርገው በሰጡት በዚህ ግቢ ውስጥ ነበር፡፡ 

ይህን ታላቅ የሆነ፣ ታሪካዊ የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲ መጎብኘት ለእኔ ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ በዚህ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ መገኘቴ የባለቤቴን የተማሪነት ዘመኑን ጣፋጭ ትዝታዎቹን በዓይነ ሕሊናዬ እንድስለው ከማድረጉም በላይ ይህ ዩኒቨርሲቲ የአገራችሁ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የሀገሬ የዛምቢያ፣ የአፍሪካና የመላው ጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ተምሳሌትና ኩራት የሆነ አፍሪካዊ ተቋም ነው ማለት እችላለሁ፡፡ በእውነትም ንጉሣችሁ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ሩቅ አላሚ፣ የአፍሪካ አባትና ጠበቃ፣ እኛን አፍሪካውያንን በአንድነትና በወንድማማችንት መንፈስ እንድንሰባሰብ መሠረት የጣሉ ታላቅ ባለራእይ ሰው ናቸው፡፡

… በመሠረቱ ይህን ለአፍሪካና ለጥቁር ሕዝቦች ነጻነት ትእምርትና ቀንዲል የሆነ ታሪካዊና ታላቅ ቤተ-መንግሥት/ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካውያን መሪዎችና ምሁራን እንዲጎበኙት ማድረግ ይኖርባችኋል፡፡ በሀገሬ በዛምቢያም ሆነ በሥራ ጉዳይ በሄድኩባቸው የአፍሪካ ሀገራት ስለዚህ ታላቅና ታሪካዊ ቦታ ብዙዎች ሲወራ ሰምቼ አላውቅም፡፡ ይህ ዩኒቨርሲቲ ከእነ ታላቅ ታሪኩና ቅርሶቹ የእናንተ የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካውያን ሁሉ ኩራት የሆነ ተቋም በመሆኑ ለአፍሪካውያን፣ ለተቀረው ዓለም በሚገባ ማስተዋወቅ ይኖርባችኋል…፡፡

ይህ በአንድ በኩል ደስታ በሌላ በኩል ደግሞ ቁጭት የታከለበት የዛምቢያዋ ቀዳማይ እመቤት፣ የዶ/ር ምዋናዋሳ ንግግር አንድ መሠረታዊ ጥያቄ እንድንጠይቅ የሚስገድደን ይመስለኛል- ይኸውም፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሕዝቦች ስላደረገችው ትልቅ ውለታ በአፍሪካም ሆነ በዓለም መድረክ መሪዎቻችንም ሆኑ አምባሳደሮቻችን በሚገኙባቸው መድረኮች ምን ያህል ይናገሩታል? ይህን የሀገራችንን አኩሪ ታሪክ ‘ለፐብሊክ ዲፕሎማሲ’ ሥራ ምን ያህል ተጠቅመንበታል? በአፍሪካና በዓለም ዙሪያ ያሉ አምባሳደሮቻችንስ ይህን የሀገራቸውን ታሪክና ውለታ ለሀገር ምልካም ገጽታ ግንባታም ሆነ ለዲፕሎማሲ ሥራው መሳካት ምን ያህል ተጠቅመውበታል… የሚሉትን ጥያቄዎች ብናነሳ ምላሹ እምብዛም የማያረካ መሆኑን በዲፕሎማሲው መስክ ያለንበት ደረጃ የሚመሰክረው ነው፡፡

የዛሬውን ክፍል አንድ ጽሑፌን ከማጠናቀቄ በፊት ከላይ ካነሳሁት ገጠመኜ ጋር የሚመሳከር አንድ ታሪካዊ ማስረጃ ልጨምርና ልሰናበት፡፡ የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የያኔው የቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያው ፕሬዚደንት የነበሩት ዶ/ር አክሊሉ ሀብቴ፤ “የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርስቲ ታሪክ” በሚል በ2010 ዓ.ም. ካሳታሙት መጽሐፍ ውስጥ በወቅቱ ሀገራችን ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ተማሪዎች ነጻ የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ የተደረገበትን አጋጣሚ እንዲህ ይተርኩታል፤

… የአፍሪቃ ሀገሮች ከቅኝ ግዛት ነፃ የመውጣት ሂደት በጋና ነፃ መውጣት መፋፋም ሲጀመር ቀደም ሲል የጋናው መሪ ዶ/ር ኳሜ ንክሩማ ከሌሎች የካሪቢያንና የአፍሪቃ መሪዎች ጋር በመሆን (ፓን አፍሪካ) አፍሪካ አቀፍ አንድነትና መተባበር እንዲፈጠር እንዲጠናከር ውይይቶች ያካሒዱ ነበር፡፡ ከነዚህ መካከል እ.አ.አ. በ1958 በአክራ ከተማ የተደረገው የነጻ አፍሪቃ ሀገሮች ጉባኤ አንዱ ነበር፡፡

በዚህ ጉባኤ ግርማዊ ንጉሠ ነገሥትን በመወከል የኢትዮጵያ መልእክተኞች መሪ በመሆን የተላኩት ልዑል ሣህለ ሥላሴ ኃይለ ሥላሴ ነበሩ፡፡ ልዑል ኢትዮጵያ ባላት አቅም በዓመት 50 (ኅምሳ) ስኮላርሺፕ ለአራት ዓመት 200 ስኮላርሺፕ ለመላው አፍሪቃ ልጆች ባሉን የከፍተኛ ትምህርት ቤቶች ገብተው አንዲማሩ መወሰናቸውን አንዳስታውቅ አዘውኛል በማለት እንዳበሰሩ፣ ጉባኤው በታላቅ ደስታና ጭብጨባ ተቀበለው፡፡ መልእክተኞቹም ወደሀገራቸው ተመልሰው ደስታውን ለሀገራቸው ተማሪዎች እንዳስታወቁ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገሮች ማመልከቻዎች መጉረፍ ጀመሩ፡፡

በዚያው ዓመት በጥቅምት ወር 1958 19 ተማሪዎች ቀጥሎም በ1961 29 ተማሪዎች ከሰባት የአፍሪቃ ሀገሮች፤ ማለትም ከዛንዚባር፣ ከኡጋንዳ፣ ከጋና፣ ከናይጄርያ፣ ከታንጋኒካ፣ ከኬንያና ሱዳን፣ በዩኒቨርስቲ ኮሌጅና በእርሻ ኮሌጅ፤ በመሐንዲስ ኮሌጅና በግርማዊት እቴጌ መነን ትምህርት ቤት ተመዝግበው ትምህርታቸውን መከታተል ጀመሩ፡፡ ቀስ በቀስም የአፍሪቃ ተማሪዎች የመጡባቸውም ሀገሮች ቁጥር እያደገ ሄዶ፤ ዩኒቨርስቲው ከመከፈቱ በፊት ከመቶ በላይ ስኮላርሺፕ እንደተሰጠና ብዙዎቹ የተመዘገቡት በዩኒቨርስቲ ኮሌጅ፤ በመሐንዲስ ኮሌጅና በእርሻ ኮሌጅ እንደሆነና አብዛኞቹ ተማሪዎችም ከምሥራቅ አፍሪቃ አገሮችና ከናጄርያ እንደመጡ ይታያል፡፡

ፕሮግራሙን ለተከታተለ እንደታሰበው የኢትዮጵያና የተቀሩት የአፍሪቃ ሀገሮች ተማሪዎች የመተዋወቅ ዕድል እንደገጠማቸውና በኋላም ትምህርታቸውን ጨርሰው ከተመለሱት መካከል በሀገር ደረጃ በመሪነት፣ አምባሳደርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ የእርሻ ምርምር ድርጅት አስተዳደርና በግልም የእርሻ ኩባንያ የመሳስሉትን በማቋቋም ከፍተኛ ደረጃ የደረሱና በአፍሪቃም ደረጃ የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ነፃ አውጭ ኮሜቴ ሊቀመንበር በመሆን የልዩ ልዩ ተቋሞች መሪዎች በመሆን ከፍ ያለ አገልግሎት የሰጡ እንዳሉ በየአገሩ በሄድኩበት ጊዜ ለመመልከት ችያለሁ፡፡ በማለት በዚሁ መጽሐፋቸው ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ 

የኢትዮጵያን ታሪክ እና ውለታ ያላገናዘበው በቅጡ ሊፈተሽ የሚገባው ‘የፐብሊክ ዲፕሎማሲያችን እና የዲፕሎማቶቻችን’ ጉዳይ… በቀጣይ ክፍሎች እመለስበታለሁ፡፡ 

ይቀጥላል…

Filed in: Amharic