በጠንካራው ህውሓት ፈንታ ትርፍራፊውን አሸባሪ መደምሰስ ለምን ከበደን?
አሳዬ ደርቤ
ሃያ ሰባት ዓመት ሙሉ ክልሉ ውስጥ ሲያጠራቅመው በኖረው ጦር መሣሪያ እብሪት የተሰማው የትሕነግ ቡድን ወደ ክልሉ ከተባረረ በኋላ ሦስት ዓመት ሙሉ ምሽግ ሲቆፍር ብሎም ኮማንዶና ልዩ ሃይል ሲያሰለጥን ነበር፡፡
ከዚያም በአገር ክህደት ወንጀል ተሰማርቶ የሰሜን እዝ ሠራዊት ላይ መብረቃዊ ጥቃት ፈጽሞ ጦርነቱን ለኮሰ፡፡ ከተሳካለት አራት ኪሎ ገብቶ ለመንገስ ካልሆነ ደግሞ አገር ለማፍረስም ተንቀሳቀሰ፡፡
በዚህም ጥቃት የተደናገጠው የኢትዮጵያ መንግሥት ‹‹ይሄን ከሃዲ ቡድን መደምሰስ ይገባል›› በማለት ወሰነ፡፡
እናም ሰማንያ ፐርሰንት የሚሆነው የጦር መሣሪያ በትሕነግ እጅ በነበረበት እና ኢትዮጵያ የምትኮራበት የሰሜን እዝ በተመታበት ሁኔታ ውስጥ ብንሆንም መንግሥት ቁርጠኛ ስለነበር የክተት አዋጅ ሳይታወጅ፣ በቂ ጊዜ ወስደን ሳንዘጋጅ ሰላሳ ዓመት ሙሉ ትሕነግ ሲዘጋጅበት የኖረውን ጦርነት በሰላሳ ቀናት ድባቅ መምታት ቻልን፡፡
የአሁኑን ያህል ስንቅም ሆነ ትጥቅ፣ ልዩሃይልም ሆነ መከላከያ፣ አገራዊ አንድነትና ሕብረት በሌለበት ሁኔታ ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ ‹‹እነ እከሌ የተባሉ አመራሮችን ስንደመስስ እነ እከሌን ደግሞ በቁጥጥር ስር አዋልን›› የሚል ዜና እንሰማ ጀመር፡፡
ሽሬን፣ አክሱምን፣ አድዋን ያዝን የሚለው እለታዊ ዜናም መቀሌን በመቆጣጠርና አሸባሪውን ቆላ ተምቤን ዋሻ ውስጥ በመወርወር ማጠናቀቅ ተቻለ፡፡ ለምን? መንግሥት እስከ መቀሌ ድረስ ድል የማድረግ ፍላጎት ስለነበረው፡፡
ይህ የድል ፍላጎት ወደ ቁማር ጨዋታ ሲለወጥ ግን…
➜ከዋሻ የወጣ አሸባሪ ሕዝባዊ ማዕበል ቀስቅሶ የሰሜን እዝን ጥቃት በሌላ እዝ ላይ መድገሙን ትሰማለህ፡፡
➜በብዙ መስዋዕትነት እስከ መቀሌ መግባት የቻለው ጦር በቅጽበታዊ ውሳኔ ራያንም ጭምር ለቅቆ ሲወጣ ትታዘባለህ፡፡
➜ክላሽ ይዞ ዋሻ ውስጥ የከረመው አሸባሪ የማረከውን ሳይሆን ወድቆ ያገኘውን ታንክና ከባድ መሳሪያ ታጥቆ ሲተኩስ ታያለህ፡፡
➜በአዲስ የውጊያ ስፍራ ላይ ሕጻናት ሳይቀር አዝምቶ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ አሸባሪን የተናጠል ተኩስ አቁም ያደረገ መንግሥት በፕሮፖጋንዳ ሲመክተው ታስተውላለህ፡፡
➜የክተት አዋጅ ታውጆ በርካታ ወጣት በዘመተበት፣ መላው የኢትዮጵያ ወጣት ለክተት ጥሪው መልስ በሰጠበት፣ የክልል ልዩ ሃይሎች በተሳተፉበት ሁኔታ ተቆጣጠርን በሚል ዜና ፈንታ ያለምንም ሥልጠና ታፍሶ የዘመተው የአሸባሪው ጦር ራያንም አልፎ ቆቦን መቆጣጠሩንና ወደ ወልድያ መጠጋቱን ትሰማለህ፡፡
➜አዋጊ ያጣ ሠራዊትና ፈላጊ ያጣ አንድነት በያዘች አገር ላይ ‹‹መሪ ያለው አሸባሪ›› ያለምንም ከልካይ በወሎ ምድር እየፏለለ ውድመት ሲፈጽም ታስተውላለህ፡፡
➜‹‹ውሰዱት›› በተባለ መሬት ላይ ‹‹አስመልሱት›› የሚል ተውኔት ተጽፎ የተሠጠው ምስኪን ገበሬ በማረሻው ፈንታ ውጅግራውን ይዞ ዋጋ በመክፈል ላይ እንደሚገኝ ትረዳለህ፡፡
➜‹‹አሸንፈን እንመጣለን›› ብለው የዘመቱ አዋጊዎችና ‹‹ተሸንፈን እንመለሳለን›› ብለው ቃል በገቡ አዋጊዎች መሃከል አለመግባባትና ግጭት መከሰቱን ትሰማለህ፡፡