>

ክፍል 3 "አይጥ በበላ ዳዋ ተመታ....!!!" ታምራት ላይኔ በሰረቀው ቡና ንጹሀን ወደ ወህኒ!! (ዳንኤል ገዛህኝ)

“አይጥ በበላ ዳዋ ተመታ….!!!”

ዳንኤል ገዛህኝ
ክፍል 3

ታምራት ላይኔ በሰረቀው ቡና ንጹሀን ወደ ወህኒ!!
ችሎቱ እየተሟሟቀ ሄደ። አስታውሳለሁ ነገር ግን ዳኞች ሊሰየሙ አልቻሉም። መርማሪዬ “ምን አልባት ወደ ጣቢያ ልትመለስ ትችላለህ ምክንያቱም ዳኞች ሊሰየሙ አልቻሉም” በማለት ወደ ባለፍርግርጉ የአንበሳ ቤት ልትመልሰኝ ከችሎቱ ስንወጣ ከጋዜጠኛ ቢንያም ጋር በአንገት ተነጋገርን።
 አንበሳ ቤት ቆርቆሮ በቆርቆሮ የታጠረች አራት በአራት የሆነች ልደታ ፍርድ ቤት ግቢ ውስጥ የምትገኝ የእስረኞች ማቆያ ነች። ልክ ውስጥ ገብቼ እንደተቀመጥኩ ሁለት ተቆራኝተው በካቴና የታሰሩ መልካቸው የሚመሳሰል የኤለመንተሪ ትምህርት ቤት ዩኒፎርም የለበሱ ሴት ልጆች ከፍርግርጉ ውስጥ አምጥተው አስቀመጡ። እርግጠኛ ነኝ ወረዳ 14 ግቢ ውስጥ ከተኮለኮሉት በርካታ ወጣቶች መሀል ተመልክቻቸዋለሁ። እንደማውቃቸው ሁሉ ሰላምታ አቀረብኩላቸው። አጠፋውን መለሱልኝ።  ፓሊሶቹ የኔን መርማሪ ጨምሮ ከአንበሳ ቤት ፈንጠር ብለው ስላሉ ከልጆቹ ጋር ለማውራት ነጻ ነበርኩ።
እናንተን ብቻ ለምን አመጡዋችሁ ?
“እኛም አላወቅንም “
ሌሎቹስ ?
“ጫኑዋቸው”
ወዴት ?
“ሸዋ ሮቢት”
በዚያ ሰሞን ፓለቲከኛው ልደቱ አያሌው እና ጓደኛዎቹ በሸዋ ሮቢት እስር ቤት በባዶ እግራቸው ሲጋዙ መታየታቸው እና በወቅቱ ፍርድ ቤትም ሳይቀርቡ ሰንብተው በሁዋላም በህገ-መንግስቱ ድንጋጌ መሰረት አካልን ነጻ የማውጣት ፋይል ተከፍቶ ነጻ እንዲወጡ ጠበቆቻቸው ፋይል መክፈታቸውን በዜና ሰምተን ነበር።
ግን ምን አጥፍታችሁ ነው ?
“በሰላማዊ ሰልፍ ተከሰን ነዋ”
ሌላኛዋ ተጣማሪ መለሰች…
ሁለቱንም በደንብ አስተዋልኩዋቸው። ቢበዛ አስራሶስት ካነሰ እስራት ሁለት እድሜያቸው ከዚያ አይበልጡም።
ታዲያ ቃል ስትሰጡ በምንድነው የተወነጀላችሁት ?
“የፌደራል መኪና በእሳት አቃጥላችሁዋል ተብለን”
ከራሴ ጋር ተነጋገርኩ። እንዴት እነዚህ ልጆች የሚፈራውን የፌደራል ፓሊስን መኪና ሊያቃጥሉ ይችላሉ?
አንደኛዋ መናገር ቀጠለች…
“እህቴ ነዳጅ እና ክብሪት አመጣችልኝ መኪናው ላይ አርከፍክፌ አቃጠልኩት…ለመርማሪዎች ግን ክጃለሁ…”
አስገራሚ ነው እያልኩ ለራሴ እየተደነቅኩ ሳለሁ መርማሪዬ ጠራችኝ ወደችሎት ይዛኝ ገባች።
እነ ዳኛ ልዑል ገብረማርያም ተሰይመዋል። ቦታ ይዤ ተቀመጥኩ። ችሎቱ ቀጠለ። የኦነግ አባላቶች፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ በሆዳቸው አደንዛዥ ዕጽ ይዘው ለማስተላለፍ የሞከሩ ናይጄርያውያን…ወዘተርፈ ብዙ ከባባድ ጉዳዮች ሲታዩ ዋለ።
የሁዋላ ሁዋላ ስሜ ተጠራ እና የተከሳሽ ሳጥን ውስጥ ገባሁ።
አስፈላጊ መረጃዎችን እየጠየቁ ቆዩ እና ዳኛው ክሴን አንብበው ሲያበቁ የክሱ ቅጅ እንዲደርሰኝ አደረጉ። ለጥቀው ክሱ እንደምቃወም እና እንደማልቃወም ጠየቁኝ ክሱን አልተቃወምኩም ።
 ከዳኛዎቹ ጋር በሹክሹክታ ግራ ቀኝ ተነጋገሩ እና በአምስት ሺህ ብር ዋስትና እንድቆይ እና ክሴን እንድከላከል ያ እስኪሆን በወህኒ እንድቆይ አዘዙ። ወድያው አንድ ሀሳብ መጣልኝ እና ጥያቄ ላቀርብ እጄን ዘረጋሁ።
“ምንድነው ? “
የዳኛው የማመናጨቅ ያህል የበረታ ጥያቄ ነበር።
የተከሰስኩበት ጋዜጣ ህትመት ስላቆመ ዋስትናውን በግሌ ስለምከፍል የዋስትናው መጠን አስተያየት እንዲደረግልኝ ነው የምጠይቀው።
ዳኛው ልዑል ገብረማርያም እሳት ለብሶ እሳት ጎርሶ …
“አንተ ህግ አታውቅም?…ስነስርእት አታውቅም ?”
ዳኛው ከፍ ዝቅ አድርገው አመናጭቀው …
ሲያበቁ …
“ውጣ …”
አስወጡኝ። የወህኒ እስረኛ አመላላሾች ተረከቡኝ። ጋዜጠኛ ብንያም ታገሰ በኩርቱ ፌስታል የተጠቀጠቀውን መኝታ እና ምንጣፍ ፣ልብሶች ሰጥቶኝ አበረታቶኝ ተለያየን።
አንበሳ ቤት ውስጥ እስከ ምሽት አስራ አንድ ሰአት ድረስ ቆይቼ በርከት ካሉ እረኛዎች ጋር በነጭ ሚኒባስ ተጭነን አሁን የአፍሪካ ህብረት ግንባታ ህንጻ ወደተሰራበት ከርቸሌ ተወሰድን። አንዳንድ ለውጦች አሉ። ካቴናዬ ከሁለት እጅ ወደ አንድ እጅ ተቀይሮዋል። የቀኝ እጄ ከሌላኛው እስረኛ ታፈሰ! ታፌ እለው ነበር ተጣምረን በካቴና ተያይዘናል።
ታፌ አጭር ነው፣ የቀይ ዳማ ፣ጎራዳ አፍንጫ ያለው።
ዳንኤል እባለለሁ…
ስለው…
እ…
ብሎ ዝም አለኝ። ስምህን አልነገርከኝም። ብዬ አጣደፍኩት…
“ታፈሰ እባላለሁ…”
ምን አርገህ ነው የተያዝከው…
“ግዳጅ ነው…”
የምን ግዳጅ ?
” ቤት ሰብሮ ዘረፋ…”
ሚኒባሱ ውስጥ ያሉት እስረኞች በአብዛኛው ወጣቶች ናቸው።
ከየት አካባቢ  ነው የመጣኽው ?
‘”ሱሉልታ”
ከምኔው ከልደታ ፍርድ ቤት ተነስተን  ከርቸሌ እንደ ደረስን ሳይታወቀኝ በሩ ላይ ደርሰን እንድንወርድ ተነገረን።
ብዙ የሰው ሀይል ባልመኖሩ በየተራ ወደቢሮ እየገቡ ምዝገባ ማካሄድ በጣም አድካሚ ተግባር ነበር። ሰአቱ እየገሰገሰ ነው ከምሽቱ አስራ ሁለት ሰእት ሊሆን ምንም አልቀረውም።
ገና ስገባ የሰፈሬን ጎረቤት አየሁዋት። እርስዋም ደነገጠች። በለጡ ዮሴፍ ጎረቤታችን ናት ባለቤትዋም እርስዋም የወህኒ ፓሊሶች ናቸው። ከቢሮው ተቀምጣ የእስረኛዎችን መረጃ ትመዘግባለች።ብቀበቶዬን፣ የኪስ ቦርሳ፣ የጫማ ማሰርያ፣ኪሴ ውስጥ የነበሩ ገንዘብ አስመዝግቤ ያዝኩ ጣጣዬን ጨርሼ ከውጭ በሰልፍ ከሚጠብቁ የተለያዩ ወረዳ ፍርድ ቤት እና ፓሊስ ጣቢያ ከመጡ እስረኛዎች ጋር በሶስት ረጃጅም ሰልፎች ወደ እስር ቤቱ ግቢ ዘለቅን።
የእስር ቤቱ የመጨረሻ አጥር ሳናልፍ በሰልፍ ረድፍ እንዳለን ከመሬት እንድንቀመጥ ተነገረን ። አንድ ጠቆር ያለ ቦርጫም መካከለኛ ቁመት ያለው የአዲስ እና ቀጠሮ ክልል የግቢው ስነ-ስነስርአት ኮሚቴ ሀላፊ መሆኑን ነግሮን ተዋወቀን። የግቢውን ተነግሮ ተዘርዝሮ የማያልቅ ህግ እየዘረዘረ ጨቀጨቀን። በሁዋላም …
“እዚህ ውስጥ በተደጋጋሚ የመጣችሁ እስረኛዎችን እያየሁ ነው። በተለይ  በግብረ ሰዶም የተከሰሳችሁ ራሳችሁን አጋልጡና ለብቻ ውጡ…”
ዘመዴ በአይኑ ሁላችንንም ገረመመን። አንድ ከእድሜ ገፋ ያሉ፣ ሁለት ወጣቶች ከሰልፉ ተለይተው ወጡ። የሰዎቹን ሁኔታ ሳይ በጣም የሚያሸማቅቅ ነበር።
“አሁን እያንዳንዳችሁ የለበሳችሁትን ልብስ በማውለቅ እዚህ ትተውታላችሁ…በተለይ ጎዳና ላይ የምትኖሩ ከተለያዩ ደረቅ ጣቢያዎች የመጣችሁ…” የተባሉት የገባቸው በፍጥነት የታዘዙትን አደረጉ። ወድያው ያሁሉ የአዳዲስ እስረኛ ልብስ እያየን ከበሩ አጠገብ በተጣደ የበርሜል ጎላ ብረት ድስት እሳት ተቀጣጥሎበት መቀቀል ጀመረ።
 ውድ ውስጥ ሲያስገቡን ትልቁ አዳራሽ ዙርያውን ጥግ ጥጉን ተደላድለው በተቀመጡ እና በተኙ እስረኞች ተሞልቷል።
መሀሉ ደግሞ የሚያሳዝኑ ጎስቋላዎች አንድ ቦታ ጥቅጥቅ ብለው ተቀምጠውበታል። አዲስ የገባነውን ወደ ሰላሳ የምንጠጋ እስረኞችን ለማነጋገር የቤቱ የምግብ ኮሚቴ ነኝ የሚል ሰው መጥቶ አነጋገረን።
” ልብሳችሁ የተወሰደባችሁ የተሰጣችሁ ቅያሪ ቲሸርት የሚመለስ አይደለም ቅያሪ ይሆናችሁዋል የናንተ ከተቀቀለ በሁዋላ ሲደርቅ ተመልሶ ይሰጣችሁዋል። ሰአት አሁን ከምሽቱ አንድ ሰአት ተኩል ነው…የእናንተ የምግብ በጀት ለዛሬ አልደረሰም ስለዚህ ዛሬ እራት የለም” ብሎን ጥሎን ሄደ።
እዛው ከአዳራሹ እንደተኮለኮልን ሌሎችም አንድ ሳምንት ሁለት ሳምንት የቆዩ አብረውን አሉ ። ምግብ የበላሁት ከአንድ ቀን በፊት ነው። ግን የረሀብ ስሜት የለኝም።
ወደ አምስት ገደማ የሚደርሱ ኮሚቴዎች ሙጥተው ከወደ አንድ መሀል አደረጉን እና አንድ አንድ ሰው እየመረጡ እግር በራስ እያሰባጠሩ አንድ እጅ እና እግር እየያዙ ጠቀጠቁን። እኔም ከአንድ መሀል ደረሰኝ። አስመራ ድርድር እንደሚባለው።
አዳራሹ ሰፊ ነው ለምን እንደዚህ ያደርጉናል በማለት ጠቅጥቀውን ከሄዱ በሁዋላ ከጎኔ ያለውን ልጅ ጠየቅኩት …
“ይሄ ደቦቃ ይባላል አዲስ እስረኛ ሲመጣ ለአስራ አምስት ቀን ግዴታ ነው” አለኝ። አጠገቤ ያለው ልጅ እንደነገረኝ እሱን እና ሌሎች በርካታ ወጣቶች ፈልገውም እንደታሰሩ አወጋኝ። ሰው እንዴት ፈልጎ ይታሰራል ደግሞ ብለው…ከት ብሎ ሳቀ እና ንግግሩን ቀጠለ…
“ምን መሰለህ ጎዳና ላይ ስትኖር በተለይ ክረምት በጣም ከባድ ነው ስለዚህ ክረምቱን እየበላህ እየጠጣህ የምታሳልፍበት ስታስብ የሚመጣልህ ወህኒ ቤት ነው…እዚህ ለመምጣት መንጩ ትሰራለህ !…”
ምንድነው መንጩ ?
“ቦርሳ ወይንም የአንገት ሀብል መንጭቀህ… መንትፈህ መሮጥ ከተማው በፓሊስ እና በደንብ አስከባሪ የተከበበ አይደል አባረው ይይዙሀል ጣቢያ አቆይተው እዚህ ያመጡሀል ዳኛ ሶስት ወር ወይንም ስድስት ወር ይፈርድብሀል ደገሎ እና ሀሰን ደያስህን  እየበላህ ወፍረህ ትወጣለህ በየአመቱ ያምርሀል ትደጋህመዋለህ…”
ሀሰን ደያስ ፓሊስ ጣቢያ ቀምሼዋለሁ ልሙጥ ሽሮ ነው ቆይ ደገሎ ምንድነው?
 ምንድንነው ?
ሳቅ አለ እና …
ንግግሩን ቀጠለ…
“እ…ደገሎ ዱባዮች የሚጋግሩት ከተለያየ የእህል አይነት የሚጋገር ጥቁር ዳቦ ነው…”
ዱባዮች እነማን ናቸው ? ወይስ እየፎገርከኝ ነው ?
“አይደለም ከሴ ቤት የተለያዩ ስሞች አሉ
ዱባይ ማለት ዱቄት ባስቸኩዋይ ይፈጭ ማለት ነው ዱባዮች እህል ይፈጫሉ ዳቦ ይጋግራሉ።”
ከሴ ምንድነው ?
“ከርቸሌውን ከሴ ነው የምንለው … ሁሉንም እየቆየህ ስትሄድ ትለምደዋለህ የከሴ ምግብ ካልጣመህ ስራ አለ እሱን እየሰራህ ከፈለግክ ክትፎ ፣ ጥብስ ፣ ቅልጥጤ ትበላለህ…”
ምንድነው ስራው ? ቅልጥጤ ማለትስ ምን ማለት ነው ?
“ቅልጥጤ ስጋ ወጥ ከቅልጥም ጋር… ስራው ደግሞ አሽኩነት ነው…”
አሽኩ!
“አዎ አሽኩ!…አሽከርነት ማለት ነው”
ወህኒ ቤት ውስት አሽከርነት ?
“አዎ!”
ለማን ነው አሽከርነቱ
“እዚህ ስንት ልጥጥ አለ መሰለሽ”
ያንተ ያለህ! አልኩኝ በውስጤ። ምንድነው ልጥጥ ?
ሀብታም ነዋ! ለልጥጦች ልብስ ታጥባለህ…ሰሀን ታጥባለህ …ምግብ ታቀርባለህ …ትላላካለህ ለሱ የሚመጣ ምግብ አለ የሚተርፈውን ትበላለህ በየሳምንቱ ለሲጋራ ሶስት ሶስት ብር ይሰጥሀል ጥጋብ ነው ምን ትፈልጋለህ…ተኚ በቃ አልደከመሽም ?”
ደክሞኛል ግን እንቅልፍ የለኝም…
‘”አይዞሽ “
ማበረታቻው በእውነት አጽናናኝ… የምጠይቀው አላጣ…ሽንት ቤቱ መግቢያ ላይ በሰንሰለት የታሰሩት ምንድናቸው ?
“ቡሽቲዎች ናቸው !”
ደግሞ ቡሽቲ ምንድነው ?
“ሉጢ ነዋ”
ሉጢ! ሉጢ!
“ፋራ ነሽ እንዴ ! ሸዋዬ ? ስትታይ ሀሪፍ ነገር ትመስያለሽ…እነዚ ወንድ ለወንድ የሚሄዱ ናቸው በር ላይ ራሳቸውን ሲያጋልጡ አላየሽም እነዚህ አንዴ ሽንት ቤት እየዘጉ አንዴ መብራት ሲጠፋ ወላ ሲሳሳሙ መላ ያኛውንም ሲያደርጉ እጅ ከፍንጅ የተያዙ ናቸው”
ነጣም አስደንጋጭ ነው አንድ ስድስት ይሆናሉ እጅ እና እግራቸው በሰንሰለት ታስሮ መተኛት አይበለው ተኝተዋል። ምሽቱ እየገፋ ሄደ እኔ እና ወጣቱ ልጅ ጨዋታችንን ቀጥለናል።
ሁለት ሁለት ሰዎች የተኛንበትን ቦታ ይዞሩታል። እነዚህ ምንድናቸው የሚዞሩን ?
“ተረኛ እንድ ናቸው “
ሮንድ ?
“አዎ ሮንድ”
ምን የሚጠብቁ ሮንድ ?
“የተመሳሳይ አመል ያለው ካለ ይይዛሉ ባለፈው ሳምንት ግምገማ ነበረ በግምገማ  ወደ ሀያ አንድ የሚደርሱ ተያዙ በተለይ መጸዳጃ ቤቱን እየዘጉ እንደፈለጉ ይሆኑ ነበር በግምገማ ለቀሙዋቸዋ። የወያኔ ዘመን ውርሰ ቅርስ ይልሀል አልኩኝ ለራሴ።
ሌሊቱን እንቅልፍ በአይኔ ሳይዞር ሊነጋጋ ሲል ሸለብ አደረገኝ። ይሁን እና ከንጋት አስራ ሁለት ሰአት ለቆጠራ ወደ ውጭ ወጣን። ወድያው በሩ ላይ የሚጠባበቀኝ አንድ ጋዜጠኛ መጥቶ አይን ለአይን እንደተገጣጠምን ጥምጥም አለብኝ። ለካንስ መግባቴን ሰምቶ ቆጠራውን ጨርሶ እየጠበቀኝ ነበር…።
ይቀጥላል!!
Filed in: Amharic