ኢ.ቴ.ቪ
ለጉብኝት አዲስ አበባ የገቡት የአሜሪካ መንግሥት የተራድኦ ድርጅት ኃላፊ ሳማንታ ፓዎር ከኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ጋር ውይይት አድርገዋል።
በውይይቱም ወቅት በትግራይ ክልል በተፈጠረው ሁኔታና የህወሃት አሸባሪ ቡድን እየፈጠረ ባለው ችግር ዙሪያ ለሃላፊዋ ሰፊ ገለፃና ማብራሪያ እንደተደረገላቸው የሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል ገልጸዋል።
የአሜሪካ መንግሥት የተራድኦ ድርጅት ኃላፊ ሳማንታ ፓዎር ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው የህወሃት አሸባሪ ቡድን እየፈፀመ ያለውን ጥፋት በትክክል እንዲረዱ ማስቻሉን ነው የጠቆሙት።
የህወሃት አሸባሪ ቡድን በአገር ላይ በፈጠረው የሀገር የህልውና አደጋ መንግስት ተገዶ ወደ ጦርነት መግባቱንም እንዲረዱ ተደርጓል ብለዋል።
ሆኖም የህወሃት አሸባሪ ቡድን በአገሪቱና በአካባቢው ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖርና ዜጎች ለችግር እንዲጋለጡ በጥፋት መንገድ መቀጠሉን እንዲረዱ መደረጉን ወይዘሮ ሙፈሪያት ተናግረዋል።
ለተራድኦ ድርጅት ኃላፊዋ በተደረገላቸው ገለፃ የህወሃት አሸባሪ ቡድን ስርአት የሚይዝ ከሆነ መንግስት በየትኛውም አማራጭ ለትግራይ ህዝብ ሰብአዊ ድጋፍ ማቅረብ እንደሚችል አረጋግጠውላቸዋል።
በትግራይ ክልል ለሚደረገው ሰብአዊ ድጋፍ በአግባቡ እንዳይደርስ አሸባሪ ቡድኑ እያስተጓጎለ መሆኑን ማስረዳታቸውን አመልክተው፤ ቡድኑ ከእኩይ አላማው የሚታቀብ ከሆነ መንግስት ለህዝቡ ማንኛውንም ሰብአዊ ድጋፍ እንደሚያደርስ አረጋግጠንላቸዋል ነው ያሉት ሚኒስትሯ።
አሸባሪው ህወሃት በመንግስት የተሰጡትን የሰላም አማራጮች እና የመንግስትን የተናጠል ተኩስ አቁም ባለመቀበል በጥፋቱ መቀጠሉን ሃላፊዋ እንድረዱ ተደርጓል።
ቡድኑ በከፈተው ጦርነት በአማራ እና አፋር ክልሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ተፈናቅለው ለከፍተኛ ችግርና እንግልት ስለመዳረጋቸው ማብራሪያ እንደተሰጣቸው ኢዜአ በዘገባው አመልክቷል።
በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ለተፈጠሩት ወቅታዊ ችግሮች ከጅምሩ አስካሁን የህወሃት የሽብር ቡድን ጥፋት መሆኑን ማስረዳት መቻሉን የሰላም ሚኒስትሯ ገልጸዋል።